ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዓለምን ያስደነገጠው የጋዛ ረሃብ ፎቶግራፍ ታሪክ
እናቱ እቅፍ ላይ ሆኖ ሲታይ ቆዳው የሸፈናቸው የአከርካሪ እንዲሁም የጎድን አጥንቶቹ ይቆጠራሉ።
በእናቱ እቅፍ ላይ ጥቅልል ብሎ የሚታየው ጨቅላ በረሃብ ክፉኛ ተጎድቷል።
ይህ የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሕጻን ሞሐመድ ዛካሪያ አዩብ አል ማቶቅ ይባላል።
በጋዛ እንደሚገኙ የእድሜ እኩዮቹ ረሃብ እጅጉን ጎድቶታል። ይህ ሕጻን በእናቱ እቅፍ ሳለ ፎቶ ያነሳው ጋዜጠኛ አህመድ አሪኒ፣ እአአ ሐምሌ 21 በጋዛ ሰርጥ በአንድ የተፈናቃዮች መጠለያ ድንኳን ውስጥ አግኝቷቸው ነው።
በጋዛ መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮች ለማግኘት እጅጉን አዳጋች ነው።
ምግብ፣ መድሃኒት፣ የነዳጅ ዘይት በእስራኤል የእርዳታ እቀባ ምክንያት ለጋዛ ነዋሪዎች በበቂ እየደረሱ አይደሉም።
የሞሐመድ እናት ሄዳያ አል ሙታ ለቢቢሲ በመጠለያ ድንኳኗ ውስጥ እየገፋች ያለችውን አሰቃቂ ሕይወት ተናግራለች።
"አሁን ስድስት ኪሎ ነው የሚመዝነው፤ በፊት ግን ዘጠኝ ኪሎ ነበር። ጥሩ ይመገብ ነበር። ነገር ግን አሁን ባለው የምግብ እጥረት የተነሳ በጣም ተጎድቷል" ትላለች የልጇን እጅ ይዛ ።
ሄዳያ በምግብ እጦት ምክንያት ሞሐመድ "እንደማንኛውም ልጅ መቀመጥም ሆነ መቆም አይችልም" እና የተጠማዘዘ ጀርባ ሲንድሮም (curved back syndrome) የሚባል የጀርባ አጥንት ሕመምተኛ ሆኗል። ከዚህም በተጨማሪ አጥንቱ በዶርሳል ፕሮቱበራንስ (dorsal protuberance) መጠቃቱ ተነግሯታል።
"ምንም አቅም የለኝም፤ባለቤቴ በጦርነቱ ተገድሏል፤ከፈጣሪ በቀር ማንም የለኝም።ብቻዬን ስለሆንኩ ልመግበው አልችልም፤ጠንክሬ እሰራለሁ፣ ነገር ግን የዱቄት ወተት ልገዛለት እንኳን አልችልም፤ ደክሞኛል" ትላለች።
ጋዜጠኛው አህመድ አል አሪኒ ለቢቢሲ ኒውስአወር እንደተናገረው የሄዳያ እና የልጇ ምስል በዓለም ላይ በጋዛ ያለውን የከፋ ረሃብ በማሳየት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
"እያንዳንዱን ፎቶ ካነሳሁ በኋላ ማቆም እና መረጋጋት፣ ትንፋሼን መሰብሰብ እና መቀጠል ነበረብኝ" ሲል የተመለከተው የስቃይ ሁኔታ እንዴት እንደረበሸው ተናግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው ወደ ጋዛ ለመግባት እየተጠባበቁ የሚገኙ 6,000 እርዳታ የጫኑ መኪናዎች አሉ። በአካባቢው ያለው ረሃብ "እንደ አሁኑ አስከፊ ሆኖ አያውቅም" ሲል አስጠንቅቋል።
እስራኤል በቂ ዕርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ፈቅጃለሁ ስትል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወቅቱ ማከፋፈል ባለመቻሉ ወቅሳለች። ለተመጣጠነ ምግብ እጥረቱም ቢሆን ተጠያቂው ሐማስ ነው ትላለች።
የቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት በመጪዎቹ ቀናት የውጭ አገራት ርዳታ ለጋዛ ነዋሪዎች ከአየር ላይ እንዲጥሉ እንደሚፈቅድ አስታውቋል።
የድንበር የለሽ ሐኪሞች (ኤምኤስኤፍ) በበኩሉ ሠራተኞቹ "አስከፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት" እያዩ ነው ብሏል።
ፊስታል እንደ ዳይፐር
"የሕፃን መሐመድን ፎቶ ያነሳሁት ከእናቱ ጋር በመጠለያ ውስጥ በነበረበት ወቅት ነው። በሰሜን ጋዛ ከሚገኘው ቤታቸው ተፈናቅለው ነው ወደዚህ የመጡት" ይላል አህመድ።
"ከአንዲት ትንሽ ምድጃ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ባዶ በሆነ ድንኳን ውስጥ ነበር የሚኖሩት። መቃብር ይመስላል። እና ፎቶውን ያነሳሁት በጋዛ ሰርጥ ያሉ ልጆች እና ሕጻናት በከፍተኛ ረሃብ እንዴት እንደሚሰቃዩ ለዓለም ሕዝብ ለማሳየት ስለፈለኩ ነው።"
ፎቶግራፉን ያነሳው ጋዜጠኛ፣ ሞሐመድ "ወተት፣ የዱቄት ወተት ወይም ቫይታሚኖችን አግኝቶ አያውቅም" ሲል ተናግሯል።
"ፎቶውን በደንብ ካያችሁት ከዳይፐር ይልቅ የላስቲክ ከረጢት አድርጎ ይታያል። በሰብዓዊ እርዳታ እና በመድሃኒት እጦት ምክንያት የእቃ ዋጋ በጣም ጨምሯል፤ ስለዚህ ጋዛ ውስጥ ማንም አቅሙ ኖሮት ሊገዛ አይችልም" ብሏል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው 122 ፍልስጤማውያን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ቢያንስ 83ቱ ሕጻናት ናቸው።
አህመድ፣ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በጋዛ ያለውን ሁኔታ እንደዘገቡት ሌሎች የፎቶ ጋዜጠኞች ሁሉ፣ ይህን አሰቃቂ ሁኔታ በምስል ለማስቀረት ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ሲገልጽ "ሕፃናት በከፍተኛ ረሃብ እንደሚሰቃዩ እና ምን ያህል አቅመ ቢስ እንደሆኑ ማየቴ በጣም ረብሾኛል፤ እኔም ሰው ነኝ።"
ለዚህም ነው አህመድ ሞሐመድን እና ሄዳያን ሲያገኛቸው ፎቶግራፎቹን ለማንሳት ብዙ ጊዜ እንደፈጀበት የተናገረው።
በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ያገኘው ይህ ሕፃን ብቻ አይደለም።
"እንዲህ ዓይነት ብዙ ረሃብ የጎዳቸው ልጆችን አይቻለሁ። በሌላ ቀን የ17 ዓመት ልጅ በአንድ ወር ውስጥ 25 ኪሎ የቀነሰ ፎቶ አንስቻለሁ። ሰዎች በጋዛ ሰርጥ ምግብ ማግኘት አልቻሉም፤ ረሃብ ብቻ ሳእሆን ከፍተኛ የምግብ እጥረት አለ፣ እናም ሰዎች ትንሽ እርዳታ ለማግኘት ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ይታገላሉ።"
የፎቶግራፍ ባለሙያው አህመድ ራሱ በረሃብ እየተሰቃየ ነው።
ሐሙስ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገረው "ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ምግብ በአፌ አልዞረም። አሁን እያወራሁህ በጣም ርቦኛል፤ ምግብ ለማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ነው።"
"የወንድሞቼ እና የእህቶቼ ልጆች ከትናንት ጀምሮ እያለቀሱ ነበር። አባታቸውን አንድ ቁራጭ ዳቦ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። የሚያስፈልጋቸው ቁራጭ ዳቦ ብቻ ነው። ግን ለሁሉም ሰው የሚሆን በቂ ምግብ የለም" ብሏል።
አንዳንዴ ስራውን ለመስራት አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ይናገራል።
"ፎቶዎቼን ለማንሳት እሄዳለሁ፤ እና በተመሳሳይ ጊዜ ይጨንቀኛል፤ ርቦኛል፤ ደክሞኛል፤ ሚዛኔን ለማሰት እንገዳገዳለሁ፤ ብዝ ይልብኛል። እኔም በውሃ እጦት፣ በጥም እቃጠላለሁ፤ ስለዚህ ሁላችንም እንሰቃያለን።"
"ብዙ ባልደረቦቼ በከፍተኛ ረሃብ እና ጥማት ሲወድቁ ተመልክቻለሁ።"
አህመድ ከዚህ ቀደም ለስራው ክፍያ ለመቀበል መተግበርያ ይጠቀም እንደነበር ተናግሮ፣ አሁን ግን ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ገንዘቡን በእጁ የሚሰጡት ሰዎች 40 በመቶ የአገልግሎት ዋጋ ይቆርጡበታል።
ምንም ነገር ከመግዛቴ ወይም ደመወዜ እጄ ከመግባቱ በፊት ግማሽ ያህሉ ጠፍቷል ሲል ሁኔታውን ይገልጸዋል።
ጋዜጠኛው የመሠረታዊ እቃዎች አቅርቦት በመቋረጡ እና እጥረት በመፈጠሩ ምክንያት ምርቶችን የሚገበያዩት በጥቁር ገበያ ሲሆን ዋጋቸውም ሊቀመስ የሚችል እንዳልሆነ ያስረዳል።
"ወደ ጋዛ እየገባ ያለው ትንሽ እርዳታ ለማንም አይበቃም፤ በዚህ ላይ የውሃ እጥረት አለ። በርግጥ አሁን አነስተኛ መጠን ያለው ዱቄት እየገባ ነው። ይህንንም ለመግዛት በጥቁር ገበያ ዋጋው ጨምሯል። ስለዚህ አሁን አንድ ኪሎ ዱቄት 16 የአሜሪካ ዶላር ይሸጣል" ብሏል።
"ከጦርነቱ በፊት ጋዛ ውብ ነበረች፤ ንፁህ እና ቆንጆ ጎዳናዎች ነበሯት። አሁን በሁሉም አቅጣጫ ውድመት ነው። … ያሉት ብቸኛው የመጓጓዣ አማራጮች በአህያ የሚጎተቱ ጋሪዎች ናቸው።
ከመካከለኛው ዘመን በፊት ወደ ነበረው ወደ ኋላ ተመለስን። ማኅበረሰቡ የተሰራበት ድርና ማግ በተግባር ወድሟል… ሰዎች በዚህ ጦርነት አቅመ ቢስ እና ደካማ መሆናቸው ይሰማቸዋል፤ እና በረሃብ እና ውሃ ጥም የበለጠ ተሰቃይተዋል።"