ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሙዝ በዳቦ እየበሉ 'ፒኤችዲ' የሚማሩ የዩኒቨርስቲ መምህራን ሰቆቃ
“…አስተማሪን? በጫማው ትለየዋለሁ እኮ። አንድን ጫማ ለብዙ ዓመታት ነው የምንጫማው። ብዙ ሲረገጥ የአቀማመጥ ሚዛኑን ያጣል።
“እኛ ግቢ ብትመጣ ትደነግጣለህ። የብዙ መመህር ጫማ ተንሻፎ ነው ያለው። ድምጽ አውጥቶ ‘ጣሉኝ!’ ነው እያለ ያለው። እንዴት ትጥለዋለህ? ግማሽ ደመወዝህ ደህና ጫማ እንደማይገዛ እያወቅክ?
“ታች ግቢ ለምሳሌ ኮመን ኮርስ የምንሰጣቸው የኢንጂነሪንግ ተማሪዎች አሉ። 5 ዓመት ገደማ ዩኒቨርስቲ ይቆያሉ። እና ሸፋፋዋን ጫማህን ያውቋታል። ጃኬትህን ያውቋታል። ገደድ- ሸፈፍ እያልክ ስትመጣ ከርቀት ይለዩሃል። በጫማህ ባይለዩህ፣ በጃኬትህ ይለዩሃል። ደግሞ ይቀልዱብሃል። ባይቀልዱብህም እንደሚቀልዱብህ ታስባለህ። በአጠገባቸው ስታልፍ ትሸማቀቃለህ። ይህ ነገር ስሜትህን ይጎዳዋል።
“አስበው! አንድ የኢንጂነሪንግ ተማሪ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በኬሚካልም ይሁን በመካኒካል ኢንዱስትሪ እስኪመረቅ ድረስ አንተ መምህሩ ጫማ መቀየር አለመቻልህ...አያምም?
“በአጭሩ ቅድም ‘ኑሯችን ጫማችንን ነው የሚመስለው’ ያልኩህ ለዚያ ነው።”
አንዳንድ የሰቆቃ እና የሰቀቀን ታሪኮች
ይህ ጥናታዊ ዘገባ የዩኒቨርስቲ መምህራን ላይ ያጠነጥናል፤ ከእነርሱም ውስጥ ፒኤችዲ የሚማሩት ላይ ያተኩራል።
መምህራኑ የበለጠ በተማሩ ቁጥር የበለጠ እየተራቡ እንደሆነ ያወሳሉ።
ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲሠሩ ከተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ መምህራን ለቅሷቸው የእናቱን ሞት ያረዱት ሰው ያህል ነው።
“በተመጣጠነ ምግብ እጦት የተነሳ እየቀነጨርን ነው” ብለው ያማርራሉ።
ቢቢሲ በርከት ያሉ የፒኤችዲ ተማሪዎችን ለወራት ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ ቆይቷል።
ከጉዳዩ ስፋት የተነሳ የብዙዎቹ ኑሮ በአምስት መምህራን ታሪክ ውስጥ ጨምቆ ማስቀመጡ የተሻለ መንገድ ሆኖ አግኝቶታል።
‘ዕጩ ዶክተሮቹ’ የሰቆቃ ሕይወታቸው በቤተሰባቸው ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ሐፍረት ለማስቀረት፣ በተማሪዎቻቸውም ላይ አሉታዊ ስሜት ለማስወገድ ማንነታቸው በፊደል ተወክሏል።
“ቀንም ማታም ቀጭን ሽሮ ነው የምበላው”
“ልጆቼንና ባለቤቴን ገጠር ትቻቸው ነው የመጣሁት።አዲስ አበባ ባመጣቸው የት ያድራሉ? ምንስ ይበላሉ?
እኔ ራሴ የማድረው ዶርም ውስጥ ለአራት ተዳብዬ ነው። በስተርጅና እንዲህ እኖራለሁ አላልኩም ነበር። ለዚህ 1500 ብር እከፍላለሁ።
ሦስት ልጆች አሉኝ። በየወሩ ለቤተሰብ 7ሺህ እልክላቸዋለሁ። እጄ ላይ ስንት ቀረ? 1ሺህ ቀረችኝ። አንድ ሰው በ1ሺህ ብር አንድ ወር እንዴት ነፍሱን ያቆያል?
ሌላም ወጪ አለብኝ። የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ። 2ሺህ ብር ነው። ከየት አምጥቼ ልክፈል?
ከዚያም ከዚህም ተበዳድሬ እከፍላለሁ።
የሚያቃዠኝ ልጆቼ ቢታመሙስ የሚለው ነው። እንቅልፌን አጣለሁ። እግዜር ረድቶን እስከዛሬ አልታመሙም።
በቃ በየወሩ ጸሎቴ ልጆቼ እንዳይታመሙ ብቻ ነው። ምን ይውጠኛል? በምኔ አሳክማቸዋለሁ?
አንዳንዴ ችግር ሲጠናብኝ ወንድሜ አለ፤ በወር በወር እንዲደጉመኝ እለምነዋለሁ። አይጨክንብኝም። በወር 4ሺህ ብር አካባቢ ይቆርጥልኛል።
እሱ ባይኖር ምን ይውጠኛል? ይህን ሁሉ ዓመት ተምሬ ራሴን አለመቻሌ ግን የእግር እሳት ይሆንብኛል።
ስለ ልጆቼ ልንገርህ?
የአስተማሪ ልጅ መዝናናት አያውቅም። ልብስ አይቀይርም። ልጆቼ ልብሳቸው ሰውነታቸው ላይ ያልቃል። ባደጉ ቁጥር እደነግጣለሁ። ሱሪው ያጥራቸዋላ። ልብስ መግዛት ሊኖርብኝ ነው። አባት ልጁ ሲያድግ መደንገጥ አለበት? እኔ ግን እደነግጣለሁ። ምንም ማድረግ አልችልም። ከየት አምጥቼ ነው ልብስ የምገዛላቸው?
አስተማሪ ነኝ። ሙስና አልሠራ። እዚህ አገር ሙስና ካልሠራህ መኖር ትችላለህ እንዴ? ተወኝ በናትህ።
ፒኤችዲ በአብዛኛው 4 ዓመት ነው የሚወስደው። በ6 ዓመት ያልጨረሱ አሉ። አእምሯቸው የተነካ አሉ። ‘ያበዱ’ መአት ልጆች አውቃለሁ። እንዴት ትማራለህ በዚህ ጭንቅ? ከአራት ኪሎ - 6ኪሎ ዞር ዞር በል። ብቻውን የሚያወራ ሰው አታጣም። የፒኤችዲ ተማሪ ነው።”
“ጓደኞቼን ካየሁ መንገድ እቀይራለሁ”
“ስለ ጓደኞቼ ልንገርህ?
ድሮ አብረውኝ የተማሩ ጓደኞቼ ብዙዎቹ ባንክ ይሠራሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ናቸው። ይናፍቁኛል - እናፍቃቸዋለሁ። ግን በፍጹም አላገኛቸውም። ከርቀት ካየኋቸው ራሱ መንገድ እቀይራለሁ። ለምን በለኛ?
ልጋብዝህ ሲሉኝ ይሰማኛል። ግብዣውን ብፈልገውም ወደ ኋላ መቅረቴ ያንገበግበኛል።
አሁን አንድ ጓደኛዬ አለ። የውጭ ድርጅት ውስጥ ነው የሚሠራው። 2500 ዶላር ገደማ ያገኛል። ኑሮው ያስቀናኛል።
ከአንዳንዶቹ ጋር መንገድ ካገናኘን፣ ‘ተው እንጂ! አትራቀን፤ እናግዝሃለን’ ይሉኛል። እሸማቀቃለሁ። ‘ምነው አሞህ ነበር እንዴ?’ ይሉኛል። ‘ራስህንማ እንደዚህ አትጣል’ ይሉኛል።
ብዙ ሰው ጀዝቦ ቀርቷል እኮ። እኔ እግዜር ረድቶኝ እጅ አልሰጥ ብዬ እንጂ ብዙ ልጆች እኮ አእምሯቸው ተነክቶ መንገድ ወድቀዋል። ቀልዴን መሰለህ?
ይሄ ይገርምሃል እንዴ? ፍቺ የፈጸሙ አሉ። ትዳራቸው የፈረሰ አውቃለሁ፤ በጭንቅ። ሱስ ውስጥ የወደቁ አሉ።
ያበደ አስተማሪ 2 እና 3 በየዩኒቨርሰቲው አታጣም። ቀልዴን መሰለህ?
እኔ ራሴ አንዳንዴ እያበድኩ ይመስለኛል። ቤተሰቤ ይደውላሉ። ባለቤቴ በጣም ስትቸገር ትደውላለች።
‘እስከመቼ ነው በዚህ ድህነት የምታኖረን? ለምንድን ነው ትምህርቱን ትተህ ሥራ የማትፈልግ?’ ትለኛለች።
እኔም ነገሩን አስቤበት ነበር። ነገር ግን በማስተማር ላይ ነው ዕድሜዬን የፈጀሁት። እንዴት ነው አሁን ድንገት ልምድ ሳይኖረኝ ኤንጂኦ እና ባንክ የሚቀጥረኝ?
ማን አስተማሪን ይቀጥራል ደግሞ? የመረጥነው መንገድ በጣም ጎዳን - ወንድሜ። ከዜሮ መነሳት ይከብዳል።
እንደነገርኩህ ጓደኞቼ አሉ። በጥሩ ጊዜ ኤንጂኦ የገቡ። በትምህርት ብዙም ያልገፉ። ጂፕላስ- 2 ቤት የገነቡ። እኔ በዚህ ዕድሜዬ ፒኤችዲ እየሠራሁ ዶርም ውስጥ ከ4 ሰው ጋር ተዳብዬ እኖራለሁ።
እንዴት አይሰማኝም ታዲያ?”
“የቱ ጋ ነው የተሳሳትኩት?’’
“ልጆቼ እንዳይታመሙ ነው ጸሎቴ አላልኩህም? እንደ ዕድል ሆኖ አይታመሙብኝም። ቢሆንም ግን ልጆች አይደሉ? ብዙ ነገር ያምራቸዋል።
ስለዚህ ቤተሰብ ጋ ስሄድ ከቤት አንወጣም። ከተማ አንወስዳቸውም። ይዘናቸው መውጣት እንፈራለን።
ይሄ ነገር ይሰማኛል። እንደ አባት፣ ‘I let them down’ [ትቻቸዋለሁ] እላለሁ። ገባህ?
የቱ ጋ ነው በሕይወት የተሳሳትኩት? እላለሁ።
ጓደኞቼ ኑሮዬን ያዩና ከንፈር ይመጣሉ።
‘የት የምትደርስ ሰው ነበርክ እኮ። ምን ዋጋ አለው፣ አስተማሪ ሆነህ ቀረህ’ ይሉኛል።
‘መማር የጎዳው ሰው ካለ አንተን ነው’ ይሉኛል።
ልክ ናቸው እኮ። ታምናለህ? በሕይወቴ 1ኛ ያልወጣሁት 9ኛ ክፍል ብቻ ነው። ታዲያ የቱ ጋ ነው የተሳሳትኩት?”
“የሃብታም ልጅ የሚያስጠና ፒኤችዲ”
“የእኔ ጓደኛ አለ። ፊዚክስ አስተማሪ ነው። የግል ትምህርት ቤት እያመለከተ አልተሳካለትም። አሁንም ተደብቆ እያመለከተ ነው፤ ሃይስኩል ለማስተማር።
ቤተሰቡ ጋ ሄዶ አያውቅም። ሁልጊዜ ቆዝሞ ነው የማገኘው።
የምናውቃቸው እጩ ዶክተሮች ደግሞ አሉ። ተደብቀው በአውቶቡስ ተሳፍረው የሃብታም ልጅ አስጠንተው የሚመለሱ። ተወኝ በናትህ። ይሄ ሙያ እኮ ገደለን።”
“በየቀኑ ዳቦ በሻይ ነው የምበላው”
“እዚህ 6 ኪሎ ግቢ ውስጥ በየያንቱ 600 ብር የሚሸጥበት ቤት አለ አሉ። ማመን አቅቶኛል። ከየት አምጥተው ነው የሚበሉት?
እኔ ሳልዋሽ ልንገርህ።
ጠዋት 2 ዳቦ እና አንድ ሻይ እበላለሁ። ቁርስ። 30 ብር ነው። ሁልጊዜ ቁርሴን የምበላው ‘ዋይት ሐውስ’፣ 5ኛ በር ባለች ካፌ ነው።
ምሳ እዚያችው ካፌ ሄጄ ቀጭን ሽሮ እበላለሁ። እራትም ሽሮ እበላለሁ። 50 ብር ነበር የምበላው። አሁን ወደ 70 ገብቶ ግራ ገብቶኛል።
‘ሥጋ አትበላም ወይ ነው ያልከኝ?’ (ሳቅ) ትቀልዳለህ አይደል?
ሥጋ የሚበላ አስተማሪ አለ እንዴ? እኔ አላውቅም። ላጤ ራሱ አይበላም፤ እንኳን እንደኔ ባለትዳር የሆነ። ሽሮ ራሱ እኮ ተሳስተህ ውጭ ከበላህ ደመወዝህ ያልቃል።
ሥጋ አለመብላት ኖርማል ነው። ረስተነዋል ሥጋን። አይናፍቀንም ሁሉ። ልጆቼ ሥጋ ቢበሉልኝ ግን ደስ ይለኝ ነበር።”
“ባለቤቴ ሱሪ ገዛችልኝ”
“ሁሉም ፒኤች ዲ ተማሪ ተደብቆ ተባራሪ ሥራ ለመሥራት ይሞክራል። ሰርቬይ የሚሠራ አለ፤ ሃይስኩል የሚያስተምር አለ፤ ስሙን ቀይሮ ሃብታም የሚያስጠና አለ።
ብዙ ፒኤችዲዎች ግን ዋና የገቢ ምንጭ የተማሪ ‘ፔፐር’ መሥራት ነው።
እኔ አንዱም ተሳክቶልኝ አያውቅም። ለዚያ ይሆናል ችግር የጠናብኝ።
አዲስ ጫማ ለመጨረሻ ጊዜ መርጬ የገዛሁት የዛሬ 10 ዓመት ነው። ዎርልድ ቪዥን አንዲት ሥራ አግኝቼ በ3ሺህ ብር ምን የመሰለ ጫማ ገዛሁ። ደጉ ጊዜ!
ከዚያ ወዲህ አዲስ ጫማ አልገዛሁም። አብዛኞቻችን እንደዚያ ነን። ጫማችን ተንሻፎ ነው ያለው።
አንድ ፒኤችዲ ተማሪ አለ፤ እዚህ የማውቀው። ሁለት ዓመት ሙሉ አንድ ልብስ ለብሶ፣ አንድ ጫማ ተጫምቶ ኖሯል።
እኔ ደህና ነኝ። የዛሬ 3 ዓመት አካባቢ ባለቤቴ ብር አገኘችና መንገድ ላይ ጂንስ ገዝታልኝ መጣች። እግዜር ይስጣት! እስከዛሬ እለብሰዋለሁ።”
“ዕድሜዬን ሙሉ በድህነት ነው የተማርኩት። አፈር በልቼ።
አሁን አንድ ልጅ አለኝ። ሚስት አለችኝ። የማስተምራት እህቴ አለች። ኑሮ አልገፋ አለ። አስተማሪነት እርግማን ሆነ።
ታምነኛለህ? ከእናቴ ጋር ከተያየሁ 7 ዓመት ሆነ። ለምን ብለህ ጠይቀኝ። ምክንያቱም የትራንስፖርት ብር የለኝም። አንድ በል።
ሁለተኛ አፈርኩ። እናቴ ሰፈር ውስጥ የምትባለውን ስለማውቅ አፈርኩ። ‘የዩኒቨርስቲ መምህር ልጅ አላት እኮ’ ይሏታል። ‘ዶክተር ሆኗል እኮ’ ይሏታል።
ከእኔ የሚጠበቀው ሌላ ነው። ኑሮዬ ሌላ ነው። የሚወራው ደግሞ ሌላ ነው። ይሄን በመፍራት ከቤተሰብ ሸሸሁ። ከዘመድ አዝማድ ሸሸሁ።
እሷን ማሸማቀቅ አልፈለኩም። ፍዳዋን በልታ ነው እኮ ያስተማረችኝ።
ዩኒቨርስቲ ስገባ አባቴ አራት በሬ ሽጦ ነው ያስተማረኝ።
ሃይስኩል እያለሁ እናቴ ከሩቅ አገር ስንቅ ተሸክማ ታመጣ ነበር። ጥናቴ እንዳይስተጓጎል ብላ እኮ ነው። እንዳይርበኝ ብላ።
ጎንደር ድረስ - ፋሲለደስ ትምህርት ቤት ድረስ ተሸክማ ምግብ ታመጣ ነበር። 4 ሰዓት በእግሯ ተጉዛ።
በቃ ተምሬ የእናቴን ውለታ እከፍላለሁ ብዬ አስብ ነበር። ከድህነት አወጣታለሁ እል ነበር።
ዛሬም ድረስ ሲከነክነኝ የሚኖረው ተምሬ -ተምሬ- ተምሬ የእናቴን ሕይወት መለወጥ አለመቻሌ ነው።”
“እናቴ ደውላ አለቀሰች”
በቅርቡ እናቴ ደውላ ‘አሁንስ በጣም ከፋኝ’ አለችኝ። ለምን ስላት? ‘እኔ ሳስተምርህ እንዲህ ትሆናለህ አላልኩም። እኔ ብር መቼ ጠየቅኩህ። ቤተሰቦችህን ይዘህ በዓል አብረኸኝ እንድታከብር ነው የምፈልግ’ አለችኝ።
በጣም ተሰማኝ።
አገር ቤት ሰው ብዙ ነገር ይለኛል።
‘ያንተ ትምህርት እንዴት ያለው ጉድ ነው? አያልቅም ወይ? ኑሮህንስ አይቀይረውም ወይ’ ይሉኛል።
‘እገሌን አወቅከው የጋሽ አገሌ ልጅ። 10ኛ ክፍል ጨርሶ ምን የመሰለ ቤት ሠራ እኮ’ ይሉኛል።
‘አንተ ነህ እንጂ የሙጥኝ ያልክ - ሰው በትምህርት ላይ ተስፋ ከቆረጠ ከረመ እኮ’ ይሉኛል። ይሰማኛል።”
“አንሶላችን ከተቀየረ 8 ዓመት ሞላው”
“የሆነ ጊዜ በጣም ችግር ጠናብኝ፣ ቤት ኪራይም መክፈል አቃተኝ። አንድ ትምህርት ቤት ተቀጠርኩ፤ በድብቅ ለማስተማር። ሃይስኩል ነው።
ፒኤችዲ እየተማርክ ሥራ መሥራት አይፈቀድም። ተደብቄ እየሄድኩ ሥራ ጀመርኩ።
ተማሪዎቹ አለባበሴን ያዩና ይስቃሉ። ጫማዬን እያዩ ይስቃሉ። ‘ተዉ እንጂ አትረብሹ - ቀልድ አይደለም እኮ የያዝነው፤ ትምህርት ነው የያዝነው’ አልኳቸው፤ ተንቀዥቅዤ። ዝም ብዬ እንደማስተማር። እኔን ብሎ መካሪ።
‘አቦ ትምህርት - ትምህርት አትበል፤ አንተ ተምረህ የት ደረስክ?’ አለኝ ከመሃላቸው አንድ ልጅ። ሁሉም ጫማዬን እያዩ ሳቁ።
ዶክትሬት እየተማርኩ መሆኑን ቢያውቁ ምን ሊሉ ነው?
እውነቴን ነው የምልህ በሸሚዜ ብቻ የሚያውቀኝ ሰው አለ። ‘በሸሚዝህ ነው የለየንህ’ ይሉኛል። ቀይሪያት አላውቅማ። ረዥም ጊዜ ከተማ ሄጄ አላውቅም።
አዲስ ልብስ ከገዛሁ 5 ዓመት ሆነኝ።
ብዙ ጊዜ ቤት ነው የምቀመጠው። አእምሮዬ ተነካ። ሰው ሸሸሁ። ዜና ራሱ የምሰማው ሦስት እና አራት ቀን ካለፈ በኋላ ነው። ከሰው አልጨመርም።
ከሁሉ የከፋኝን ቀን ልንገርህ።
ባለትዳር ነኝ ብዬኻለሁ። አንሶላዬን ሳየው ሆድ ይብሰኛል። ድሮ ኑሮ ጥሩ በሆነ ዘመን ነው የገዛሁት። ትዝ ሲለኝ 8 ዓመት ሆኖታል - አንሶላችን።”
“ምናለ ጎበዝ ተማሪ ባልነበርኩ” እላለሁ
“ከሰው አልጨመርም። አብዝቼ እተክዛለሁ። ፊደል ያልቆጠረ ብዙ የማውቀው ሰው ቤት ንብረት አለው። የተሻለ ሕይወት ይመራል። እኔ ለምን ተማርኩ እላለሁ - አንዳንዴ። እንደሱ አይባልም - አውቃለሁ። ግን ምን ላድርግ? ወደ አእምሮዬ የሚመጣውን ነው የምነግርህ።
ውስጤ ጠንካራ ሆኖ ነው ከራሴ ያለሁት እንጂ ጭንቅላቴ እኮ ልክ አይደለም።
እንደ ባይተዋር ነው የምኖረው።
አንዳንዴ ለብቻዬ እያወራሁ ራሴን አገኘዋለሁ።
ጓደኛ የለኝ፣ ምን የለኝ። ሰው ሆነህ ከሰው ጋ መጨመር ካልቻልክ ማበድ ማለት አይደለም?
ከወር-ወር ኪሴ ባዶ ነው።ከቤት የማልወጣውም ለዚያ ነው። ታክሲ ውስጥ ሰው ባገኝስ ብዬ እሳቀቃለሁ። ከዚህ ሁሉ ለምን ቤት አልቀመጥም ብዬ ነው ያለሁ።
በቀደም ትዝ ሲለኝ ለባለቤቴ የተጋባን ቀን ከገዛሁላት ስጦታ ውጭ ገዝቼላት አላውቅም።
ባትነግረኝም ሞራሏ መጎዳቱ አይቀርም። ለልጄም እንደዚያው። ከዚህ በላይ ምን የሚያሳዝን ነገር አለ?
እኔ መምህር በመሆኔ እና እነሱ የመምህር ቤተሰብ በመሆናቸወ ተጎድተዋል። ምንም ጥያቄ የለውም። አንዳንዴ ‘ምናለ ድሮ ጎበዝ ተማሪ ባልነበርኩ’ የምለውም ለዚያ ነው።”
“ፒኤችዲ ከተመዘገብክ በኋላ ሁለት ሴሚስተር መደበኛ ኮርስ ትወስዳለህ። ከዚያ ሲኖፕሲስ ዲፌንስ ታቀርባለህ።
ከኮርሱ በኋላ መምህራን ‘ፐብሊኬሽን’ ይጠይቃሉ። ‘አርቲክል ሪቪው’ በጆርናል ማሳተም አለብህ። ማሳተም ያለብህ በሥመ ጥር ጆርናል (Reputable journal) ላይ ነው።
ለዚያ ትከፍላለህ። በሌለኝ ገንዘብ መቶ ዶላር ከፈልኩ።
መጀመሪያ 900 ዶላር ነው የጠየቁኝ።
አገሬ ኢትዮጵያ እንደምትባል። ያለሁበትን አሳዛኝ ሁኔታ ዘርዝሬ፣ የኔ ደመወዝ 100 ዶላር እንደማይሞላ አብራርቼ፣ ስንት እና ስንት የሰቆቃ ደብዳቤ ጽፌላቸው፣ ከስንት የወራት ልመና በኋላ 100 ዶላር ተደረገልኝ።
ፒኤችዲ መምህራን ተባባሪ ፕሮፌሰር (Associate Professors) ናቸው። አሳትም የሚሉህ ላንተ አስበው መለህ? ለራሳቸው ብለው ነው። ተማሪው ጥናታዊ ጽሑፍ ዕውቅ ጆርናል ላይ ባሳተመ ቁጥር የእነሱም ስም ይገባል። ያን ሙሉ ፕሮፌሰር ለመሆን ይፈልጉታል። ስለዚህ ካላሳተምክ ግሬድ አላስገባም ብለው ይደራደሩሃል።
አስበው እንግዲህ ለምግብ የሚተርፍ ገንዘብ የሌለውን መምህር በጆርናል ፍዳውን ሲያበሉት።
ለማንኛውም ወደ ጥያቄህ ልሂድ። ኑሮህን ንገረኝ ነበር ያልከኝ?
ምኑን ልንገርህ? ደመወዜ ያው ተጣርቶ 9900 ብር አካባቢ ነው። 1350 ብር ተጨማሪ አለች። ፒኤችዲ መሥሪያ መሆኗ ነው። (ወደው አይስቁ!) ችግሩ ምን መሰለህ። ለፒኤችዲ ትምህርት ስትሄድ የትምህርት መልቀቂያ (Study leave) ትሞላለህ።
ያ ማለት ከመማር ውጪ ምንም ተጨማሪ ሥራ አልሠራም ብለህ ቃል መግባት ማለት ነው።
በፊት ትንሽ ማስታገሻ የነበረው የትርፍ ሰዓት ሥራ ነው። ለምሳሌ የማታ ወይም የርቀት ክላስ እናስተምርና ገቢ እናገኝ ነበር። ለምሳሌ ‘ኦቨርሎድ’ የሚባል ነገር ነበር። ከ12 ክሬዲት በላይ ካስተማርክ በሴሚስተር ይከፈልሃል። ልክ ፒኤችዲ ስትጀምር ያ ሁሉ ይቆማል። ስለዚህ ከፍ ባልክ ቁጥር ሕይወትህ ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሚሆነው።
እኔ ለምሳሌ ባለትዳር ነኝ። ልጅ አለኝ። ቤተ ተከራይቼ መኖር ግን አልችልም። ትቻቸው ነው የምማረው። ትዳሬም አስተምረው እንደነበረው ትምህርት የርቀት ሆኗል።
ለልጄ ክብር ስል ስሜን አትጥቀሰው። ኑሮዬን ግን ልነግርህ እችላለሁ።
በየቀኑ ሙዝ በዳቦ ነው የምበላው። እኔ ብቻ ሳልሆን ሁላችንም እንደዚያ ነን። ሙዝ በዳቦ እየበላን ነው የምንማረው። እያነቀን።
ቤተሰብ ይዘህ በ3ሺ ብር ታዲያ ሥጋ ልትበላ ያምርሃል? 3ሺህ ብር ነው እኮ የሚተርፈን ለምግብ።
ቤት ኪራይ ሌላው ራስ ምታት ነው። በየጊዜው ኑሮ ሲጨምር የሚቀንስ ቤት ፍለጋ እንንከራተታለን።
ፍራሽ ተሸክመህ ስትሄድ ያስተማርከው ተማሪ ያይሃል። በቃ ይሰማሃል።
መንግሥት ምናለ የሳር ቤት እንኳ ሠርቶ ቢሰጠን። የጭቃ ቤት ቢሰራልን ምን አለ? Is this too much to ask? [ይህ ይከብዳል?] የዩኒቨርሰቲ መምህር ሆነህ ባልዲ ይዘህ-ፍራሽ ተሸክመህ ስትንከላወስ አያሳዝንም?
ደግሞ አከራዮች መምህር መሆናችንን ሲያውቁ ቅድሚያ ብር ይጠይቁሃል። ላይኖረው ይችላል ብለው ስለሚፈሩ ነው። መምህር የማያከራዩ ሁሉ አሉ።
እኔ እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ወደፊት መምህር የሚሆን ሰው በዚች አገር የሚኖርም አይመስለኝም።”
“አእምሮዬ ልክ አይደለም”
“የፒኤችዲ ትምህርቱ ያን ያህል ከባድ አይደለም። ግን ቀልባችን ተበተነ። በትምህርቴ ላይ ማተኮር ተቸገርኩ። በዚህ የተነሳ መቀጠል አልቻልኩም።
አሁን ከራሴ ጋ አወራለሁ። ኮምፒውተር ከፍቼ ስንት ሰዓት ሙሉ አፈጣለሁ። ሥራዬን ለመሥራት ግን እቸገራለሁ።
‘የማኅበረሰቡን ችግር በጥናት ልቀርፍ ቀርቶ እኔ ራሱ መቼ ችጋሬን ቀረፍኩ?’ እያልኩ እብሰለሰላለሁ።
አገሬ ደመወዝ ትከፍለኛለች። አመሰግናለሁ። የምትከፍለኝ ግን ከአቅሟ በላይ ይሁን ከአቅሟ በታች አላውቅም። የሚመለከታቸው ያወቃሉ። እኔ የማውቀው ግን ለመኖር መቸገሬን ነው።
አንድም ቀን ቅንጦት አልጠየቅኩም። ትንሹን ኑሮ መኖር የሚያስችለንን ነገር ስጡን ነው የምለው።
ልንገርህ - እኔ በልጅነቴ ፓይለት ወይም ዶክተር ልሁን ብዬ አላልኩም። ከልጅነቴ ጀምሮ መምህር መሆን ነበር ህልሜ። ከተመረቅኩ በኋላ አዋሽ ባንክ ሥራ አግንቼ ነበር። አልፈልግም ሕልሜ መምህር መሆን ነው ብዬ ነው የተውኩት።
ከዚያ ወዲህ ከቤተሰብ ጋር ግጭት ውስጥ ገባሁ።
እነሱ ‘ትምህርት-ትምህርት አትበል፤ ውጣና ባንክ ግባ’ ይሉኛል። እኔ ደግሞ አሁንማ በቃ ረፈደ እላለሁ።
ሰሞኑን ጓደኞቼ አንድ ነገር በስልኬ ላኩልኝ። ከፈትኩት። በፌስቡክ የሚሽከረከር ቪዲዮ ነው።
አንድ መምህር ግብዣ ቤት ሄዶ ሰሀኑ ላይ ያለውን ቆሎ ከበላው በኋላ የቀረውን ኪሱ ላይ ሲሸጉጥ ያሳያል።
ተሸማቀቅኩ። ጓደኞቼ የላኩልኝ የገዛ ኑሮዬን ነው።
ክርስቶስ እኮ መምህር ነበር። መሪዎቻችን በሙሉ አንድ መምህር አስተምሯቸዋል እኮ። ‘ለምን በኛ መጨከን ተፈለገ ግን?’ እላለሁ።”
“የድሃ ድሃ ነን”
“የድሃ ድሃ አይደላችሁም ይሉናል። ነን። እደግመዋለሁ የድሃ ድሃ ነን። ለመምህር የድሃ ድሃ የሚል ቃል ያንሰዋል። ብዙ ሰው ደመወዝ ስለምናገኝ የድሃ ድሃ አንመስለውም።በዲግሪ ላይ ዲግሪ ስለጫንን የድሃ ድሃ አንመስለውም።
የድሃ ድሃ ነን። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፒኤችዲ ተማሪ ሆነው የማይሆን ሥራ የሚሠሩ መምህራን አሉ ብለውኛል ጓደኞቼ። በጋራ ፍራሽ ዘርግተው ለብዙ ሆነው አንዲት ክፍል ቤት የሚኖሩ የዩኒቨርስቲ መምህራን አውቃለሁ።
በተለይ ቤተሰብ ያለን መምህራን በጣም ተጎዳን።
እኔ አሁን አሁን በመረጥኩት የሕይወት መስመር እጸጸታለሁ። በልጅነቴ መምህር ለመሆን የተመኘሁት ራሱ ስህተት ነበር ወይ እላለሁ።
በጣም የማደንቃቸው መምህራን ስለነበሩ ነው የተሳሳትኩት። እነሱ ናቸው ያሳሳቱኝ። እወዳቸው ስለነበረ ነው የተሳሳትኩት።
ከእነርሱ ሕይወት መማር ነበረብኝ።
ልንገርህ!
ድሮ እኔን ያስተማሩኝ መምህራን እኮ ከእኔ እኩል ወይም ያነሰ ነው የሚያገኙት።
ምን ያህል ሞራል ይኖራቸዋል? መንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤት እንደዚያ አይደለም። በየጊዜው ዕድገት አለ።
እንዴት ከ20 ዓመት በፊት ያስተማረኝ መምህር ጋር እኩል ደመወዝ አገኛለሁ?
እኔን ያስተማረኝ ዶክተር እኮ አሁን ስመረቅ ከእሱ እኩል ደመወዝ ላገኝ ነው። ይሄ ልክ አይደለም።
ድሮ 2008 ላይ ያስተማረኝ ሰውዬ አሁን እኩል ነው ደሞዛችን። ወላጅ እና ልጅ እንዴት እኩል ይሆናል? የቀለም አባቶቼ ጋ ደመወዜ እኩል መሆን አለበት? እንደው ስታስበው - ስሜትስ ይሰጣል?
እስኪ መንግሥት የሚሰማ ከሆነ ንገሩልን። በጣም ተቸገርናል። የምሬን ነው።
ቅድም ‘ሥጋ በምን ያህል ጊዜ ትበላለህ ነው ያልከኝ?’
ተው እንጂ። የትኛው መምህር ሥጋ ሲበላ አየህ?
እኔ ስሜን ካልጻፍከው ምን እንደምበላ ልነገርህ እችላለሁ። ጠዋት ክላስ ከመግባታችን በፊት ሙዝ በዳቦ እንበላለን።
ከክላስ ስንወጣ በድጋሚ ሙዝ ይዘን ወደቤት እንሄዳለን።
ምሳ ላይ ደረቅ እንጀራ 25 ብር ገዝተን በሽሮ እንበላለን።
ጥናት ላይ ቆይተን ማታ ሲደክመን ቀን ይዘነው የመጣነውን ሙዝ በዳቦ እንበላለን።
ሙዝ እና ዳቦ ይዘን በልተን በውሃ አወራርደነው እንተኛለን። እዚህ በጋራ በአንድ ክፍል ቤት የምንኖረው ሁላችንም የፒኤችዲ ተማሪዎቸ ነን። ዶርማችን የሙዝ ልጣጭ ነው የሞላው።
ሥጋ ትበላለህ ነው ያልከኝ? ሥጋ የሚበላ መምህር አለ እንዴ?
የማልዋሽህ በዚህ ዓመት [2016 መጨረሻ ነው ያነጋገርነው] ከ2 ጊዜ በላይ ሥጋ አልበላሁም። ሁለቱንም ጊዜ ሰው ጋብዞኝ ነው።”
“ማኅበራዊ ተሳትፎዬ ላይ ታቅቤያለሁ።
ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የቅርብ ወዳጄ ‘ሚዜ ሁነኝ’ አለኝ። ደነገጥኩ። ለጥናት ከከተማ እወጣለሁ ብዬ ስልክ አጥፍቼ ጠፋሁ።
ሰው ብዙም አላገኝም። ግን ለምሳሌ ጓደኞቼን ባጋጣሚ ባገኛቸውም ቶሎ ብዬ ከምሳ በፊት እለያቸዋለሁ። ‘ምሳ እንብላ’ ቢሉኝስ።
ሁልጊዜ ጅማ ዩኒቨርሰቲ ዋናው ግቢ ላውንጅ ነው የምንባለው። በፍጹም ውጭ አልበላም። የምበላውም በዘዴ ነው።
ለምሳሌ አሁን ቁርስ ላይ ፉል የሚባል ምግብ አለ። ባቄላ ነው። 35 ብር ነው። ጥሩ ነው ሆድ ያዝ ያደርጋል።
ወተት በዳቦ 35 ብር አለ። እሱን አዘወትራለሁ።
የትርፍ ሰዓት ሥራ ለመሥራት እሯሯጣለሁ። ለምሳሌ ተደብቄ ማስተማር።
ሁልጊዜ ለምን ወደዚህ ሥራ ገባሁ እያልኩ እጸጸታለሁ። ቤተሰቦቼ የሚስቴ ዘመዶች ሃብታም ስለምመስላቸው ገንዘብ ቸገረን ይሉኛል። ‘ትምህር ላይ ነኝ፤ ለኔም አይበቃኝም፤ ይቅርታ’ እላቸዋለሁ።
ለቤት ኪራይ 2ሺህ ብር እከፍላለሁ። አንድ ክፍል ውስጥ ነው ፍራሽ ዘርግቼ ጥቅልል ብዬ የምተኛው።
አግብቼ ነገር ግን የላጤ ኑሮ ነው የምኖረው። ምክንያቱም ቤተሰቤን ገጠር ትቻቸው ነው የመጣሁት። እዚህ ካመጣኋቸው ብሩ አይበቃም።
የልጄ ነገር ሁሌ ይጨንቀኛል።
ልጅህ አድጎ መምህር እንዲሆን ትፈልጋለህ? ወይ ብትለኝ - በፍጹም! ነው የምልህ። በእኔ ይበቃል።
እኔ አሁን እየተፍጨረጨርኩ ነው። ፒኤችዲዩን ለመጨረስ። ግን ደግሞ ይሄን ሁሉ የምለፋው 2ሺህ ብር ለመጨመር እንደሆነ ሳስብ ተስፋ እቆርጣለሁ።”
“እኔ ዕድለኛ ነኝ። ቤተሰቦቼ ያግዙኛል። ብዙም አይቸግረኝም። ጥሩ ነው ያለሁት። ግን ልንገርህ የጓደኞቼን።
ትዳራቸው የፈረሰ አውቃለሁ። ግራ ገብቶት ባጃጅ የሚሠራ ልጅ አውቃለሁ። ክፍለ አገር ነው ያለው። ጥሎ ሄደ በቃ። ከዚህ ትምህርት ባጃጅ ብነዳ ይሻለኛል ብሎ ጠፋ።
መቀለ ደግሞ ባጃጅ ኮንትራት የሚሠራ መምህር ነበረ። አሁንም ያለ ይመስለኛል።
የተማሪ የማስተርስ ወረቀት እየሠሩ ኑሯቸውን የሚደጉሙ አውቃለሁ። ከክላስ መልስ መሸት ሲል ሮጥ ብሎ ሰልቫጅ እየሸጠ ፒኤችዲ የሚማር ልጅ አውቃለሁ።
በሊቢያ ወደ ስደት የወጡ እና በረሃ የቀሩ አውቃለሁ። የሚያስጠኑማ መአት ናቸው።
የሃብታም ልጅ ማስጠናት ዕድል ነው። የት ተገኝቶ። በሰው ሰው ካገኘህ ነው።
የሚያሳዝንህ ምን መሰለህ? ነገ ተስፋ ቢታይህ እና ብትማር እኮ ጥሩ። ለመለወጥ መሰቃየት አንድ ነገር ነው። ይሄን ሁሉ ተሰቃይተህ ደመወዝህ ፈቀቅ አትልም።
በአዲስ ማዕረግ እና በአዲስ ስም ድህነትን እንደ አዲስ ትጀምራለህ።”
ብሔራዊ ፈተና ለመፈተን ያለው ፈተና
ከጥቂት ወራት በፊት በዩኒቨርስቲ የሚገኙ መምህራን የ2ኛ ደረጃ ብሔራዊ ፈተና ለመፈተን እንዲዘጋጁ ተነገራቸው።
“ትንቅንቁ ተጀመረ” ይላል በዚህ ሂደት ያለፈ አንድ የዩኒቨርስቲ መምህር።
“ፈታኝ ከሆንክ አበል ትበላለህ። በዓመት አንዴ የሚመጣ ዕድል ስለሆነ ሎቶሪ እንደደረሰን ነው የምንቆጥረው”
በዚህ ትንቅንቅ ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰሮች፣ ዶክተሮች፣ ሌክቸረሮች ይገኙበታል። የፒኤችዲ ተማሪዎችም በልመና ሰርገው የሚገቡበት አጋጣሚ አለ።
ትንቅንቁ ለሳምንታት ይቀጥላል።
ነገሩን ለማርገብ ኃላፊዎች ማስጠንቀቂያ መስጠት ጀመሩ። ፈታኞች ለደኅንነት አስጊ የሆኑ ቦታዎች ጭምር ሊመደቡ እንደሚችሉ ማስፈራሪያ ሰጡ።
ይህ ማስፈራሪያ ግን በተለይ ‘ዕጩ ፒኤችዲዎችን’ ሊመልሳቸው አልቻለም።
በመጨረሻ ዕድለኞች ተመረጡ።
ከአክሱም ዩኒቨርስቲ ለዚህ ፈተና የተመደበ መምህር ለቢቢሲ ሲናገር ለደኅንነት አስፈሪ የሆኑ፣ ለምሳሌ ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው ደምቢዶሎ እና ነቀምት አካባቢዎች፣ የፋኖ ኃይሎች በሚገኙባቸው የደባርቅ ገጠራማ አካባቢዎች በወታደራዊ ኮንቮይ ታጅበን ሄድን” ይላል።
አንዲት የደረሰች ነፍሰጡር መምህርትም አብራቸው እንደነበረች ይኸው መምህር ያስታውሳል።
“ይሄ ሁሉ ተጋድሎ. . . የአበል እና ኑሮን ለመደገፍ ነው። ከሞትንም እንሙት ብለን የገባንበት ነው።”
ቢቢሲ፦ ለመሆኑ አበሉ ምን ያህል ቢኾን ነው?
መምህሩ፡ በቀን 400 ብር ነው። ፈተናውን ስትፈትን ደግሞ 550 ብር ይጨመራል። ከ550 ብሩ ውስጥ ግን ግብር ይቀነስና 357 ብር ከ50 ሳንቲም ይደርሰናል።
“ጥብሱ መረቅ ይብዛበት”
ቢቢሲ ያነጋገረው በዚህ ፈተና የተሳተፈ ሌላ መምህር ብሔራዊ ፈተና ለመፈተን መመረጥ ትልቅ ዕድል እንደሆነ ይመሰክራል።
“እውነት እልሃለው ከስንት ጊዜ በኋላ ጥብስ የበላንበት መልካም አጋጣሚ ነበር የተፈጠረልን” ሲልም ወቅቱን ያስታውሳል።
“የጥብስ ዋጋ ውድ ነው። ደግነቱ ገጠር ምግብ ቤቶች ደግሞ ጥብሱ በርከት ይላል። 5 ሆነን 3 ጥብስ እናዛለን። ነገር ግን ምግብ ስናዝ አንድ ማሳሰቢያ እንሰጣለን፤ “መረቅ ይብዛበት!” እንላለን።
በዩኒቨርስቲ መምህራን ዘንድ ከኑሮ ውድነት ጋር ተይይዞ አዲስ የምግብ አስተዛዘዝ እንደመጣ የሚናገረው ይህ መምህር፣ ስሙም ‘Minus-1’ እንደሚባል ይናገራል።
ይህም ማለት ከተመጋቢው በአንድ ቁጥር ያነሰ የምግብ ብዛት የማዘዝ ጥበብ ነው።
ይህ ግን ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ ወደ ‘minus 2’ እንደወረደ ያብራራል። ለ5 ተመጋቢ 3 ምግብ እንደማለት ነው።
“ይሄም ታዲያ በስንት ጊዜ ሬስቶራንት ሄደን የመመገብ ዕድል ከገጠመን የምናደርገው ነው እንጂ . . . ማን አቅምሶን።”
ቢሮ ውስጥ የሚያድሩ መምህራን
ከዚህ ቀደም ቢቢሲ በመቀለ ዩኒቨርስቲ አንዳንድ መምህራን የተማሪ ዶርም ውስጥ ማደር መጀመራቸውን መዘገቡ ይታወሳል።
ለዚህ ጽሑፍ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሌሎች የዩኒቨርስዎች መምህራን እንደሚናገሩት ቤት ኪራይ የፈተናቸው፣ ብስጭት ወደ ሱስ የመራቸው አንዳንድ መምህራን ቢሮ ውስጥ ተደብቀው ለማደር ተገደዋል።
ትልቅ ቤተሰብ ያላቸው መምህራን ደግሞ በቤት ኪራይ ውድነት የተነሳ ቤተሰባቸውን ወደ መበተን ሄደዋል። ከልጆቻቸው ጋር ለመኖር የተቸገሩ መምህራን ቤተሰባቸውን ገጠር ውስጥ ወደሚገኙ ራቅ ወዳሉ የትውልድ አካባቢያቸው መላክም በጣም የተለመደ ነገር ሆኗል።
“የኑሮ ውድነቱ ከባለትዳርነት ወደ ላጤ ሊግ አውርዶናል” ይላሉ።
ማስታወሻ፡ ይህ ጽሑፍ የተሰናዳው የደመወዝ ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት ነው።