“አንድ ሰሞን የክሪስቲያኖ እና ሜሲ የነበረው ላ ሊጋ. . .የዘረኞች ሆኗል”፡ የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ቪኒሲየስ ጁኒየር

 ቪኒየስ ጁኒየር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቪኒየስ ጁኒየር

የሪያል ማድሪድ አጥቂ ቪኒየስ ጁኒየር የዘረኝነት ጥቃት ከደረሰበት በኋላ “ላ ሊጋ የዘረኞች ሆኗል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የ22 ዓመቱ ብራዚላዊ በ97ኛው ደቂቃ ከቫሌንሲያው ኡጎ ዱሮ ጋር በፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በቀይ ካርድ ከሜዳ አንዲወጣ ተደርጓል።

ጨዋታው ከጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ ቪኒሲየስ የቫሌንሲያ ደጋፊዎችን ድርጊት ለዳኛው ለማስረዳት ሲሞክር ነበር።

ቪኒሲየስ በኢንስታግራም ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት “በአንድ ወቅት የሮናልዲንሆ፣ የሮናልዶ፣ የክሪስቲያኖ እና የሜሲ የነበረው ላ ሊጋ ዛሬ የዘረኞች መፈንጫ ሆኗል” ብሏል።

“ይህ የመጀሪያው አይደለም። ሁለተኛው አሊያም ሦስተኛው አይደለም። ዘረኝነት በላ ሊጋ የተለመደ ሆኗል። ከምንም አይቆጠርም። ፌዴሬሽኑም እንዲሁ ምንም አይመስለውም። ተቀናቃኞች ደግሞ ያበረታቱታል።”

ቪኒ አክሎ “በጣም ውብ አገር፤ በፍቅር የተቀበለችኝ እኔም የምወዳት ናት። ነገር ግን ምስሏ በዘረኝነት እየተባለሸ ነው። በእኔ ሐሳብ ለማስይስማሙ ስፔናውያን ይቅርታ እላለሁ፤ ነገር ግን አሁን ብራዚል ውስጥ ስፔን እንደ ዘረኛ አገር ነው የምትታየው። የዘረኞች አገር ተደርጋ ነው የምትቆጠረው” ሲል ሐሳቡን አስፍሯል።

“የሚያሳዝነው በየሳምንቱ የሚፈጠረውን ነገር እኔ የምመክትበት አቅም የለኝም። ቢሆንም እኔ ጠንካራ ነኝ። እስከ መጨረሻው ዘረኞችን እፋለማለሁ። ከዚህም ርቄ ቢሆን።”

ላ ሊጋው በለቀቀው መግለጫ “ይህንን ባሕሪ ለዓመታት ስንታገለው ነበር። የስፖርቱን አዎንታዊ ገፅታ ለማስተዋወቅ እየሠራን ነው። ሜዳ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳም ውጪም ቢሆን” ብሏል።

ቪኒየስ ጁኒየር
የምስሉ መግለጫ, ቪኒየስ ጁኒየር ከዳኛው ጋር ሲጨቃጨቅ

“አንድ ሙሉ ስታድየም ዘረኛ”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ብራዚላዊው የፊት መስመር ተጫዋች በተለይ በያዝነው የውድድር ዘመን በርካታ ጊዜ የዘረኝነት ጥቃት ሰላባ ሆኗል።

ትላንት እሁድ በነበረው ጨዋታ ቪኒ በሁለተኛው አጋማሽ ከደጋፊዎች በደረሰበት ጥቃት ምክንያት ግጥሚያ እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር።

ከዚህ በኋላ ደሙ እንደፈላ የሚያስታውቀው ቪኒ ከቫሌኒሲያው ተጫዋች ጋር በገባው እሰጥ አገባ ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀይ ካርድ ሰላባ የሆነው።

የሪያል ማድሪዱ አሠልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ቪኒ ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት ጨዋታው ሊቋረጥ ይገባ ነበር የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ጣሊያናዊው አሠልጣኝ “ዛሬ ያየነው ምንም ዓይነት ተቀባይነት የለውም። አንድ ሙሉ ስታድየም ዘረኛ ቃላት ሲሰነዝር ነበር” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።

“ዛሬ ስለእግር ኳስ ማውራት አልፈልግም። ለእኔ ቪኒሲየስ በዓለማችን ውዱ ተጫዋች ነው። ላ ሊጋው ችግር አለበት፤ እንዲህ ዓይነት ዘረኛ ጥቃቶች ሲኖሩ ጨዋታው መቆም አለበት።

“ሙሉ ስታድየሙ ነው ዘረኛ ቃል እያወጣ ሲዘፍን የነበረው። እኛ ጨዋታውን 3 ለ 0 ብናሸንፍ ኖሮም ይህን ነበር የምለው። ሌላ ምንም አማራጭ የለም።”

አንቼሎቲ አክለው የቪኒ ተግባር ከደረሰበት ጥቃት አንፃር “ልንረዳው” ይገባል ብለዋል።

“መጫወት መቀጠል ይሆን እንደሁ ጠየቅኩት። እሱ መቀጠል ፈለገ። ቪኒ በጣም ተናዷል፤ አዝኗል። በምንኖርባት ዓለም ይህን የመሰለ ነገር ሊኖር ባልተገባ ነበር።”

ላ ሊጋው የተፈጠረውን ነገር እንደሚመረምር ገልጿል። ቫሌንሲያ ደግሞ በድረ-ገፃቸው የተፈጠረውን ነገር አውግዘው ምርመራ እንደሚያደርጉ የሚያትት መግለጫ ለጥፈዋል።

የስፔን ላ ሊጋ መርምሮ ጥፋት የፈፀሙ ሰዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ያመቸው ዘንድ ሰዎች ያላቸውን ተንቃሳቃሽ ምስል እንዲያጋሩ ጠይቋል።

የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ የነበረው ሪዮ ፈርዲናንድ፣ ቪኒ ምን ያህል እርዳታ እየተደረገለት ነው ሲል በኢንስታግራም ገፁ ጠይቋል።

የሪያል ማድሪዱ ግብ ጠባቂ ቲቦ ኮርትዋ ጨዋታው ከጀመረ ከ20 ደቂቃዎች በኋላ “የዝንጀሮ ድምፅ” መስማቱን ገልጾ የቡድን አጋሮቹ ቢስማሙ ጨዋታውን ጥሎ ለመውጣት ዝግጁ እንደነበር ተናግሯል።

የብራዚል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኤድናልዶ ሮድርጌዝም የተፈጠረውን የዘረኝነት ጥቃት አውግዘዋል።

ጨዋታው ዲየጎ ሎፔዝ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በቫሌንሲያ 1 ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።