የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት: ከ60 ዓመታት በኋላ ዳግም ይመለስ ይሆን?

ዩኒቨርሲቲ መግባት ብርቅ በነበረበት ጊዜ በኢትዮጵያ የነበሩት ተቋማት በአንድ እጅ ጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ የጎንደር ጤና ኮሌጅ እና አለማያ እርሻ ኮሌጅ ነበሩ የሚጠቀሱት።

በጊዜው ጃንሆይ እሳቸው እንደሚሉት 'ለሕዝባቸው' ዝመናን ለማስተዋወቅ፣ ፊደል ለማስቆጠር ይጥሩ የነበረበት ጊዜ ነው።

ለዚያም ነው ቤተ መንግሥታቸውን ተማሪ ቤት እንዲሆን የሰጡት።

ትምህርት ገና መስፋፋት የጀመረበት ጊዜ ቢሆንም ጥራቱ ግን የሚያወላዳ አልነበረም። ትምህርት የጥቂት ባለጸጎች ሆነ የሚል ስጋትም ነበር።

ባሉት ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩት ተማሪዎችመ ከተግባር የተፋቱ፣ ከማኅበረሰባቸው የራቁ የመጽሐፍ ቀበኞች ብቻ መሆናቸው አሳሳቢ ነገር ሆነ።

ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ 'የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አግልግሎት' እንደ መፍትሔ ሆኖ የቀረበው።

ፕሮፌሰር አማረ አስገዶም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የሠሩት በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ልማት እና የአካዳሚክ ነጻነት ላይ ነው።

ከ18 ዓመታት በፊት በጻፉት የፒኤችዲ ማሟያ ጥናታቸው ላይ "ለማኅበረሰቡ አገልግሎት የመስጠትን ሃሳብ ያመነጩት ራሳቸው ተማሪዎች ናቸው" ይላሉ።

ተማሪዎች ለክረምት እረፈት ወደ መጡበት አካባቢ ሲመለሱ ተመሳሳይ አገልግሎቶችን ይሰጡ እንደነበርም ያክላሉ።

የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ባለበት መርገጥ ያላማራቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአንድ ዓመት የግዳጅ አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽፈዋል።

በተማሪዎች ተነስቶ በፕሮፌሰር መስፍን ድጋፍ ያገኘው ይህ አገልግሎት በሚያዚያ 1956 ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ደንብ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ለሁሉም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግዴታ መሆኑን ደንግጓል።

የዩኒቨርሲቲው ካውንስል ተማሪዎቹ አንድ ዓመት በአገልግሎት ላይ ማሳለፋቸው ለአገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለተማሪዎቹም ጠቀሜታ አለው ብሎ እንደሚያምን በዚሁ ደንብ ላይ ሰፍሯል።

ፕሮፌሰር አማረ አስገዶም ከዚህ ውሳኔ ጀርባ ሁለት አመክንዮዎች መኖራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ትምህርቱ በጣም ንድፈ ሃሳባዊ ሆነ፤ መጽሐፍ ላይ ብቻ ያተኮረ የመማር ማስተማር ሂደት በቂ አይደለም [ተማሪዎቹ] ወደ ኅብረተሰቡ ቢገቡ እና በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ነገር በተግባር ቢያዩት እና ቢሞክሩት የበለጠ ሊማሩ ይችላሉ የሚለው ነው ትልቁ ምክንያት" ይላሉ ፕ/ር አማረ።

"ላስተማራቸው ኅብረተሰብ አግልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ" ደግሞ ሁለተኛው ምክንያት መሆኑን ያክላሉ።

ተማሪዎቹ በአንድ ዓመት ቆይታቸው ማስተማር እና ከማስተማር ውጪ ያሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር።

በትምህርት ሚኒስቴር ተቆጣጣሪነት በሚከናወነው የማስተማር አገልግሎት ተማሪዎቹ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ይሰማሩ ነበር።

ሌላኛው ከማስተማር ውጪ ያለው አገልግሎት እንደ ግብርና እና ጤና ባሉ ዘርፎች ላይ በተማሪዎች የሚሰጥ ነው።

በፕሮግራሙ ዕቅድ መሠረት 60 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎችን በማስተማር ቀሪዎቹ ደግሞ በሌሎች ዘርፎች ላይ ማሰማራት ነበር።

ነገር ግን ከአጠቃላይ ተማሪዎች 73 በመቶዎቹ አስተማሪዎች መሆናቸውን ፕሮፌሰር አማረ በዶክትሬት ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።

ፕ/ሩ ይህ የሆነበትን ምክንያት ለቢቢሲ ሲያብራሩ "የሰርቪስ አና ኢንዱስትሩ ዘርፉ በጣም ደካማ ነበር። የተማረውን የሰው ኃይል መቅጠር (absorb) የማድረግ አቅሙ አነስተኛ በመሆኑ ይመስለኛል የታሰበው ቀርቶ አብዛኛው አስተማሪ የሆው" ይላሉ።

ዶ/ር ወንዶሰን ታምራት የተባሉ ተመራመማሪ ከሦስር ዓመታት በፊት በጻፉት መጣጥፍ "የመምህራንን እጥረት ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፣ እንዲሁም መንግሥት የአገር ውስጥ ወይም የውጭ መምህራንን ቢቀጥር ሊያወጣው የሚችለውን ወጪ አድኗል" ሲሉ የዩኒቨርሲቲ አገልግሎትን አስተዋጽዖ ይገልጻሉ።

ፕ/ር አማረ በበኩላቸው "አስር ዓመት ብቻ ስለነበር ሥራ ላይ የዋለው በሰፊው ለአገሪቷ ዕድገት ያደረገውን አስተዋጽዖ ለመናገር ያስቸግራል" ይላሉ።

"በእንጭጩ ነው የተቀጨው የረዥም ጊዜ አስተዋጽዖውን ለማየት በተለይ በትምህርት ዘርፍ ላይ አስቸጋሪ ነው" ሲሉም ያክላሉ።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥትን መገርሰስን ተከትሎ በ1966 ዓ.ም. ተቋርጧል።

ዘናጮቹ አስተማሪዎች

ወይዘሮ ቅድስት በለጠ ሁለተኛ ደረጃ የተማሩት ደብረ ብርሃን ኃይለማሪያም ማሞ ትምህርት ቤት ነው። በአብዮቱ ማግስት በ1965 ዓ.ም. ዘጠነኛ ክፍል እያሉ በዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ኬሚስትሪ ሲያስተምራቸው የነበረውን ተማሪ በቅጡ ያስታውሱታል።

"በጣም ዘናጭ ነበር። ንጽት ያለ ነው ኩስትር ያለ ነው" የሚሉት ወይዘሮ ቅድስት የእጅ ጽሁፉ ሳይቀር ትዝ ይላቸዋል። "እንደ አዲስ መምህር አልነበረም። በጣም ቆንጆ የእጅ ጽሑፍ ነበረው" ይላሉ።

"ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር የመጣው። እንደ ተማሪ አልነበረም ሲያስተምረን የነበረው። ከሌሎቹ መምህራን ያነሰ አልነበረም የሚያስተምረን። በደንብ ነበር የሚያስረዳን በተለይ ኖት ሲጽፍ ትዝ ይለኛል ጥቁር ሰሌዳውን ሙሉ ነበር የሚጽፈው እኛ ራሱ መገልበጥ ይደክመን ነበር" ሲሉ ትጋቱን ያስታውሳሉ።

"ለማስተማር የነበረው ጉጉት፣ ፍላጎት እና ኃይል ትዝ ይለኛል። ከልቡ ነበር የሚያስተምረን ያዝ ለቀቅ ወይም ለብ ለብ አልነበረም። አሁን ስናስበው ተማሪ ሆኖ ያን ያህል ዕውቀቱን ከየት አገኘው? ቁርጠኝነቱስ ከየት መጣ? ብለን እናስባለን" ሲሉ ያክላሉ።

ወይዘሮ አጸደ ወልደሚካኤል ደግሞ ደብረ ሲና አብዬ ትምህርት ቤት እያሉ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተምረዋል።

"ልክ እንደ አንድ መምህር አንድ የትምህርት ዓይነት ይይዛሉ፥ እሱን ያስተምራሉ። እንደ ሂሳብ፣ ፊዚክስ፣ ታሪክ እና ጂኦግራፊ ያሉ ትምህርቶችን ያስተምሩ ነበር" ሲሉ ያስታውሳሉ።

"ሲያስተምሩን ግን በትጋት ነበር፤ ለምን መሰለህ ሥራቸው ስላልነበረ ተማሪዎች ስለነበሩ አዲስ ነገር ሆኖባቸው ይመስለኛል" የሚሉት ወይዘሮ አጸደ ከመምህራኖቻቻው ይልቅ እነዚሀን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጣም ይቀርቧቸው እንደነበረ ይናገራሉ።

"መምህራኖቻችን ትልልቆች ሰዎች ናቸው፤ እንደ አባት ነበር የምንፈራቸው እነዚህ ደግሞ እንደ እኩያ እንደ ጓደኛ ስለሚያደርጉን እንቀርባቸዋልን። ዩኒቨርሲቲ መግባታቸው ያስቀናን ነበር፤ በጣም ነበር ደስ የሚሉን በጣም።"

"ዐይን ከፋች ተሞክሮ"

ዶ/ር ወንዶሰን ታምራት ፕሮግራሙ "ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለይም በተሰማሩባቸው አካባቢዎች እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ስላለው ሕይወት ዐይንን የሚከፍት ተሞክሮ" መስጠቱን በመጣጥፋቸው ላይ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት በ1960ዎቹ መጀመሪያ እና አጋማሽ ለተቀጣጠለው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ይነገርለታል።

በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ አካባቢዎች ያለውን ኅበረተሰብ አኗኗር በቅርብ ለመታዘብ ችለዋል። ይህም በአገሪቱ የተንሰራፋውን የከፋ ድህነት እና ኋላቀርነት እንዲረዱ አድርጓቸዋል።

ፕሮፌሰር አማረ "ኅብረተሰቡን ፖለቲካ አስተምረዋል። ይሄ የማይፈለግ ነበር፤ ኅብረተሰቡን ፖለቲካ አስተምረዋል፣ አነቃቅተዋል፤ ራሳቸውም ነቅተው እንዲደራጁ አድርገዋል። የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ያደረገው አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው" ይላሉ።

ወይዘሮ አጸደም ይህን የሚያጠናክር ትውስታ አላቸው።

ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከተዘዋወሩ በኋላ ደብረ ብርሃን ትምህርታቸውን የተከታተሉት ወይዘሮ አጸደ "ሃይስኩል ከገባን በኋላ አልፎ አልፎ አንዳንዶቹ በደንብ ያደራጁ ነበር። በጣም ያደራጁ ነበር፤ በቡድን በቡድን እየጠሩ እንደጓደኛ ምናምን የሆኑትን እየሰበሰቡ ያነቁ ነበር" ሲሉ ያስታውሳሉ።

አንጋፋው የቀድሞው የኢህአፓ አመራር አቶ ክፍሉ ታደሰም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ተማሪዎች ከሕዝብ ጋር አንዲቀራረቡ ማድረጉን ይገልጻሉ።

በ1960 ትምህርት ለሁሉም የሚል ጥያቄ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ ተነስቶ ነበር፤ በየቦታው ተማሪዎች ሰፊ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር።

በዚህ ወቅት በባሕር ዳር ከተማ አጼ ሰርጸ ድንግል ትምህርት ቤት ያስተምር የነበረ አንድ ተማሪ ይህ ጉዳይ ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፋ ፍላጎት እንደነበረው አቶ ክፍሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ይህ ለዩኒቨርሲቲ አገልግሎት የመጣ ወጣት እኔ እና አንድ ጓደኛዬን ያገኘናል። ሦስታችንም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ነበር የተማርነው። ባሕር ዳር ላይ ተመሳሳይ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መደረግ አለበት ይለናል። መልዕክቱ ወደ ባሕር ዳር እንዲተላለፍ እና ተማሪዎች እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል" ሲሉ ያስታውሳሉ።

እንደ አቶ ክፍሉ ገለጻ ይህን ሃሳብ ባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ እና አጼ ሰርጸ ድንግል ትምህርት ቤት ባሉ ተማሪዎች ተቀባይነት ማግኘቱን እና ተማሪዎችም አድማ አድርገዋል።

የኢሕአፓ ወታደራዊ ክፍል (ኢሕአሠ) አባል የነበረው ፀጋዬ ገብርመድኅን (ደብተራው) በርካታ ተማሪዎች ማፍራቱንም አቶ ክፍሉ ይናገራሉ።

"ፀጋዬ ጎንደር የተማሪዎች እንቅስቃሴ እንዲነሳ ሚና ነበረው። በተለይ በጤና ኮሌጁ እና በሁለተኛ ደረጃ አካባቢ የነበሩ ተማሪዎችን በመቅረብ ትግሉ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ሰዎችን አፍርቷል" ይላሉ።

የዩኒቨርሲቲ አገልግሎት ዳግም ይመለስ ይሆን?

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ አገልግሎት በመጪው ዓመት ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ተናግረዋል።

ይህ ሃሳብ ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በድጋሚ የተነሳው ግን አሁን አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 2018 የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከቅድመ ምረቃ ትምህርታቸው የመጨረሻ ዓመት በፊት የኢንተርንሺፕ አገልግሎትን እንደገና ማስተዋወቅን በምክረ ሃሳብ ደረጃ አቅርቧል።

ፍኖተ ካርታው ተማሪዎች ከትምህርት ዘርፋቸው ጋር በሚያያዙ ጉዳዮች ላይ እንዲሠሩ ከተወለዱበት አካባቢ ውጪ እንዲመደቡ ይጠይቃል። ይህ ምክረ ሃሳብ የቀረበው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አንድነትን ለማጠናከር ነው።

የፌደራል ሥርዓቱ ከተጀመረ በኋላ "በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ያለው አንድነት መሸርሸሩን" ፍኖተ ካርታው ይጠቅሳል።

ሰነዱ "ይህ የአንድ ዓመት አገልግሎት የኢንተርንሺፕ ፕሮግራም የዩኒቨርሲቲ ትምህርት አካል መሆን አለበት" ይላል። ተማሪዎቹን የሚቀበሉት ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲው የፕሮግራሙን ወጪዎች መሸፈን ሊኖርባቸው እንደሚችልም ያስቀምጣል።

ፕሮፌሰር አማረ አስገዶም ፍኖተ ካርታው ላይ ምክትል ፕሮጀክት ኃላፊ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቡድን መሪ ሆነው ሠርተዋል።

የዩኒቨርሲቲ አገልግሎትን በምክረ ሃሳብ ደረጃ ካቀረቡት ሰዎች መካከል አንዱ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

ፕ/ሩ የዩኒቨርሲቲ አገልግሎት መጀመር አለበት እንዲሉ ያደረጋቸውን ምክንያት ሲያብራሩ በክፍል ውስጥ የሚከናወነው የመማር መስተማር ሂደት ውጤታማ አለመሆንን በማንሳት ነው።

"አሁን ትምህርት ክፍል ውስጥ ቀርቷል። ተማሪዎች በዐይናቸው እየዩ በእጃቸው እየጨበጡ ራሳቸው እያስተዋሉ ራሳቸው የሚማሩበት እና በሪፖርት መልክ ሥራቸውን እያቀረቡ የሚገመገሙበት ሥርዓት ነው ያለው" ይላሉ።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት በመማሪያ ክፍሎች ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚያነሱት ፕ/ር አማረ፤ "ተማሪዎች ከዚህ የክፍል ውስጥ ትምህርት መገላገል አለባቸው። ቢያንስ ለአንድ ዓመት ከመማሪያ ክፍሎች ተማሪዎችን ቢገላግሏቸው አንድ ነገር ነው። ፈጽሞ ለመማር ማስተማር የማይሆኑ ትምህርት ቤቶች ናቸው ያሉን። ስለዚህ ይሄ አንድ የተማሩትን ነገር መልሰው እንዲመረምሩ እና መጠነኛ የሆነ መረዳት እንዲኖራቸው ያደርጋል" ሲሉ ያብራራሉ።

"በአሁኑ ወቅት እና አሁን ባለው ሁኔታ ምን ያህል ውጤማ ይሆናል በምን ዓይነት ሁኔታ ይፈጸም የሚለው ሌላ ነገር ነው" ሲሉ አፈጻጸሙ ሌላ ጥናት እንደሚያስፈልገው ይገልጻሉ።

"ይህ ግብ በፖለቲካዊ አዝማሚያዎች እና በአገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግ በቀላሉ ማሳካት ይቻላል ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው" የሚሉት ዶ/ር ወንዶሰን በበኩላቸው "አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ለእንደዚህ ዓይነት ዕቅድ ስኬት የራሱ የሆነ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል" ይላሉ።