በአፋር የተገኘው አዲስ ቅሪተ አካል ስለ ሰው ልጅ አመጣጥ ምን ይነግረናል?

ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን ዓመታት በፊት ያለው የጊዜ ልዩነት በሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ውስጥ ወሳኝ ወቅት እንደሆነ ይታመናል።

የሰው ልጅ እና ቅድመ የሰው ልጅ ዝርያዎች በቅሪተ አካል መዝገብ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መታየት የጀመሩት በዚህ ወቅት እንደሆነ ሳይንቲስቶች ይገልጻሉ።

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በ'ኔቸር' የምርምር መጽሔት ላይ የታተመ ግኝት በዚህ ወቅት ሆሞ እና ፓራትሮፖስ የተባሉት ዝርያዎች በቅሪተ አካል መዝገብ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መታየታቸው እና የእነዚህ የዘር ግንዶች ቅድመ አያት አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ የጠፋበት መሆኑ ሰፍሯል።

በኢትዮጵያ የቅርስ ባለሥልጣን ፓሊዮኮሎጂስት የሆኑት ዶ/ር ሰሚነው አስራት ይህ ጊዜ በጣም ወሳኝ ወቅት የሆነው "ብዙውን ጊዜ ከሰው ልጅ ቅሪተ አካል ውጪ ሌሎች የሰው ልጅን ባህሪ የሚያሳዩ ቁሶች ወይም የድንጋይ መሳሪያ መጠቀም የጀመረበት ስለሆነ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሰሚነው ይህን ሲያብራሩ "ሰዎች በዚህ ወቅት የማሰብ ክህሎታቸው እያደገ ሲመጣ የተለያየ የድንጋይ መሳሪያ መጠቀም ጀምረዋል፤ ስለዚህ ተመራማሪዎች ከቅሪተ አካላቸው አጠገብ የተለያየ የድንጋይ መሳሪያ አብረው ያገኛሉ" ይላሉ።

በተጨማሪም "የድንጋይ መሳሪያዎች ስለባህሪያቸው፣ ከባቢያቸው ላይ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ወይም ደግሞ በቴክኖሎጂ ምን ያህል [ወደፊት] እንደተራመዱ፣ አስተሳሰባቸው ምን ያህል የዳበረ እንደነበር ለማወቅ ይረዳል" ሲሉ ያብራራሉ።

ባለፈው ሳመንት በ'ኔቸር' መጽሔት የታተመው ሳይንሳዊ መጣጥፍ የሰው ልጅን ዝግመተ ለውጥ የምናይበት መነፅር ላይ አዲስ ዕይታን የሚጨምር ነው።

ሳይንቲስቶቹ በዚህ ጽሑፋቸው ላይ በምሥራቅ አፍሪካ ከሰው ልጅ እና ከቅድመ የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ጋር በተያያዘ ዝርያዎቹን ወደ እነዚህ ክስተቶች እንዲያመሩ ስላደረጓቸው ተለዋዋጭ ሁኔታዎች መላምቶችን ለመፈተሽ የሚደረጉት ሙከራዎች የተገደቡ መሆናቸውን አስፍረዋል።

ነገር ግን ሳይንቲስቶቹ ከለዲ ገራሩ የምርምር ፕሮጀክት አካባቢ ባገኟቸው አዳዲስ የቅድመ ሰው ቅሪተ አካላት ዕድሜ፣ ሥነ ምድራዊ (ጂኦሎጂካል) አውድ እና የጥርስ ህዋሳት ላይ ትንታኔ ሠርተዋል።

ትንታኔያቸው በአፋር ክልል በሚገኘው እና ለፕሮጀክቱ መጠሪያ በሆነው ለዲ ገራሩ አካባቢ በተገኙ የቅድመ ሰው ቅሪተ አካላት ግኝት ላይ የተመሠረተ ነው።

ተመራማሪዎቹ ባገኟቸው የጥርስ ቅሪተ አካላት መሠረት ሆሞ ከ2.78 እና 2.59 ሚሊዮን ዓመታት በፊት እና አውስትራሎፒቴከስ ከ2.63 ሚሊዮን ዓመታት በፊት እንደነበረ ያሳያሉ።

'ኔቸር' ላይ የታተመው ጥናት ምንም እንኳን የአውስትራሎፒቲከስ ናሙናዎች እስከ ዝርያቸው ተለይተው ሊታወቁ ባይችሉም፣ ቅርጸ ምስላቸው (morphology) ከአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ እና አውስትራሎፒቲከስ ጋርሂ ይለያል።

እነዚህ ናሙናዎች እንደሚጠቁሙት አውስትራሎፒቲከስ እና ቀደምት ሆሞ በአፋር ክልል ከ2.5 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ሁለት የተለያዩ የዘር ሐረጋት እንደነበሩ እና የሆሚኒን ቅሪተ አካል መዝገብ ቀደም ሲል ከሚታወቀው በላይ የተለያየ ነው።

በግኝቱ መሠረት በምሥራቅ አፍሪካ ከ3.0 እና 2.5 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በነበሩት መካከል እስከ አራት የሚደርሱ ሆሚኒን ዘሮች ይኖሩ ነበር።

እነሱም ቀደምት ሆሞ፣ ፓራትሮፖስ፣ አውስትራሎፒቲከስ ጋርሂ እና አዲስ የተገኘው ለዲ ገራሩ አውስትራሎፒቲከስ ናቸው።

ተመራማሪዎቹ በአፋር ክልል ለዲ ገራሩ በተባለ ቦታ ለዓመታት ካካሄዱት ቁፋሮ በኋላ ከዚህ በፊት የማይታወቅ ዝርያ የሆኑ አስር የጥርስ ቅሪተ አካላትን አግኝተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ይህ ዝርያ የሰው ልጅ ዝርያ ከሆነው ቀደምት ጂነስ ሆሞ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ ይኖር እንደነበር አመላካች ነገሮች መኖራቸውን ሳይንቲስቶቹ ይፋ አድርገዋል።

በቁፋሮ የተገኙት ስድስት የመንጋጋ፣ ሁለት የፊት፣ አንድ የመጀመሪያ መንጋጋ እና አንድ የክራንቻ ጥርሶች ናቸው።

እነዚህ ጥርሶች አንድ ዓይነት ዝርያ ካላቸው ከሁለት የተለያዩ የአውስትራሎፒቲከስ የተገኙ መሆናቸው ተገልጿል።

እስካሁን ድረስ ስድስት የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን፣ የዝንጀሮ መሰል እና ሰው መሰል ባህሪያትን የያዙ ቀደምት የሰው ቅድመ አያት ናቸው።

አዲስ የተገኙት ጥርሶች ከስድስቱም አውስትራሎፒቲከስ ዝርያዎች ጋር ተመሳሳይነት የሌላቸው እና ሰባተኛ ዝርያ መሆናቸውን የሚጠቁሙ ባህሪያት እንዳላቸው ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል።

ይህ ምን ማለት ነው?

ቀደም ባሉት ጊዜያት የሚታወቁት የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያዎች፤ አውስትራሎፒቲከስ አናመንሲስ፣ አፋረንሲስ፣ አፍሪካነስ፣ ጋርሂ፣ እና ሌሎች ሳይንሳዊ ስያሜ ያላቸው ዝርያዎች ነበሩ።

በኢትዮጵያ የቅርስ ባለሥልጣን ፓሊዮቶሎጂ እና ፓሊዮአንትሮፖሊጂ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ቶማስ ጌታቸው፤ "አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ የመጨረሻው የታየበት ዘመን ከ2.95 ሚሊዮን ዓመት በፊት ነበር። ከዚያ በኋላ አልታየም። እንደገና እዚሁ አፋር አካባቢ አውስትራሎፒቲከስ ጋርሂ የሚባል በተመሳሳይ ጂነስ ውስጥ ግን የተለየ ዝርያ ተገኘ" ይላሉ።

የባለፈው ሳምንቱን የለዲ ገራሩ ግኝት አዲስ ያደረገውን ነገር "አዲሱ [የአውስትራሎፒቲከስ] ግኝት 2.6 ሚሊዮን ዓመት በፊት ነው። ስለዚህ ይህን ግኝት አዲስ ያደረገው ከሌሎቹ አሁን ከምናውቃቸው ከአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ እና ጋርሂ ከሚባሉት ዝርያዎች የተለየ መሆኑ ነው" ሲሉ ያብራራሉ።

"የጋርሂንም አፋረንሲስንም አይመስልም፤ እንደገና ደግሞ የእኛ ዝርያ የሚገኝበትን ሆሞም አይመስልም። ስለሆነም የተለየ የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያ ነው የሚለውን ነገር ያሳየ ነው" ሲሉ ያክላሉ።

በለዲ ገራሩ የተገኘው ግን የአውስትሮሎፒቲከስ ዝርያ ያለው ጥርስ ብቻ አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪም ሳይንቲስቶቹ ከ2.59 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠሩ ሦስት የጂነስ ሆሞ ጥርሶችን በዚሁ ቁፋሮ አግኝተዋል።

ዶ/ር ሰሚነው አስራት "[ቅሪተ አካላቱ] ለዲ ገራሩ የሚባል አካባቢ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ነው የተገኙት፤ በቦታው ውስጥ ትናንሽ ሳይቶች አሉ። እነዚህ 'locality' ይባላሉ። እያንዳንዳቸው 'locality' ዕድሜያቸው ይታወቃል" ይላሉ።

'ኔቸር' መጽሔት ላይ የታተመው የምርምር ግኝት 'ጉሩማህ'፣ 'ሊ አዶይታ' እና 'ጊዲ ሳንድ' የተባሉ ቦታዎችን ይዘረዝራል።

የተገኘው ምንድን ነው? ፋይዳውስ?

በአጭሩ የተገኘው ሁለት የተለያዩ ዝርያዎች ጥርስ ነው። አንዱ ወደ አውስትራሎፒቲከስ ይመደባል። አንደኛው ደግሞ ወደ ጂነስ ሆሞ ይመደባል። ነገር ግን ፋይዳው ከዚህ የዘለለ ነው።

አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ለመጨረሻ ጊዜ በታየበት (2.95 ሚሊዮን ዓመት በፊት) እና 2 ሚሊዮን ዓመት በፊት መካከል ያለው የሆሚኒን ቅሪተ አካል መዝገብ በቅጡ የሚታውቅ አይደለም።

ሳይንቲስቶቹ ካገኟቸው 13 የጥርስ ቅሪተ አካሎች መካከል አስሩ በሊ አዶይታ የተገኙ የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያ ጥርሶች ናቸው።

ሁለት የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያዎች በተቀራራቢ አካባቢ እና በተመሳሳይ ጊዜ አብሮ የመኖር ዕድላቸው ጠባብ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከዚህ ቦታ የተገኙት ጥርሶች የአንድ ነጠላ የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያ ናቸው ብለው ገምተው ነበር።

ዶ/ር ሰሚነው ሳይንቲስቶቹ ቅሪተ አካላቱን እንዳገኙ "አንድ 'species' ወይም አንድ ዝርያ መስሏቸው ከሉሲም ጋር ጨምሮ የተለያዩ የንጽጽር ትንታኔ (analysis) ሰርተዋል። እርስ በርሳቸውም ከአዎስትራሎፒቲከስም ጋርም ሠርተዋል። ስለዚህ ሳይንቲስቶቹ ማነጻጸር እና ማወዳደር ሲሠሩ አሁን ያገኟቸው የጥርስ ቅርጾች እና መዋቅሮች የተለዩ ሆነው አግኝተዋቸዋል። እስካሁን ካሉት ግኝቶች ጋር ተመሳሳይ አይደሉም" ሲሉ ይህን የሳይንቲስቶቹን ቅድመ ግምት ያብራራሉ።

ፓሊዮንቶሎጂስቱ ዶ/ር ቶማስም "[ቅሪተ አካሉ] የጋርሂንም አፋረንሲስንም አይመስልም፤ እንደገና ደግሞ የእኛ ዝርያ የሚገኝበትን ሆሞም አይመስልም። ስለሆነም የተለየ የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያ ነው የሚለውን ነገር ያሳየ ነው" ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ሳይንቲስቶቹ ሦስት የጥርስ ቅሪተ አካላትን ያገኙ ሲሆን፣ እነዚህ ቅሪተ አካላት የጂነስ ሆሞ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ዶ/ር ሰሚነው "አንደኛው ዝርያ ወደ ሆሞ የቀረበ ነው። ግን ከሆሞ ጋር ደግሞ ተመሳሳይ ሆኖ ስላላገኙት ሆሞ ነው፤ ነገር ግን የተለየ species (ዝርያ) ነው ብለው ገምተዋል" ይላሉ።

ሳይንቲስቶቹ ከሆሞ ጋር እና ከአውስትራሎፒቲከስ ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው የጥርስ ቅሪተ አካላት ማግኘታቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሰሚነው፤ "ሁለቱንም በአንድ ዝርያ ስር ላለመደብ የተለያየ 'species' ናቸው ብለዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ካሉት ግኝቶች ለየት ያሉ የጥርስ መዋቅር ሆነው ስላገኟቸው የተለያየ ሆሞ ዝርያ እና የአውስትራሎፒቲከስ ዝርያ ብለው ሰይመውታል" ሲሉ ያክላሉ።

የቅሪተ አካላቱን ዝርያ ለመለየት እና ሳይንሳዊ መጠሪያ ለመስጠት "በቂ የሆነ አካላዊ ቅርጽ መኖር አለበት፤ የእግር እና የእጅ ቅሪተ አካላትን ጨምሮ የሰውነት አካላት በዛ ብለው መገኘት አለባቸው" ይላሉ።

ሁለት የተለያዩ ዝርያዎች በአንድ ቦታ እና ጊዜ?

ተመራማሪዎች ልክ ቀደምት ሆሞ እና ፓራንትሮፕስ በኦሞ ቱርካና ተፋሰስ ባሉ ቦታዎች ላይ ተደጋጋፊ እንደነበሩ ሁሉ፤ በለዲ ገራሩ የተገኙ አዳዲስ ግኝቶች ቀደምት ሆሞ እና አውስትራሎፒቲከስ ሁለቱም በአፋር ክልል ከ2.5 ሚሊዮን ዓመት በፊት እንደነበሩ እንደጠቁሙ ገልጸዋል።

ይህ ማለት ሁለት የተለያዩ ቅድመ ሰው ልጅ ዝርያዎች በአንድ አካባቢ በተቀራራቢ ዘመን አብረው ይኖሩ ነበር ማለት ነው።

የቅሪተ አካላቱ ተመሳሳይ ዕድሜ እንደሚያመለክተው ይህ አዲስ የተገኘው አውስትራሎፒቲከስ ዝርያ በዚህ ክልል ውስጥ ከቀደምት የሆሞ ዝርያዎች ጋር አብረው መኖራቸውን ሲሆን፣ ይህም ለተፈጥሮ ሃብቶች ይፎካከሩ ነበር? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ዶ/ር ቶማስ ጌታቸው "የተገኙበት የጊዜ ማዕቀፍ ሆሞ እና ይሄ ገና ስያሜ ያልተሰጠው አውስትራሎፒቲከስ የተባለው ዝርያ በጋራ አንድ አካባቢ ላይ በተመሳሳይ የጊዜ ዘመን ውስጥ አብረው ይኖሩ እንደነበር የሚያሳይ ነው" ይላሉ።

የተመራማሪዎቹ ሳይንሳዊ ግኝት የሁለቱም ቀደምት ሆሞ እና አውስትራሎፒቲከስ በለዲ ገራሩ መገኘት በአካባባው ከሦስት እስከ ሁለት ሚሊዮን ዓመት በፊት ለሆሚኒን ምድብ እና ብዝኃነት ላይ አንድምታ እንዳለው ያወሳል።

ይህ ማለት ሆሞ እና አውስትራሎፒቲከስ በአፋር ክልል ከ2.5 ሚሊዮን ዓመታት በፊት አንድ ላይ አብረው ይኖሩ እንደነበር እና በምሥራቅ አፍሪካ ከ3 እና 2.5 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ቢያንስ አራት የሆሚኒ የዘር ሐረጎች አሉ ማለት ነው።

በለዲ ገራሩ የተገኙት ቅሪተ አካላት በ3 እና 2.5 ሚሊዮን ዓመት በፊት በዚሁ አካባቢ ቢያንስ ሦስት የዘር ሐረጎች እንደነበሩ ያመለክታል። እነሱም የሆሞ፣ አውስትራሊፒቲከስ ጋርሂ እና በለዲ ገራሩ የተገኘው አዲስ አውስትራሎፒቲከስ ዝርያ ናቸው።

"እስከ ዛሬ ባለው የቅድመ ታሪክ ወይም ደግሞ የሥነ ጥንት ምርምር ሂደት እንደዚህ ዓይነት ሁለት የተለያዩ ዝርያዎች በአንድ ሳይት ላይ ተገኝተው አያውቁም" ይላሉ ዶ/ር ሰሚነው።

"እስከዛሬ የሚታሰበው አውስትራሎፒቲከስ የጂነስ ሆሞ ቅድመ አያት ነው ተብሎ ነበር። ሆሞ የሚባለው የአውስትራሎፒቲከስ ቀስ በቀስ የመጣ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር። አሁን ግን ሁለቱ ዝርያዎች በተመሳሳይ ጊዜ፣ በተመሳሳይ ቦታ ላይ በመገኘታቸው ሁለቱ ተመሳሳይ ሃብት እየተጠቀሙ አብረው መኖር ችለዋል ማለት ነው" ሲሉም ግኝቱን ለየት የሚያደርገውን ነገር ያብራራሉ።

በተጨማሪም "እንደዚህ ዓይነት ግኝት እስካሁን ተገኝቶ አያውቅም። እስካሁን በሳይንሱ የሚታወቀው linear (መስመራዊ) የሆነ የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ መዋቅር እንዳለ ነው" ይላሉ።

ተመራማሪው "ብዙ ጊዜ ዝግመተ ለውጥን ስናስብ የሚታየው ምሥል አለ፤ ጦጣ የመሰለ፣ ከዚያ የተሻለ ቀጥ እያለ የጭንቅላት የማሰብ አቅሙ (brain capacity) እያደገ እየመጣ ዘመናዊ ሰዎችን የመሰለ ሆኖ ነው ያገኙት የሚባለው። ነገር ግን ይኼኛው መገኘቱ በሰው ልጅ አመጣጥ ላይ የተለየ አስተሳሰብ እንዲኖር አድርጓል" ሲሉ ያስረዳሉ።

በተጨማሪም "ብዙ ጊዜ የአካባቢ ወይም ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ቅድመ የሰው ልጅ ዝርያ በለውጥ ውስጥ እንዲያልፉ የሚያደርግ ወይም አንድ ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ እንዲቀየር ያደርጋል ተብሎ ይታሰብ ነበር። ነገር ግን አሁን ሁለቱም ተመሳሳይ የጊዜ ማዕቀፍ ላይ አንድ ቦታ ላይ አብረው መኖራቸው አንድ ዓይነት ሃብትን ሲጠቀሙ ነበር ማለት ነው" ይላሉ።

ዶ/ር ቶማስ ጌታቸው በዚህ ዘርፍ እስካሁን ያልተገኙ የተለያዩ ግኝቶች ሲገኙ ዘር ግንዱን የሚያሳይ ወይም የቤተሰብ ዘር ግንድ (family tree) የሚባለውን በተለየ መልኩ የሚቀይር ነው በማለት የግኝቱን ፋይዳ ያስረዳሉ።

"ለምሳሌ አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ብለን ከዚህ በፊት ቀጥታ ቅርንጫፉ የሚሄደው አውስትራሎፒቲከስ ጋርሂ ላይ ነው። ነገር ግን አሁን ከዚህ የበለጡ ግኝቶች ቢኖሩ በተለይም ይሄ ጥርስ ላይ ስለተመሠረተ ነው እንጂ፣ እንደ ጭንቅላት ያሉ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን ብናገኝ እነሱ የተሻለ የንጽጽር ጥናት በግልጽ የሚያሳየን ስለሚሆን በትክክለኛው የቤተሰብ ዘር ግንድ (family tree) ላይ ማስቀመጥ የሚቻልበትን ደረጃ ወይም ፍንጭ ያሳያል።"

"የአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ እና በጋርሂ መካከል ሌላ ግኝት ስላልነበረ ይታሰብ የነበረው ምናልባት የአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ለጋርሂ ቅርብ ነበር ተበሎ ነው" የሚሉት ዶ/ር ቶማስ፤ "አሁን ግን በእነሱ መካከል አዲሱ ግኝት ከእነዚህ ሁለቱ የተለየ ነው። ስለዚህ ሌላ መስመር (ቅርንጫፍ) እንዘረጋለን ማለት ነው። መስመራዊ (Linear) የነበረው [የሰው ልጅ አመጣጥ አረዳድ] ላይ ሌላ ቅርንጫፍ ይዘረጋል ማለት ነው" ሲሉ ያክላሉ።