ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኬ፡ ሊዝ ትረስ በ45 ቀናቸው ስልጣን እንደሚለቁ አስታወቁ
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ሊዝ ትረስ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ አስታወቁ።
ሊዝ ትረስ ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በዳውኒንግ ስትሪት በሰጡት መግለጫ የተመረጥኩበትን ኃላፊነት መወጣት አልቻልኩም ብለዋል።
ከበርካታ ጋዜጠኞች ፊት ቀርበው መግለጫ የሰጡት ሊዝ ትረስ ወደ ስልጣን የመጣሁት “ከፍተኛ የምጣሄ ሃብት እና ዓለም አቀፍ አለመረጋጋት ባለበት ወቅት ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሯ የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት ለጠቅላይ ሚንስትርነት ቦታ ሲመርጧቸው፤ የሰጧቸውን ኃላፊነቶች መወጣት ባለመቻላቸው ስልጣን እንደሚለቁ አስታውቀዋል።
ተሰናባቿ ጠቅላይ ሚንስትር በአጭሩ ንግግራቸው፤ ወግ አጥባቂ ፓርቲያቸው የመረጣቸው ግብር እንዲቀንሱ እና የምጣሄ ሃብት እድገት እንዲያመጡ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ትረስ፡ “ወግ አጥባቂ ፓርቲ ለመረጠኝ ኃላፊነት መወጣት እንደማልችል ተረድቻለሁ” ብለዋል።
የወግ አጥባቂ ፓርቲ ተቀናቃኝ የሆነው የሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኬር ስታርመር እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የጠቅላይ ሚንስትሯን መሰናበት ተከትሎ አጠቃላይ ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።
ሊዝ ትራስ እርሳቸውን የሚተካ ፖለቲከኛ እስኪገኝ ድረስ በስልጣን ላይ እንደሚቆዩ ጨምረው የገለጹ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት የአመራር ምርጫ እንዲጀመር ከስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።
ሊዝ ትረስ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር በሆኑ በ45ኛ ቀናቸው ስልጣን መልቀቃቸው በአገሪቱ ታሪክ ለአጭር ጊዜ የመሩ ሰው ያደርጋቸዋል።
ሊዝ ትረስ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የዩኬ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ነበር።
ባለፉት ዓመታት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ሊዝ ትረስ፤ የወግ አጥባቂ መሪ ለመሆን ከቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ብርቱ ፉክክር ገጥሟቸው ነበር።
ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ሊዝ ትረስ በሰፊ የድምጽ ብልጫ ሪሺ ሱናክን በመብለጥ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ እንዲሆኑ በፓርቲው አባላት ተመርጠው ነበር።
ትረስ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የምጣሄ ሃብት ፖሊሲያቸው እጅጉን ሲያስተቻቸው ነበር።
ሊዝ ትረስ ማን ናቸው?
ሜሪ ኤልዛቤት ትረስ በሚለው ሙሉ የመዝገብ ስማቸው የሚታወቁት ፖለቲከኛዋ፣ ከሂሳብ ሊቁ አባታቸው እና ከነርስ እናታቸው እአአ 1975 በኦክስፎርድ፤ ኢንግላንድ ነበር የተወለዱት።
ሊዝ ትረስ በወጣትነት እድሜያቸው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፤ ፍልስፍና፣ ፖለቲካ እና ምጣሄ ሃብት አጥንተዋል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎን ያደርጉ ነበር።
አሁን ላይ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ይሁን እንጂ፤ ሊዝ ትረስ በተማሪነት ዘመናቸው ሊብራል ዴሞክራት ነበሩ። ሊዝ በፀረ ንጉሣዊ አስተዳደር ላይ በሚያንጸባርቁት ጠንካራ አቋም ይታወቁ ነበር።
ሊዝ ገና በኦክስፎርድ ሳሉ ነበር የፖለቲካ አቋም ለውጥ በማድረግ ፊታቸውን ወደ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ያዞሩት።
ሊዝ የፓርላማ አባል በሆኑ በሁለት ዓመታት ውስጥ የትምህርት ሚንስትር ሆነው ተሾሙ። ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ በእድገት የአካባቢ ጥበቃ ሚንስትር በመሆን ሌላ ሹመት አግኝተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ አስተዳደር ውስጥ የፍትሕ ሚኒስትር፣ ከዚያም ደግሞ የግምጃ ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
እአአ 2019 ላይ ቦሪስ ጆንሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ደግሞ ሊዝ ትረስ የዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር ሆነው ማገልገል ጀምረዋል።
ሊዝ የ46 ዓመት ጎልማሳ ሳሉ ነበር ትልቁን የመንግሥት ኃላፊነት የተረከቡት። እአአ 2021 ከዶሚኒክ ራብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥልጣንን ተረክበዋል።
የሊዝ ትረስ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያደረጉት ጉዞ አልጋ ባልጋ አልነበረም። ከተቀናቃኛቸው ሪሺ ሱናክ ጋር በነበሯቸው ክርክሮች ላይ ባቀረቧቸው መከራከሪያዎች ሲተቹ ነበር።
ይሁን እንጂ የምርጫ ውጤቱ ሊዝ ትረስ ከሪሺ ሱናክ ይልቅ በፓርቲ አባላት ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት እንዳላቸው አሳይቷል።