ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በሐማስ መሪ ላይ የእስር ማዘዣ ሊወጣባቸው ነው
የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ዋና ዐቃቤ ሕግ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በጋዛ የሐማሱ መሪ ፈጽመዋቸዋል ባሏቸው የጦር ወንጀሎች የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ማመልከቻ አቀረቡ።
ዋና ዐቃቤ ሕጉ ካሪም ኻን ሁለቱ ተከሳሾች ከመስከረም ወር ማብቂያ ጀምሮ ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ ለተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂ መሆናቸውን ለማመን የሚያስችል ምክንያታዊ መሠረት አለ ብለዋል።
ዋና ዐቃቤ ሕጉ የእስር ማዘዣ የጠየቁባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና በጋዛ የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር እየተካሄደ ባለው ጦርነት በፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ ናቸው በሚል ነው።
የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት እና የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያህ እንዲሁም የሐማስ ወታደራዊ መሪ ኦሐመድ ዴይፍ ከተፈላጊዎቹ መካከል ናቸው።
መቀመጫው ዘ ሄግ የሆነው ዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ባለፉት ሦስት ዓመታት እስራኤል በወረራ በያዘቻቸው ግዛቶች ውስጥ የምትወስደውን እርምጃ ሲመረምር የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ የሐማስን ድርጊቶችንም እየመረመረ ነው።
የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአይሲሲ የተፈላጊዎች ዝርዝር ውስጥ የመካተታቸውን ሃሳብ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ “በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ” በማለት ቁጣቸውን ገልጸው ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ፖለቲካዊ ተቀናቃኝ የሆኑት እና የአገሪቱ የጦር ካቢኔ አባል የሆኑት ቤኒ ጋንትዝ፣ የዐቃቤ ሕጉን ውሳኔ አውግዘውታል።
ጋንትዝ “አገራቸውን ከአስከፊ ሽብር ለመከላከል የቆረጡ የአንድ ዲሞክራቲክ አገር መሪዎችን ደም ከጠማው የሽብር ቡድን መሪዎች ጋር እኩል መመልከት ጥልቅ የፍትህ መዛባት እና ከባድ የሞራል ክስረት ነው” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ተቃውመዋል።
በዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስር ማዘዣ ለማውጣት ዐቃቤ ሕግ ጥያቄውን አቅርቦ ዳኞች ውሳኔ ለመስጠት ሳምንታት ወይም ወራት ሊያስፈልግ ይችላል።
የፍርድ ቤቱን ዋና ዐቃ ሕግ ውሳኔን ተከትሎ የእስራኤል ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ወዳጅ አገሮች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ፣ ሌሎች አገራት እና ታዋቂ ሰዎች እርምጃውን ደግፈውታል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት እርምጃን የሚቃወም እና የሚከታተል ልዩ የዕዝ ማዕከል እንደሚቋቋም አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረውም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እስራኤል እራሷን የመከላከል መብቷን እንዳትጠቀም እጇን ለማሰር የታሰበ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ውሳኔው በሐማስ ጥቃት ሰለባዎች ላይ የተፈጸመ “ቀጥተኛ ጥቃት ነው” ያሉት ሚኒስትሩ “ይህም ለዘላለም ሲታወስ የሚኖር ታሪካዊ አሳፋሪ እርምጃ ነው” በማለት “በዓለም ላይ የትኛውም ኃይል” እስራኤል ታጋቾችን ከማስለቀቅ እና ሐማስን ከመደምሰስ አያስቆማትም ብለዋል።
ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከገደለ እና አግቶ ወደ ጋዛ ከወሰደ በኋላ እስራኤል እያካሄደችው ባለው ከባድ ወታደራዊ ዘመቻ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
ይህም በእስራኤል ላይ ከባድ ትችትን ያስከተለባት ከመሆኑ በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በአገሪቱ ላይ ክስ እንድትመሠርት አድርጓታል።
ተቃውሞ እና ትችት ቢቀርብባታም እስራኤል ሐማስን በማጥፋት የታገቱባትን ዜጎቿን ሳታስለቅቅ ወታደራዊ ዘመቻዋን እንዳማተቆም ገልጻለች።