የቻይና እና የምዕራባውያን ፍጥጫ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቻይና፤ አውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን ያጣመረው “አውኩስ” የተሰኘው ስምምነት ባለፈው ሳምንት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ቁጣዋን ገልጻለች።
ይህ መጋቢት 04/2015 ዓ.ም. አሜሪካ ሳንዲያጎ የተፈረመው አውኩስ ትብብር ቻይና በሕንድ -ፓስፊክ ውቅያኖሶች ቀጠና ታደርገዋለች የተባለውን ወታደራዊ መስፋፋት ለመግታት ያለመ የመከላከያ እና ደኅንነት ስምምነት ነው።
“አደገኛ ጎዳናን የተከለ”፣ “የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ስጋትን ችላ ያለ” እንዲሁም “አዲስ የጦር መሳሪያ እሽቅድድም እና የኑክሌር መስፋፋትን ያለመ” ስትል ነው ቻይና የምዕራባውያኑን ሦስትዮሽ የመከላከያ እና የደኅንነት ትብብርን የገለጸችው።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ናንሲ ፔሎሲ አወዛጋቢ የሆነውን የታይዋን ጉብኝታቸውን ባለፈው ዓመት ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ቻይና ምዕራባውያን ይፈጽሙታል ያለችውን ትንኮሳ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውማለች።
ቻይና በዓለማችን በሕዝብ ቁጥር ቁንጮ ናት። በሕዝቧ ብቻ ሳይሆን በምድር እና በባሕር ኃይልም የቀዳሚነት ስፍራ ያላት ሲሆን፣ በምዕራብ ፓስፊክ ውቅያኖስ በኩልም አሜሪካ እና ምዕራባውያን አጋሮች መፈናፈኛ እንዳይኖረኝ እየሞከሩ ነው ትላለች።
ለዚህም ምላሽ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አገራቸው በቅርቡ የመከላከያ በጀቷን እንደምትጨምር እና ብሔራዊ ደኅንነቷን በመጪዎቹ ዓመታት ቀዳሚ ጉዳይ አድርጋ የምትይዘው እንደሆነ አስታውቀዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የሚመጡት አስርት ዓመታት አደገኛ እንደሆኑ እና ዓለምን እየፈተኗት ያሉትን እየጨመሩ የመጡ የደኅንነት ተግዳሮቶች ለመወጣት መዘጋጀት አስፈላጊ ነው ሲሉ አጽንኦት በመስጠት በዚህ ሳምንት ተናግረዋል።
በምዕራባውያኑ እና በቻይና መካከል እየተሰማ ያለው የቃላት ልውውጥ ጦርነት እና ፍጥጫ ወደ ግጭት ያመራ ይሆን? የሚል ስጋትን መፍጠሩ አልቀረም።
በዚህም የተነሳ ዓለም፣ ቻይና በአንድ ጎራ በሌላው በኩል ደግሞ አሜሪካ እና ምዕራባውያን አጋሮቿ የተሰለፉበት አስከፊ ጦርነት ያጋጥማት ይሆን? እዚህ የከረረ ሁኔታ ላይስ እንዴት ተደረሰ?
ምዕራባውያን በቻይና ላይ የተሳሳተ መንገድን ተከትለዋል። ቻይና ምጣኔ ሃብቷ ላይ የተከተለችው ነጻ የማድረግ (የሊበራላይዜሽን) ፖሊሲ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩንም እንዲከፈት መንገድ ይከፍታል የሚል የምዕራባውያኑ ግምገማ ነበር።
የምዕራቡ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ በመግባት ከቻይና ኩባንያዎች ጋር ጥምረት ፈጠሩ። በዚህም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቻይና ዜጎች የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ጀመረ።
ይህንንም ተከትሎ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ (ሲ.ሲ.ፒ.) በሕዝቡ ላይ ያለውን ቁጥጥር ያላላል፣ አንዳንድ መጠነኛ ዲሞክራሲያዊ መሻሻሎችን ይፈቅዳል እንዲሁም “በሕጎች ላይ የተመሠረተ የዓለም አቀፍ ሥርዓት አባል” ይሆናል የሚልም ነበር የምዕራባውያኑ እሳቤ።
ነገር ግን ምዕራባውያን ባሰቡት እና ባቀዱት መንገድ ነገሮች ሊሄዱ አልቻሉም።
እውነት ነው! ቻይና ወሳኝ እና ግዙፍ የሚባል ምጣኔ ሃብት ባለቤት ናት። በዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥም ዋነኛ ምንጭ እና ለበርካታ አገራትም የንግድ አጋር ሆናለች።
ሆኖም ቻይና ይህ የምጣኔ ሃብቷ መመንደግ ወደ ዲሞክራሲ እና ነጻነት ሽግግር አላደረገም በማለት ምዕራባውያን መንግሥታት ይተቿታል።
ቻይና እና ምዕራባውያንን የሚያጋጩባቸው ጉዳዮች በዛ ያሉ ቢሆኑም፣ እስቲ የተወሰኑትን እንጥቀስ
- ታይዋን፦ ቻይና ራሷን የምታስዳድረውን ደሴት ካስፈለገም በኃይል እንደምትጠቀልላት ደጋግማ ዝታለች። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ምንም እንኳን የአሜሪካ ፖሊሲ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስድ ባያበረታታም አገራቸው ታይዋንን ለመከላከል ድጋፏን ትሰጣለች ብለዋል።
- የደቡብ ቻይና ባሕር፡- ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግዙፍ የባሕር ኃይሏን ተጠቅማ የደቡብ ቻይና ባሕርን በከፊል ወደ ግዛቷ ጠቅልላች። ምዕራባውያኑ ይህንን ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚቃረን እንዲሁም ቅኝ ግዛት ሲሉ ጠርተውታል።
- ቴክኖሎጂ፡- ቻይና ከፍተኛ መጠን ያለው ግላዊ መረጃን በድብቅ በመሰብሰብ እንዲሁም የአዕምሯዊ ንብረት መብትን በመጣስ እና በመስረቅ የንግድ ጥቅም ለማግኘት እየሞከረች ነው በሚል ክስ እየተሰነዘረባት ይገኛል።
- ሆንግ ኮንግ፡- ቻይና በቀድሞዋ የብሪታንያ ቅኝ ግዛት፣ ሆንግ ኮንግ ፀረ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የመብት ተሟጋቾች ላይ ረጅም የእስር ቅጣት በይናለች ይሏታል።
- የቻይና ሙስሊሞች፦ የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ቡድን ይፋ ባደረገው ልዩ ጥንቅር ቻይና እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሙስሊም ዜጎቿን የምታጉርበት የበረሃ ካምፕ መኖሩን አጋልጧል።
በወታደራዊ ኃይል ቻይና ኃያል አገር ናት፤ በዚህ በኩል ቻይናን መገዳደርም ፈታኝ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሕዝባዊ ነጻነት ሠራዊቷ ቁጥር ከማሻቀብ በተጨማሪ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራም ረገድ ትልቅ እመርታን አሳይቷል።
የቻይና ዶንግ ፌንግ ሃይፐርሶኒክ የተሰኙት ሚሳኤሎች ከድምጽ በአምስት እጥፍ በሚበልጥ ፍጥነት የሚወነጨፉ ሲሆን፤ ከባድ ፈንጂዎችን ወይም የኑክሌር የጦር መሳሪያ የታጠቁ ናቸው።
ሆኖም የአሜሪካ የባሕር ኃይል በጃፓን ዩኮሳካ የሚገኝ ሲሆን፣ የቻይናንም ግዙፍ ሚሳኤሎች በቅርብ ርቀት ይከታተላል።
ቻይና የኑክሌር ባሊስቲክ ሚሳኤሎችም ላይ ፈጣን የማስፋፋፊያ መርሃ ግብርም ጀምራለች። ቁጥሩንም በሦስት እጥፍ ለማሳደግ አቅዳለች።
ሆኖም ይህ ማለት ቻይና ወደ ጦርነት መግባት ትፈልጋለች ማለት አይደለም። ጦርነት አትፈልግም። ታይዋንን በተመለከተ የምታራምደው ፖሊሲ ምንም ዓይነት ጥይት ሳትተኩስ በቻይና ጫና ስር እንድትሆን ነው የምታሰላው።
ሆንግ ኮንግ፣ ሙስሊም ዜጎቿን እና በአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ዙሪያ የሚነሳባት ትችት እየደበዘዘ እንደሚሄድም ታውቃለች፤ ምክንያቱም ከቻይና ጋር የሚደረገው የንግድ ልውውጥ ለቀሪው ዓለም በጣም ቁልፍ ስለሆነ ነው።
በአሁኑ ወቅት በቻይና እና በምዕራቡ ዓለም ያለው ውጥረት ከፍተኛ ቢሆንም፣ ከአደገኛ ትርክቶች ጀርባ በፓስፊክ ውቅያኖስ ሊቀሰቀስ የሚችል ጦርነት አደገኛ መሆኑን ሁለቱም ወገኖች ይረዱታል።












