ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀይ ጨረቃ ማህበር በጋዛ የሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ በእስራኤል ጦር ጥቃት እንደተፈጸመበት አስታወቀ
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማህበር የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ በፈጸመው ጥቃት አንድ የረድዔት ሰራተኛው መገደሉንና ሶስት ደግሞ መቁሰላቸውን አስታወቀ።
እሁድ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት "እሳት በህንጻው ላይ ማስነሳቱን" የረድኤት ድርጅቱ ገልጿል።
በጋዛ፣ ኻን ዩኒስ ከተማ ደቡባዊ አካባቢ የሚገኘው የቀይ ጨረቃ ማህበር ዋና መስሪያ ቤት ላይ በእስራኤል የተፈጸመው ጥቃት "ሆን ተብሎ የተፈጸመ" እንደሆነ ተቋሙ ገልጿል።
የቀይ ጨረቃ ማህበር እንደሚለው ዋና መስሪያ ቤቱ በእስራኤል ጦር የሚታወቅ እንዲሁም እንደ ጥበቃ የሚታየው የቀይ አርማ መለዮ በግልጽ አለው።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በበኩሉ ጦሩ በፈጸመው ጥቃት የቀይ ጨረቃ ማህበር መስሪያ ቤት ህንጻ ተጎድቷል እንዲሁም በኻን ዩኒስ የሚኖሩ ተሳታፊ ያልሆኑ ግለሰቦች ተጎድታል የሚለውን ሪፖርት እየገመገምኩት ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
የቀይ ጨረቃ ማህበር በማህበራዊ ሚዲያ ባጋራው ቪዲዮ ላይ የህንጻው ክፍሎች በእሳት ተያይዞ ጭስ ሲወጣ ያሳያል። በኋላም ላይ በወጡ ምስሎች ህንጻው ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት እና ደም ተረጭቶም ያሳያሉ።
የረድዔት ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ቅዳሜ ለእሁድ ከእኩለ ሌሊት በኋላ የእስራኤል ጦር የህንጻውን ላይኛውን ፎቆች በከባድ መሳሪያ በቀጥታ መትቶታል" ብሏል።
"የቀይ ጨረቃ ማህበር ቡድን አባላት ሰራተኞችን እያስወጡ እንዲሁም ጉዳቱን እየገመገሙ በነበረበት ወቅት ሁለተኛው ፎቅ በድጋሚ የተመታ ሲሆን ከዚያም የከባድ መሳሪያ ጥቃቱ በታች ባሉ የህንጻው ክፍሎች ቀጠለ። በዚህ ወቅት የነፍስ አድን ቡድኖቻችን የቦምብ ጥቃቱ ያስነሳውን እሳት ለማጥፋት እየታገሉ ነበር" ሲል መግለጫው አትቷል።
ተቋሙ የተገደለው የረድዔት ሰራተኛው "ኦማር ኢስሊም" እንደሚባል ገልጾ፤ ግድያውን "ልብ ሰባሪ" ብሎታል።
በጥቃቱ ሁለት የረድዔት ሰራተኞች እንዲሁም እሳቱን ሊያጠፋ የሞከረ አንድ ሲቪሊያን መጎዳቱን አስረድቷል። ተቋሙ ዋና መስሪያ ቤቱ በአርማው "ግልጽ ምልክት" እንደተደረገበት አጽንኦት ሰጥቷል።
"ይህ ስህተት አይደለም። የረድዔት እና የህክምና ባለሙያዎች በሙሉ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጥሪ እናቀርባለን" ብሏል።
የጋዛ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ "51 ሰራተኞቹ እና በጎ ፈቃደኞቹ" በእስራኤል ጦር ጥቃት እንደተገደሉበት የገለጸው የረድኤት ድርጅቱ ከነዚህም ውስጥ 29 ሰብዓዊ ተግባራትን ሲያከናውኑ ህይወታቸውን መቀጠፉን አክሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ "በጋዛ በረድዔት ሰራተኞች ላይ የሚደረገው ግድያ መቀጠሉ ድንጋጤ እንዲሁም ቁጣ እንደፈጠረበት" ገልጾ ነጻ ምርመራ እንዲካሄድ አሳስቧል።
የረድዔት ድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ጥቃት የተሰማው በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ቀውስን በተመለከተ በርካታ ማሳሰቢያዎች እየወጡ ባለበት ወቅት ነው።
እሁድ እለት የእስራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት 104 ፍልስጤማውያን በ24 ሰዓታት ውስጥ መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር ገልጿል።
ከነዚህም ውስጥ 65ቱ እርዳታ ሲጠባበቁ የነበሩ እንደሆነ በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አክሏል።
እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።
የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ድርጅት አቋቁመዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
በባለፉት ሁለት ወራት የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥም 766 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።
ቀሪዎቹ 288 ፍልስጤማውያን ደግሞ የተገደሉት የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።