በሳዑዲ አረቢያ ሞት የተፈረደበት ኬንያዊ ከረጅም ጊዜ ዘመቻ በኋላ በነጻ ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Dorothy Kweyu
በሳዑዲ አረቢያ ሞት ተፈርዶበት የነበረ ኬንያዊ ህይወቱን ለመታደግ ከተደረገ ረጅም ጊዜ ዘመቻ በኋላ በነጻ መለቀቁን የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ስቴፈን አብዱካሪም ሙንያኮ የተባለው ኬንያዊ የተለቀቀው "በፍርድ ውሳኔ" መሆኑን ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎች ያልሰጡት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ጸሐፊ ኮሪር ሲንጎይ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
አንጋፋዋ ጋዜጠኛ እናቱ ዶሮቲ ክዌዩ የልጃቸውን መለቀቅ ዜና ሲሰሙ "ወለል ላይ መንከባለላቸውን" ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
በሳዑዲ አረቢያ ስራ እየሰራ የነበረው ስቴፈን የየመን ዜጋ የሆነውን የስራ ባልደረባውን በአውሮፓውያኑ 2011 በመግደል ነበር የተከሰሰው።
የፈጸመው ወንጀል የሞት ቅጣት የሚያስቀጣ ቢሆንም ከተራዘመ ድርድር በኋላ የተጎጂው ቤተሰብ የገንዘብ ካሳ ለመቀበል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሳዑዲ አረቢያ የእስልምና እምነት ህግን መሰረት ያደረገውን ዲህያ ተብሎ የሚታወቀውን የደም ገንዘብ ካሳ ተጎጂ ቤተሰቦች ከተቀበሉ የሞት ፍርድ የመቀልበስ አሰራር አላት።
ለሟቹ ቤተሰቦች የኬንያ መንግሥት እና 'ዘ ሙስሊም ወርልድ ሊግ' የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት በጋራ 1 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ከጥቂት ወራት በፊት እንደከፈሏቸው የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የስቴፈን የሞት ቅጣት የኬንያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ጣልቃ መግባታቸውን ተከትሎ በርካታ ጊዜያት መራዘሙ ተገልጿል።
ጋዜጠኛው እናቱ የልጇን ህይወት ለመታደግ ረጅም እና ተስፋ አስቆራጭ ዘመቻ ማድረጋቸው ተነግሯል።
"ደስታዬ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው" ሲሉ ከልጃቸው መለቀቅ በኋላ እናቱ መናገራቸውን ስታር ጋዜጣ ዘግቧል።
"በአሁኑ ዙር እውነት ነው። የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር አረጋግጠውልኛል" ብለዋል።
ስቴፈን በ20ዎቹ ዕድሜ እያለ ከ14 ዓመታት በፊት ነበር ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናው፤ በዚያም ሬድ ሲ የተሰኘ ሪዞርት የዕቃ ማከማቻ ስራ አስኪያጅ ነበር።
እናቱ ባለፈው ዓመት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ልጃቸው ከየመናዊ የስራ ባልደረባው ጋር እንደተጋጨ ተናግረዋል።
እሳቸው እንደሚሉት ባልደረባው በፖስታ መክፈቻ ስለት ስቴፈንን ከወጋው በኋላ ልጃቸውም በአጸፋው በዚያው ስለት እንደወጋው ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ የስራ ባልደረባው ህይወቱ አልፏል።
መጀመሪያ በተከሰሰበት ወቅት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል አምስት ዓመት ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም ይግባኝ ተጠይቆበት በአውሮፓውያኑ 2014 የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ጸሐፊ ስቴፈን ከእስር ከተፈታ በኋላ ወደ መካ ሃይማኖታዊ ጉዞ ማድረጉን ተናግረዋል።
ግለሰቡ ወደ አገሩ መቼ እንደሚመለስ የተባለ ነገር የለም።















