በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጋዛ-ግብፅ የድንበር ማቋረጫ በኩል ለመውጣት እየተጠባበቁ ነው

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ራፋህ በተሰኘው የጋዛ-ግብፅ የድንበር ማቋረጫ በኩል ለመውጣት በተስፋ እየተጠባበቁ ነው።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የምታደርገው የእግረኛ ጦር ጥቃት ከመጀመሩ በፊት ድንበሩ እንዲከፈት የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድንበር ማቋረጫውን እንደገና ለመክፈት የተደረጉ ድርድሮች ፍሬ አለማፍራታቸውን ገልጿል።

ግብፅ እስራኤል “እየተባባረች አይደለም" ስትል ወቅሳለች።

እስራኤል ሐማስ ለፈጸመው ጥቃት ምላሽ ነው በሚል ጋዛ ሰርጥን በሙሉ ከበባ ውስጥ ያስገባቻት ሲሆን፣ ከጋዛ የሚያስወጡ መስመሮችም እንዲዘጉ ተደርገዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እስራኤል ገብተዋል።

በቀጣናው ከሚገኙ ስድስት የአረብ አገራት መሪዎች ጋር የተወያዩት አንቶኒ ብሊንከን፣ የድንበር ማቋረጫው እንደገና ተከፍቶ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ እና የውጭ ፓስፖርት የያዙ ዜጎች እንዲወጡ ለማድረግ ወደ እስራኤል ተመልሰዋል።

ከአንቶኒ ብሊንከን በተጨማሪ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄምስ ክሌቨርሊ ከእስራኤል፣ ከግብፅ እና በቀጣናው ካሉ ተሰሚ የፖለቲካ አመራሮች ጋር በመተባበር የድንበር ማቋረጫውን ለማስከፈት እየጣሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስራኤል ጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ከበባ እንዲደረግ ያዘዘች ሲሆን፣ በጋዛ 'ኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ነዳጅ አይኖርም ሲሉም የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ባለፈው ሳምንት ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።

ጋዛ ሰርጥ ወደ 2.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጥኤማውያን መኖሪያ ስትሆን፣ ለ16 ዓመታት ያህል የቆየ ከበባ ውስጥ ትገኛለች።

ከዘጠኝ ቀናት በፊት ሐማስ በወሰደው ያልተጠበቀ ወታደራዊ እርምጃ ምክንያት 1ሺህ 400 ሰዎች ተገድለዋል።

የሐማስ ታጣቂዎች በጋዛ ሰርጥ በኩል ድንበር ተሻግረው ነበር በንጹሐን እና በወታደሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙት።

እስራኤል ላለፉት ዘጠኝ ቀናት ቀን ተሌት ጋዛን በቦምብ በመደብደብ ላይ ትገኛለች። ምናልባትም በቀጣይ ቀናት እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዝ ልታስገባ ትችላለች ተብሎ ይጠበቃል።

ሰኞ ዕለት ለሰዓታት በሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት የራፋህ የድንበር ማቋረጫ ይከፈታል መባሉንም ተከትሎ፣ በርካቶች ወደ ድንበሩ ጎርፈው ነበር።

እስራኤልም ሆነች ሐማስ ምንም ዓይነት የተኩስ አቁም ስምምነት አልተደረገም ሲሉም በፍጥነት ውድቅ አድርገውታል።

ሰኞ ዕለት በጋዛ በኩል የሚገኘው የድንበር ማቋረጫ በእስራኤል አየር ጥቃት እንደፈተጸመበት እና ሕንጻም እንደተመታ በደቡብ ጋዛ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ አረጋግጧል።