በ200 ዩኒቨርስቲዎች ማመልከቻ ያስገባው ጥቁር አሜሪካዊ 9 ሚሊዮን ዶላር ለስኮላርሺፕ ቀረበለት

ዴኒስ ባርነስ ይባላል። ገና 16 ዓመቱ ነው። ኒው ኦርሊያንስ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት በማጠናቀቅ ላይ ሳለ ለከፍተኛ ትምህርት ማመልከት ይጀምራል።

ከባለፈው ነሐሴ ጀምሮ ዴኒስ ለ200 ኮሌጆች ማመልከቻ ያስገባ ሲሆን እስከ አሁን 125ቱ እንደተቀበሉት ተናግሯል።

አሁንም ሌሎች ተጨማሪ ኮሌጆች እንደሚቀበሉት ተስፋ ያደርጋል።

እስከ አሁን የቀረበለት የስኮላርሺፕ መጠን ወደ ገንዘብ ሲቀየር 9 ሚሊዮን ደርሷል።

ዴኒስ ባርነስ በአሜሪካ ታሪክ ብዙ ዩኒቨርስቲዎች የተቀበሉት ተማሪ ሆኖ ክብረ ወሰን እንደሰበረ እየተነገረለት ነው።

“ዕቅዴ 10 ሚሊዮን ዶላር መድረስ ነው” ብሏል ዴኒስ፣ ዜናውን ለዓለም ላበሰረው የደብሊው ደብሊው ኤል ቲቪ።

ከዴኒስ በፊት ክብረ ወሰኑ ተይዞ የነበረው ከሦስት ዓመት በፊት የሊዊዚያና ተማሪ በነበረችው ኖርማንዴ ኮርሚየር ነበር።

ኮርሚያር በሊዊዚያና ግዛት በዣቪየር ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረች ሲሆን አሁን የማስተርስ ዲግሪዋን በሊዊዚያና ስቴት ዩኒቨርስቲ እየተከታተለች ትገኛለች።

ከሦስት ዓመት በፊት ለዚህች ተማሪ 140 ኮሌጆች በድምሩ 9.4 ሚሊዮን ዶላር የስኮላርሺፕ ገንዘብ አቅርበውላት ነበር።

በወቅቱ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ እንደዘገበው ጊነስ የድንቃ ድንቅ መዝገብ ይህን ስኬቷን እንደሚዘግብላት ኮርሚያር ፈልጋ የነበረ ሲሆን ነገር ግን በዓለም ላይ የሚገኙ ኮሌጆች አሠራር ወጥነት ስለሌለው ስኬቷ ሊመዘገብላት አልቻለም ።

ዴኒስ ባርነስ ይህ ዜና ከተሰማ ወዲህ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ በእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ከቁጥጥር ውጭ እንደሆነበት አስታውቋል።

ጥቁር አሜሪካዊው ዴኒስ ስፓኒሽ ቋንቋን አቀላጥፎ ይናገራል። የናሽናል ኦነርስ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንትም ነው። የትምህርት ቤት ጠቅላላ አማካይ ነጥቡ በጣም ከፍተኛ የሚባል ነው። ገና 2ኛ ደረጃ ሳይጨርስ የኮሌጅ ኮርሶችን በሳውዘርን ዩኒቨርስቲ ኒው ኦርሊየንስ እየወሰደም ይገኛል።

ዴኒስ “ጥቁር ስትሆን ከትምህርት ይልቅ ቅርጫት ኳስ መጫወት ነው የሚጠበቀው፤ እኔ በትምህርትም መላቅ እንደሚቻል ማሳየቴ አስደስቶኛል” ብሏል።

ብዙ ሰው ለኮሌጆች ማመልከት አድካሚ ነው ይላል፤ ለኔ ግን እንደዚያ አይሰማኝም። ማመልከት የጀመርኩት በመጀመርያው ዓመት ነበር፤ ቀስ በቀስ እዚህ ደረስኩ ብሏል።

ዴኒስ የሚማርበት ትምህርት ቤት ዜናውን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በተማሪው ዴኒስ እንደሚኮራና ጥምር ዲግሪ ለመማር እንደሚፈልግ አስታውቋል። ዲግሪውም በኮምፒውተር ሳይንስና ወንጀልና ሥነ ፍትሕ ዘርፍ ይሆናል ብሏል።

ተማሪው በመጨረሻ የት ኮሌጅ ሊገባ እንደሚችል በሚቀጥለው ዓመት ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

ዴኒስ ለኮሌጅ ስኮላርሺፕ አመልካቾች ምክር ካለው ተጠይቆ፣ “የስኬት ቁልፉ ቀድሞ ማቀድ ነው፤ ግብህን ቀድመው ካየኸው ትደርስበታለህ” ብሏል።