ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት እየፈጸመች ነው አሉ
ሁለት ስመ ጥር የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እስራኤል ጋዛ ውስጥ በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመች እንደሆኑ አስታወቁ።
'ቤትሰሌም' እና 'ፊዚሻን ፎር ሂውማን ራይትስ እስራኤል' የተሰኙት በእስራኤል ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ ተቋማት የጋዛን ጦርነት አስመልክቶ ባወጡት ሪፖርት እስራኤል በፍልስጤም ሕዝብ ላይ እየፈጸመችው ያለው ድርጊት በዘር ፍጅትነት የሚፈረጅ ነው ብለዋል።
የመብት ቡድኖቹ ያለፉትን 21 ወራት የጋዛ ጦርነት አስመልክቶ ያደረጓቸውን ጥናቶች ሰኞ፣ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም. ይፋ አድርገዋል።
በእስራኤል ውስጥ መቀመጫቸውን ለአስርት ዓመታት ያደረጉት እና በንቁ ተሳትፏቸው የሚታወቁት ተቋማቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ "ወንጀሎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ ከማድረግ በተጨማሪ፤ በዚህ የጨለማ ወቅት ድርጊቶችን በስማቸው መጥራት መሠረታዊ ጉዳይ ነው" ብለዋል።
እስራኤላውያኑ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች አገራቸው "በፍልስጤማውያኑ ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው" በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጡትን ሪፖርት የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ውድቅ አድርገውታል።
"የእኛ መከላከያ ሠራዊት በአሸባሪዎች ላይ እንጂ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አያነጣጥርም። በጋዛ ለሚደርሰው ሰቆቃ ተጠያቂው ሐማስ ነው" ሲሉ ዴቪድ ሜንሰር ተናግረዋል።
የቤትሰሌም ዋና ዳይሬክተር ዩሊ ኖቫክ ተቋማቸው እንዲህ ዓይነት ሪፖርት "እናወጣለን ብለን አስበን አናውቅም" ሲሉ ሰኞ ዕለት በእየሩሳሌም በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል።
ባለ 88 ገጹ ሰነድ እንደሚያትተው "እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምትከተለው ፖሊሲ እና ያስከተለውን አሰቃቂ ሁነቶች ፤እንዲሁም የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ወታደራዊ አዛዦች የጋዛን ጥቃት አላማ አስመልክቶ የሰጡትን መግለጫዎች ስንፈትሽ፤እስራኤል ሆን ብላ በጋዛ ሰርጥ የሚገኘውን የፍልስጤም ሕዝብ ለመፍጀት የተቀናጀ እርምጃ እየወሰደች ነው ወደሚል የማያሻማ ድምዳሜ ይመራናል" ይላል።
'ፊዚሻንስ ፎር ሂውማን ራይትስ እስራኤል' በበኩሉ ባወጣው 65 ገጽ ሪፖርቱ እስራኤል የጋዛን የጤና አጠባበቅ ሥርዓት "በተሰላ እና ስልታዊ በሆነ መልኩ" ዒላማ ማድረጓን በጤና ላይ ያተኮረ የሕግ ትንታኔ መሥራቱን አስታውቋል።
"መረጃዎቹ የጋዛን ጤና እና የሕይወት አድን ሥርዓቶች ሆን ተብሎ ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዲወድሙ መደረጉን ያሳያል። ለእነዚህም ማሳያዎቹ በሆስፒታሎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ የሕክምና እርዳታዎች ክልከላ፣ የጤና ባለሙያዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች እና እስሮች ናቸው" ሲል ሪፖርቱ አጽንኦት ሰጥቷል።
የፊዚሻንስ ፎር ሂውማን ራይትስ እስራኤል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጋይ ሻሌቭ እንዳሉት "የዘር ማጥፋት ሲፈጸም ዝም ማለት አማራጭ አይደለም። የዘር ማጥፋትን መጋፈጥ የሕግ እና የፖለቲካ ተቋማት ኃላፊነት ብቻ አለመሆኑን እና ይህንን ዓለም አቀፉ የጤና ማኅበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰብ እንፈልጋለን" ብለዋል።
ተቋማቱ ሐማስ ከ21 ወራት በፊት በእስራኤል ላይ "የፈጸመው ጥቃት" በእስራኤላውያን ዘንድ ፍርሃትን እና ሰቆቃን ያነሳሳ ቀስቃሽ ክስተት ሆኖ አግኝተውታል።
ሆኖም የእስራኤል መንግሥት ለጥቃቱ ምላሽ በሚል "በጋዛ ውስጥ ያሉ ፍልስጤማውያንን ከሰብዓዊነት ማማ በማውረድ እንዲሁም ጽንፈኛ የሆነ የማጥፋት ዘመቻን" የተከተለ ነው ብለዋል።
ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ አዛዦች እንዲሁም ተዋጊ ወታደሮች ጭምር የሚጠቀሟቸው ቃላት በጋዛ ውስጥ ያሉ ፍልስጤማውያንን በሙሉ ተጠያቂ ያደረገ እንደሆነም ተቋማቱ በሪፖርታቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተቋሙ እስራኤል እየፈጸመችው ያለው ድርጊት "በፍልስጤማውያን ላይ ያነጣጠረ የፖሊሲ አካል ነው" ሲል ድምዳሜ ሰጥቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች፣ ምሁራንን ጨምሮ በርካታ የዓለም አቀፍ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመች ነው ሲሉ ይከሷታል።
የዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት በበኩሉ የእስራኤል ጦር በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸመ ነው በሚል በደቡብ አፍሪካ የቀረበውን ክስ እየመረመረ ይገኛል።
እስራኤል በበኩሏ ክሱን አጥብቃ በመቃወም "ፍጹም መሠረተ ቢስ" እና ሐሰተኛ ስትል ውድቅ አድርጋዋለች።
ዶክተር ሻሌቭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስራኤል የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው በሚለው ሪፖርታቸው ተቋማቱ እንዲሁም ሠራተኞቻቸው ከእስራኤል የቃል ወይም አካላዊ ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸዋል።
"ሆኖም የምንናገረውን ነገር ሰዎች እንደሚሰሙን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል።
የቤትሰሌም ዩሊ ኖቫክ እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት እየፈመች ነው ወደሚል መደምደሚያ ላይ መድረሱ ቀላል እንዳልነበር ተናግረዋል።
"አገራችሁ፣ የጋራ የሆነችው በእርግጥ የዘር ማጥፋት እየፈጸመች መሆኑን ለመረዳት በጣም ከባድ የአዕምሮ ሂደት ነው" ብለዋል።
አክለውም "ስለ ማንነታችን ያለንን ግንዛቤ መሠረታዊ ነገር የሚሰብር ነው" ሲሉም አክለዋል።