ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አይሻ መሃመድ ድጋሚ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት በመከላከያ ሚኒስትርነት ተሹመው ለመንፈቅ ያህል ያገለገሉት አይሻ መሃመድ ድጋሚ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።
አይሻ መሃመድ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን አብርሃም በላይን (ዶ/ር) እንደሚተኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ ግንቦት 12/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
አብርሃም በላይ አይሻ ሲያገለግሉበት በነበረው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው እንደሚተኳቸውም መግለጫው አመልክቷል።
አይሻ መሃመድ የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ጥቅምት 6/2011 ዓ.ም. ቢሾሙም ያገለገሉት ለስድስት ወራት ብቻ ነው።
አይሻ የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙበት ወቅት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ በሹመታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው ነበር፥
“ለኢትዮጵያ ሴቶች ክብር ነው፣ እኔ ለተወለድኩበት አካባቢ ክብር ነው፣ ለግሌም ክብር ነው። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ትልቅ ግዙፍ እና ታሪካዊ ኃይል ከመምራት በላይ ክብር የለም” ብለው ነበር። ብለዋል።
መከላከያ ተቋሙንስ እንዴት ይመሩት ይሆን ተብለው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በዋናነት የአገራችንን ውስጣዊ ሰላም ማስጠበቅ አለብን። የምታሰባስበን፣ የማንነታችን መገለጫ ኢትዮጵያ እስከሆነች ድረስ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አድርገን ማቆየት የምንችለው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት በአገራችን ሲኖር ነው።
“ነገር ግን በርካታ ልናስባቸው የሚገቡ ስጋቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አምናለሁ። በተቻለ መጠን በዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት እና በሰላም አሁን እንደጀመርነው ከጎረቤቶቻችን ጋር መኖር መቻል አለብን” ብለው ነበር።
አይሻ መሃመድ በመከላከያ ሚኒስቴር ከወራት ግልጋሎት በኋላ ቀድሞ ወደ ነበሩበት የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተመልሰው ነበር።
በዚያም ከሚያዝያ 10/2011 እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. ድረስ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ከሁለት ዓመት ዘጠኝ ወራት በፊት አዲስ ካቢኔ ሲዋቀር አይሻ መሃመድ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል ። አይሻ ለሁለት ዓመት ገደማ ይዘውት ቆዩትን የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርነት ቦታ ያስረከቡት ለጫልቱ ሳኢ ነው።
አይሻ ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ከመምጣታቸው በፊት የኮንስትራክሽን ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፤ ወደ ፌደራል ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በአፋር ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የአደጋ መከላከል ቢሮ አመራር ነበሩ።
በአፋር ክልል በተለለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን፤ በ2008 ዓ.ም. በተደረገው የመንግሥት ምደባ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር በመሆን ሠርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በመከላከያ ሚኒስቴር ለስድስት ጊዜያት ያህል ሹም ሽሮች ተካሂዶበታል።
ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ካቢኔያቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዋቅሩ አቶ ሞቱማ መቃሳን የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸዋል። አቶ ሞቶማ በመከላከያ ሚኒስትርነት የቆዩት ለስድስት ወራት ያህል ብቻ ነበር።
ከስድስት ወራት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አይሻ መሃመድን የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው ሹመዋል። እንደ አቶ ሞቱማ ሁሉ አይሻ መሃመድም በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ የቆዩት ለመንፈቅ ያህል ብቻ ነው።
አይሻ መሃመድ ኃላፊነታቸውን “የለውጡ” አካል ለነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ያስረከቡት በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. ነበር። አቶ ለማ በመከላከያ ሚኒስትርነት ለአንድ ዓመት ከአራት ወር ከቆዩ በኋላ ቦታውን ለዶ/ር ቀነዓ ያደታ አስረክበዋል።
አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ቀነዓ የመከላከያ ሚኒስቴርን ለአንድ ዓመት ያህል መርተዋል። ዶ/ር ቀነዓ ኃላፊነታቸውን ያስረከቡት ዛሬ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው ለተሾሙት ዶ/ር አብርሃም በላይ ነው።
ዶ/ር አብርሃም ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ዛሬ ከሥልጣን እስከ ተነሱበት ዕለት ድረስ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት ሹመት መሃመድ እንድሪስን (ዶ/ር) በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሹመዋል።
ዶ/ር መሃመድ እንድሪስ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክትር ሆነው እያገለገሉ ነበር። ዶ/ር መሐመድ የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው።