አሜሪካ ስደተኞችን በጅምላ ማሰሯን ተከትሎ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ሀብታቸውን ለማፈሰስ ያመነታሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ በጆርጂያ በሚገኘው የሃዩንዳይ ፋብሪካ ላይ በድንገት ደቡብ ኮሪያውያን ሠራተኞችን በጅምላ ማሰሯን ተከትሎ የአገሪቱ ኩባንያዎች ሀብታቸውን ለማፍሰስ "በጣም ያመነታሉ" ሲሉ ፕሬዚዳንት ሊ ጄ ሚዩንግ ተናገሩ።
የአሜሪካ መንግሥት ከፋብሪካው ሰብስቦ ያሰራቸው ከ300 በላይ ደቡብ ኮሪያውያን አርብ ዕለት ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ተገልጿል።
ባለሥልጣናት የሚመለሱበት ጊዜ የዘገየው "በአሜሪካ ወገን በተፈጠሩ ሁኔታዎች" ነው ብለዋል።
"ይህ ሁኔታ እጅግ በጣም ግራ አጋቢ ነው" ያሉት ሊ ከአገር ውጭ የሚቋቋሙ ኩባንያዎችን ለማገዝ ደቡብ ኮሪያውያንን መላክ የተለመደ አሰራር ነው ብለዋል።
"ይህ ደግሞ መፈቀድ ካቆመ፣ በአሜሪካ ኩባንያዎችን መገንባት የበለጠ አስቸጋሪ ይሆንል. . . ኩባንያዎች እዚያ ሄዶ መስራት አዋጭ ይሆናል የሚለውን መጠየቅ ይጀምራሉ"
ቢቢሲ ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተየየት ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ባለስልጣናት 475 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ያዋሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 300 የሚሆኑት ደቡብ ኮሪያውያን ናቸው።
አሜሪካ የያዝኳቸው በአገሪቱ ውስጥ ካሉ እጅግ ግዙፍ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ በሆነው የደቡብ ኮሪያ የባትሪ ፋብሪካ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ እየሰሩ የነበሩ ናቸው ብላለች።
ሊ በስልጣን ላይ የቆዩበትን 100 ቀናት በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ደቡብ ኮሪያ ከዋሺንግተን ጋር ዜጎቿ ቪዛ ስለሚያገኙበት ሁኔታ "ከፍ ያለ ኮታ ወይንም አዲስ የቪዛ አማራጭ ማግኘት ላይ" እየተደራደረች ነው ብለዋል።
አክለውም "አሜሪካ ተግባራዊ ሊሆን አንደሚችል አስፈላጊ ጉዳይ የሚያዩት ከሆ ነበቅርቡ ምላሽ የሚሰጡ ይመስለኛል" ብለዋል።
በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካውያን ሠራተኞች ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ጊዜ የዘገየው ከዋይት ሐውስ በተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን ተናግረዋል።
"ሠራተኞቹ መቆየት የሚፈልጉ ከሆነ አሜሪካ ውስጥ መቆየት እንደሚችሉ የተሰጠው ትዕዛዙ መጣ የተባለው ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ነው"
የሃዩንዳይን ፋብሪካ የሚያንቀሳቅሰው ኤልጂ ኢነርጂ ሶሉሽን በቁጥጥር ስር የዋሉ በርካታ ሠራተኞቹ የተለያየ ዓይነት ቪዛ አላቸው ወይንም ደግሞ በአገሪቱ መቆየት የሚያስችል ቪዛ ተሰጥቷቸዋል ብሏል።
በፋብሪካው የሚሰራ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ የአሜሪካ መንግሥት በፋብሪካው ላይ በድንገት መጥቶ ሠራተኞችን በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት ስለተፈጠረው ግራ መጋባት ተናግሯል።
ሠራተኛው በቁጥጥር ስር የዋሉት አብዛኞቹ ሠራተኞች በኮንትራክተር የተቀጠሩ እና ማሽን የሚተክሉ መካኒኮች ናቸው።
በአገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙኃን እስሩን "አስደንጋጭ" ሲሉ የጠሩት ሲሆን ዶንግ አ ኢልቦ የተሰኘው ጋዜጣ "በአሜሪካ የሚኖረን ንግድ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ይቸልስበታል" ሲል አስጠንቅቋል።
ዩንሃፕ የዜና ወኪል ደግሞ "ሁለቱ አገራት ግንኙነት መካከል የተፈጠረውን ስንጥቃት በፍጥነት አንዲጠግኑ" ጠይቋል።
የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችው ደቡብ ኮሪያ፤ በዋሽንግተን የማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ላይ በአስር ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለማፍሰስ ቃል ገብታለች።
ይህንን ቃል የገባችበት አንዱ ምክያትን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ታሪፍ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በከፊል ለመከላከል ነው።
የሁለቱ አገራት መንግሥታት ሚስጥራዊ የንግድ ውይይት እያደረጉ ባለበት ወቅት የተካሄደው የፋብሪካው ዘመቻ፤ ሴኡል ውስጥ ስጋት ፈጥሯል።















