በሪያል ማድሪዱ ቪኒሲየስ ላይ ከተሰነዘረው የዘረኝነት ጥቃት ጋር በተያያዘ ሦስት ሰዎች ታሰሩ

ቪኒሲየስ ጁኒየር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቪኒሲየስ ጁኒየር

የስፔን ፖሊስ ሦስት ሰዎችን በሪያል ማድሪዱ ተጫዋች በቪኒሲየስ ጁኒየር ላይ በተሰነዘረው የዘረኝነት ስድብ ጠርጥሪያቸዋለሁ ብሎ አስሯል።

ሦስቱ ተጠርጣሪዎች በሪያል ማድሪዱ ቁልፍ ተጫዋች ቪኒሲየስ ጁኒየር ላይ የዘረኝነት ጥቃት ሰንዝረዋል ተብለው ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 21 እንደሚገመት የስፔን ፖሊስ በትዊተር ሰሌዳው ገልጧል።

ብራዚላዊው እግር ኳስ ተጫዋች ቪኒሲየስ ጁኒየር በጥቁር የቆዳ ቀለሙ የተነሳ ለዘረኝነት ስድቦች ሲጋለጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው እሑድ ቡድኑ ማድሪድ ከቫለንሺያ ጋር በነበረው ጨዋታ በእርሱ ላይ የደረሰው ጥቃት በብራዚል እና ስፔን ውስጥ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

በእሑዱ ጨዋታ የዘረኝነት ጥቃቱ የረበሸው ይህ ተጫዋች ለዳኛ ሁኔታውን በማሳወቁ ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንዲቆም ምክንያት እስከመሆን ደርሷል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የ22 ዓመቱ ቪኒሲየስ ጁኒየር የሰጠው አስተያየት ደግሞ ሌላ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኗል።

ቪኒሲየስ ጨዋታውን ተከትሎ በሰጠው አስተያየት “ላ ሊጋ የዘረኞች ቦታ ሆኗል” ማለቱ ሌላ ውዝግብ ፈጥሯል።

በዚህ አስተያየቱ የተቆጡት የላ ሊጋ ፕሬዝዳንት ጃቪየር ቴባስ ትዊተር በጻፉት ምላሽ “እንዲህ ዓይነት የዘረኝነት ስድቦች ሲኖሩ ለመነጋገር ሁለት ጊዜ ጠርተንህ አልተገኘህም። አሁን ላ ሊጋን ትዘልፋለህ፤ መጀመሪያ ራስህ ምን ማድረግ እንዳለብህ እወቅ” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለሰጡት አስተያየት ተጫዋቹ ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ የሰጠ ሲሆን በትዊተር ሰሌዳው የጻፈው መልዕክት በከፊል እንዲህ የሚል ይዘት አለው።

“እርስዎ ዘረኞችን ከመውቀስ ይልቅ እኔን መውቀስን መርጠዋል። ይህን ማድረግዎ ከዘረኞቹ ተርታ ያሰልፍዎታል። ስለዘረኝነት ለማውራት የሚጋብዙኝ ጓደኛዎ አይደለሁም። የእርስዎ ድርሻ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ነው።”

የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አለቃ ሉዊስ ሩቢያልስ በበኩላቸው “የስፔን እግር ኳስ [በረዘረኝበት ላይ] መሠረታዊ ችግር አለበት። ይህ ክለቦችን፣ ቡድኖችን ጭምር የመረዘ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

የስፔን ዐቃቤ ሕግ አሁን የወንጀል ክስ ለመክፈት ሁኔታዎችን እየመረመረ ይገኛል።

የብራዚል መንግሥት በበኩሉ ይህ የዘረኝነት ጉዳይ በምንም መለኪያ ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሶ ከስፔን ሚኒስትሮች፣ ዐቃቤ ሕግ እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች ጋር አስቸኳይ ምክክር እንዲደረግ ጠይቋል።

ቀደም ብሎ የስፔን ፖሊስ አራት ሰዎችን ማሰሩ ይታወሳል። አራቱ ሰዎች በማድሪድ ድልድይ ላይ የቪኒሲየስ ጁኒየርን ምስል የያዘ ጸያፍ ምስል ሰቅለዋል ተብለው ነው።

ይህ ምስል የተሰቀለው ማድሪድ ከአትሌቲኮ ከነበረው ጨዋታ ቀደም ብሎ ነው።

ምን ነበር የተከሰተው?

የሪያል ማድሪድ ተጫዋቹ ቪኒየስ ጁኒየር የዘረኝነት እሁድ ዕለት ጥቃት ከደረሰበት በኋላ “ላ ሊጋ የዘረኞች ሆኗል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የ22 ዓመቱ ብራዚላዊ በ97ኛው ደቂቃ ከቫሌንሲያው ኡጎ ዱሮ ጋር በፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በቀይ ካርድ ከሜዳ አንዲወጣ ተደርጓል።

ጨዋታው ከጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ ቪኒሲየስ የቫሌንሲያ ደጋፊዎችን ድርጊት ለዳኛው ለማስረዳት ሲሞክር ነበር።

ቪኒሲየስ በኢንስታግራም ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት “በአንድ ወቅት የሮናልዲንሆ፣ የሮናልዶ፣ የክሪስቲያኖ እና የሜሲ የነበረው ላ ሊጋ ዛሬ የዘረኞች መፈንጫ ሆኗል” ብሏል።

“ይህ የመጀሪያው አይደለም። ሁለተኛው አሊያም ሦስተኛው አይደለም። ዘረኝነት በላ ሊጋ የተለመደ ሆኗል። ከምንም አይቆጠርም። ፌዴሬሽኑም እንዲሁ ምንም አይመስለውም። ተቀናቃኞች ደግሞ ያበረታቱታል።”

ቪኒ አክሎ “በጣም ውብ አገር፤ በፍቅር የተቀበለችኝ እኔም የምወዳት ናት። ነገር ግን ምስሏ በዘረኝነት እየተባለሸ ነው። በእኔ ሐሳብ ለማስይስማሙ ስፔናውያን ይቅርታ እላለሁ፤ ነገር ግን አሁን ብራዚል ውስጥ ስፔን እንደ ዘረኛ አገር ነው የምትታየው። የዘረኞች አገር ተደርጋ ነው የምትቆጠረው” ሲል ሐሳቡን አስፍሯል።

“የሚያሳዝነው በየሳምንቱ የሚፈጠረውን ነገር እኔ የምመክትበት አቅም የለኝም። ቢሆንም እኔ ጠንካራ ነኝ። እስከ መጨረሻው ዘረኞችን እፋለማለሁ። ከዚህም ርቄ ቢሆን።”

ላ ሊጋው በለቀቀው መግለጫ “ይህንን ባሕሪ ለዓመታት ስንታገለው ነበር። የስፖርቱን አዎንታዊ ገፅታ ለማስተዋወቅ እየሠራን ነው። ሜዳ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳም ውጪም ቢሆን” ብሏል።