ዩክሬናውያንን እየገደለ ያለው የሰሜን ኮሪያ ጦር መሣሪያ እና አንድምታው

ያልተለመደው የሚሳኤል ስብርባሪ

ከጥቂት ወራት በፊት የዩክሬን ወጣቷ የጦር መሳሪያ መርማሪ ክርሰቲና ኪማቹክ ያልተለመደ ሚሳኤል በካርኪቭ ከተማ በሚገኝ ህንጻ ላይ ማረፉን ሰማች።

መረጃ ለማግኘት በሚል የዩክሬን ጦር አባላት ዘንድ መደወል ጀመረች። በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በዋና ከተማዋ ኪየቭ ውስጥ በሚገኝ ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ የሚሳኤሉን ስብርባሪ እንድታገኝ ሆነ።

ከጥፍሮቿ የሚያንሱትን የኮምፒዩተር ቺፖችን ጨምሮ ብሎኖች ለየብቻ መለየት እና እያንዳንዱን ክፍል ፎቶ ማንሳት ጀመረች። ይህ የሩስያ ሚሳኤል እንዳልሆነ ወዲያውኑ ማወቅ ችላለች። ቀሪው ጥያቄ ይህን ማረጋገጥ ነበር።

ለማጥቃት ከብረቶች እና ከተጠላለፉ ሽቦዎች መካከል የኮሪያ ፊደላት አገኘች። ተጨማሪ ጠቋሚ ዝርዝር ነገሮችንም አገኘች።

112 የሚል ቁጥርም ስብርባሪው ላይ ታትሟል። ይህ በሰሜን ኮሪያ አቆጣጠር የፈረንጆቹን 2023 የሚገልጽ ነው።

የሰሜን ኮሪያ መሣሪያ አገሯን ለማጥቃት ጥቅም ላይ መዋሉን ያረጋገጠችበትን የመጀመሪያውን ጠንካራ ማስረጃ እየተመለከተች እንደሆነ ተረዳች።

"አንዳንድ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ሩሲያ እንደላኩ ሰምተናል። ነገር ግን አይቼው፣ ነክቼው ወይም መርምሬው አላውቅም። ይህ በጣም አስደሳች ነገር ነው” ስትል ከኪዬቭ በስልክ ገልጻለች።

ከዚያን ወዲህ ብቻ በደርዘን የሚቆጠሩ የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሎችን ሩሲያ ወደ ግዛቱ መተኮሷን የዩክሬን ጦር ተናግሯል። ቢያንስ 24 ሰዎችን ገድለው ከ70 በላይ አቁስለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቅርቡ ኪም ጆንግ ኡን የኒውክሌር ጦርነት ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው የሚል መረጃ በስፋት ይደመጣል። ይበልጥ ስጋት የሆነው ደግሞ ሰሜን ኮሪያ አሁን ያሉትን ጦርነቶች ማቀጣጠል እና ዓለም አቀፋዊ አለመረጋጋትን እንዲቀጥል መሥራቷ ነው።

ኪማቹክ የኮንፍሊክት አርማሜንት ሪሰርች (ሲኤአር) አባል ናት። ተቋሙ በጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪያዎችን የሚመመረምር እና እንዴት እንደተመረቱ ለማወቅ ለማወቅ የሚሠራ ነው።

የሚሳኤሉን ቁርጥራጭ ፎቶግራፍ ማንሳት ከጨረሰች በኋላ እና ባልደረቦቿ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክፍሎቹን ከተተነተኑ በኋላ ነበር በጣም አስገራሚው ጉዳይ የመጣው።

በአዲስ የውጭ ቴክኖሎጂ የተሠራ ነበር። አብዛኛዎቹ የኤሌክትሮኒክስ ክፍሎቹ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ እና በአውሮፓ የተመረቱ ነበሩ።

መጋቢት 2023 የተሠራ የአሜሪካ ኮምፒዩተር ቺፕ አለበት። ይህ ማለት ሰሜን ኮሪያ በህገ-ወጥ መንገድ ወሳኝ የሆኑ የጦር መሣሪያ ክፍሎችን ገዝታ ወደ አገሯ እያስገባች፣ ሚሳኤሉን በድብቅ ወደ ሩሲያ ታጓጉዘች ማለት ነው።

በጥቂት ወራት ውስጥም መሣሪያው የጦር ግንባር ላይ ይውላል።

"ይህ በጣም የሚያስደንቀው ነገር ነው። ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ከባድ ማዕቀብ ቢጣልባትም ሰሜን ኮሪያ አሁንም የጦር መሳሪያዋን ለመሥራት የሚያስፈልጋትን ሁሉ በፍጥነት በእጇ ማስገባት እየቻለች ነው" ሲሉ የሲኤአር ምክትል ዳይሬክተር ዴሚየን ስፕሌተር ተናግረዋል።

የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ተቋም (ሩሲ) የሰሜን ኮሪያ ኤክስፐርት የሆኑት ጆሴፍ ባይርን በተመሳሳይ መደናገጣቸውን ገልጠዋል።

"ሰሜን ኮሪያ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች በአውሮፓ ምድር ሰዎችን ለመግደል ጥቅም ላይ ሲውሉ አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ኪም ወደ ሩሲያ አቅንተው የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲንን ካገኙበት ጊዜ አንስቶ የጦር መሳሪያ ስምምነት ስለመፈጸሙ ጥርጣሬ አለ።

ከዚያ ወዲህም ጆሴፍ እና የሩሲ ባልደረቦቻቸው የሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ወደ ሩሲያ ስለሚላክበት ሁኔታ ሲከታተሉ ቆይተዋል።

የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀምም በሰሜን ኮሪያ እና በሩሲያ ወታደራዊ ወደብ መካከል በመማለለስ የሚሠሩ አራት የሩሲያ የጭነት መርከቦች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኮንቴይነሮች ጭነው ሲጓዙ ለማየት ችለዋል።

እንደሩሲ ግምት ከሆነ ሰባት ሺህ ኮንቴይነሮች ተልከዋል። ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ጥይቶች እና ሮኬቶች ተላልፈው ተሰጥተዋል።

ግምገማቸው ከአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ደቡብ ኮሪያ በተገኘ የስለላ መረጃ የተደገፈ ቢሆንም ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ግን ውድቅ አድርገውታል።

"እነዚህ ጥይቶች እና ሮኬቶች ዛሬ በዓለም ላይ በጣም ከሚፈለጉ ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ሩሲያ የዩክሬን ከተሞችን እንድትታወድም አስችለዋታል።

ዩናይትድ ስቴትስ እና አውሮፓ ደግሞ ለኪዬቭ ምን አይነት መሣሪያ ማዋጣት እንዳለባቸው ለመወሰን የተጨነቁበት ወቅት ነው” ሲሉ ባይርን ተናግረዋል።

መግዛት እና መተኮስ

ባይርን እና ባልደረቦቻቸውን ያሳሰበው ከሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ መርሃ ግብር የተገኙ የባለስቲክ ሚሳኤሎች ወደ ጦር ሜዳ መግባታቸው ነው።

ሰሜን ኮሪያ እአአ ከ1980ዎቹ ጀምሮ የጦር መሳሪያዋን ለውጭ አገራት ሸጣለች።

በተለይም በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ እንደ ሊቢያ፣ ሶሪያ እና ኢራን አገራት ይጠቀሳሉ።

መሣሪያዎቹ ያረጁ እና የሶቪየት ዓይነት ሚሳኤሎች ከመሆናቸው ባለፈ መጥፎ ስምም ያላቸው ናቸው።

የሐማስ ተዋጊዎች ባለፈው መስከረም 26 በሰነዘሩት ጥቃት ወቅት አንዳንድ የፒዮንግያንግ አሮጌ ሮኬቶችን ተጠቅመው ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ አለ።

ኪማቹክ የተመለከተችው እና ጥር 2 ላይ የተተኮሰው ሚሳኤል ግን ፒዮንግያ ያመረተችው በጣም የተራቀቀው የአጭር ርቀት ሚሳኤሏ ህዋሶንግ 11 እንደሆነ የሚገመት እና እስከ 700 ኪሜ መጓዝ የሚችል ነው።

ምንም እንኳን ዩክሬናውያን ብቃታቸውን አቅልለው ቢናገሩም በሚድልበሪ የዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም የሰሜን ኮሪያ ጦር መሣሪያ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ጄፍሪ ሉዊስ ግን ከሩሲያ ሚሳኤሎች ብዙም የከፉ አይመስሉም ይላሉ።

የእነዚህ ሚሳኤሎች ጥቅም እጅግ በጣም ርካሽ መሆናቸው ነው ሲሉ ዶ/ር ሉዊስ አብራርተዋል።

ይህ ማለት ብዙ መግዛት እና የበለጠ ማጥቃት ይቻላል። በዚህም የአየር መከላከያዎችን የበላይነትን ለመያዝ የሚያግዝ ሲሆን ሩሲያም ይህንኑ ነው በትክክል እያደረገች የምትገኘው።

ቀጥሎ የሚነሳው እንግዲህ ሰሜን ኮሪያውያን ከእነዚህ ሚሳኤሎች ውስጥ ምን ያህሉ ማምረት ይችላሉ የሚለውን ጥያቄ ነው።

ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ 6 ሺህ 700 ኮንቴይነሮች ወደ ሩሲያ መላኳን የደቡብ ኮሪያ መንግስት ተመልክቷል።

የፒዮንግያንግ የጦር መሣሪያ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ እየሠሩ መሆኑ ተነግሯል። እነዚህን ፋብሪካዎች በሳተላይት ሲያጠኑ የነበሩት ዶ/ር ሉዊስ በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩትን ማምረት እንደሚችሉ ገምተዋል።

ስፕሌተርስ እና አጋሮቻቸው ኩባንያዎች ለሰሜን ኮሪያ ምንም እንዳይሸጡ ተከልክለው ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ እየሞከሩ ነው።

ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በአየር ላይ ተጉዘው የተቀመጠላቸውን ዒላማ እንዲመቱ የሚያግዙ አብዛኞቹ የኮምፒዩተር ቺፖች ስልኮቻችንን፣ ማጠቢያ ማሽኖችን እና መኪኖቻችንን ለማምረት የሚያገለግሉት ቺፖች ናቸው ይላሉ ስፕሌተር።

እነዚህ ደግሞ በዓለም ዙሪያ በሚያስደንቅ ሁኔታ ይቸበቸባሉ። አምራቾች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ቺፖች በችርቻሮ ለሚሸጡ ለአከፋፋዮች ይሸጣሉ። ይህም ማለት አምራቾቹ ብዙውን ጊዜ ምርቶቻቸው የት እንደሚደርሱ አያውቁትም።

የሚሳኤሉ ምን ያህል አካላት ከምዕራቡ ዓለም እንደመጡ ማወቁ ባይርን አበሳጭቷል። የሰሜን ኮሪያ የግዢ ኔትወርኮች እሳቸው ከተገነዘቡት በላይ ጠንካራ እና ውጤታማ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ካላቸው ልምድ በመነሳት በባህር ማዶ የሚኖሩ ሰሜን ኮሪያውያን በሆንግ ኮንግ ወይም በሌሎች የመካከለኛው እስያ ሀገራት እቃዎቹን በብዛት የተዘረፈ ገንዘብ ለመግዛት የሚያስችላቸው ኩባንያዎችን አቋቁመዋል።

ከዚያም ምርቶቹን ወደ ሰሜን ኮሪያ ይልካሉ። ብዙውን ጊዜ የሚልኩትም ከቻይና ጋር ባለው ድንበር በኩል ነው። ኩባንያ ከታወቀ እና ማዕቀብ ከተጣለበት ሌላ ኩባንያ በፍጥነት በእሱ ቦታ ተቋቁሞ ብቅ ይላል።

ማዕቀብ እነዚህን መረቦች ለመዋጋት ፍጹምና እንከን የሌለው መሣሪያ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

ሆኖም ግን በየጊዜው መዘመን እና መተግበር አለባቸው። ሩሲያ እና ቻይና ከ 2017 ወዲህ ሰሜን ኮሪያ ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ሞስኮ የፒዮንግያንግ የጦር መሳሪያ በመግዛት በአንድ ወቅት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሆና የደገፈችውን ማዕቀብ እየጣሰች ነው።

ከወራት በፊት ደግሞ የማዕቀብ ጥሰቶችን የሚከታተለውን የተባበሩት መንግስታት ቡድን በትናለች። ይህም የሚገጥማትን ምርመራን ለማስቀረት ሊሆን ይችላል ተብሎ ተገምቷል።

“ለፒዮንግያንግ ብዙ ዕድል የሚሰጣትን በሰሜን ኮሪያ ላይ የተባበሩት መንግስታት የጣለው ማዕቀብ በቅጽበት እየፈራረሰ መሆኑን እያየን ነው" ሲሉ ባይርን ተናግረዋል።

ይህ ሁሉ በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ካለው ጦርነት በላይ የሚደርስ አንድምታ አለው።

“ከዚህ እውነተኛ አሸናፊ የሆኑት ሰሜን ኮሪያውያን ናቸው። ሩሲያውያንን ጉልህ በሆነ መንገድ ረድተዋቸዋል" ብለዋል።

እንደ ሩሲ ከሆነ በመጋቢት ወር ከፍተኛ መጠን ያለው ዘይት ከሩሲያ ወደ ሰሜን ኮሪያ ተጓጉዟል። በሩዝ እና ዱቄት የተሞሉ ባቡሮችም የአገራቱን ድንበር ሲያቋርጡ ታይቷል።

ይህ ስምምነት በመቶ ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት ሲሆን የፒዮንግያንግ ኢኮኖሚን ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ ኃይሏንም ያሳድጋል።

ፒዮንግያንግ ሚሳኤሏን መሥራቷን እንድትቀጥል ጥሬ ዕቃውን ሩስያ ልትሰጣት ትችላለች። እንደ ተዋጊ ጄት ያሉ ወታደራዊ መሣሪያዎችን ወይንም ደግሞ አርቆ ከታየ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዋን ለማሻሻል የቴክኒክ ድጋፍ ከሞስኮ ልታገኝ ትችላለች።

ሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሎቿን በእውነተኛ ጦርነት ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሞከርም ዕድሉን እያገኘች ነው። ከዚህ የተገኘው መረጃ የተሻለ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ፒዮንግያንግ፡ ዋናዋ ሚሳኤል አቅራቢ?

የበለጠ አሳሳቢ የሆነው ነገር ጦርነቱ ሰሜን ኮሪያን ለተቀረው ዓለም የንግድ በር እየከፈተ መሆኑ ነው።

ፒዮንግያንግ እነዚህን የጦር መሳሪያዎች በብዛት እያመረተች በመሆኗ ለተጨማሪ አገራትም መሸጥ ትፈልጋለች።

ሩሲያ ማዕቀብ መጣስ ምንም እንዳልሆነ በማሳየቷ ሚሳኤሎቹ ለሞስኮ ጥሩ ከሆኑ ለሌሎችም ይፈለጋሉ ብለዋል ዶ/ር ሉዊስ።

በቻይና-ሩሲያ-ኢራን ቡድን ውስጥ ሰሜን ኮሪያ ትልቅ ሚሳኤል አቅራቢ እንደምትሆንም ተንብየዋል።

በዚህ ወር ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ ከኢራን ጋር በኒውክሌር እና ባለስቲክ የጦር መሳሪያ መርሃ ግብሯ ላይ ልትሠራ ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላት አሜሪካ ተናግራለች።

"ስለዚህ ችግር ስንነጋገር ብዙ የጨለሙ ፊቶች አይቻለሁ። ጥሩ ዜናው ግን በውጭ ቴክኖሎጂ ላይ ምን ያህል ጥገኛ እንደሆኑ ስለምናውቅ አንድ ነገር ማድረግ እንችላለን” ብለዋል ስፕሌተር።

ከአምራቾች ጋር በመተባበር የሰሜን ኮሪያን የአቅርቦት ሰንሰለት መቁረጥ ይቻላል የሚል ተስፋም አላቸው። ቡድናቸው አስቀድሞ በመለየት እና ወሳኝ ሽያጭ ከማጠናቀቁ በፊት ህገ-ወጥ መረብን ማዘጋት ችሏል።

ዶ/ር ሉዊስ ግን እርግጠኛ አይደሉም።

“የበለጠ አስቸጋሪ፣ የበለጠ የማይመች ምናልባትም ወጪውን ከፍ ልናደርግ ብንችልም አንዳቸውም ግን ሰሜን ኮሪያ እነዚህን መሣሪያዎች እንዳትሠራ የሚከለክል አይደለም” ብለዋል።

ሚሳኤሎቹ የክብር እና የፖለቲካ ሃይል ምንጭ ብቻ ሳይሆኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እያፈሩትበትም ጭምር ነው ብለዋል ዶ/ር ሌዊስ። ታዲያ ለምን ኪም ጆንግ ኡን አሳልፎ ይሰጣቸዋል?