ያለስልክ ግንኙነት ለ10 ሰዓታት በምስጢር በባቡር የተጓዙት ጆ ባይደን

አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንዲህ ያለው ድፍረት የተሞላበት ምስጢራዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያው ይመስላል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በተደጋጋሚ ጥቃት የሚፈፀምበት የጦርነት ቀጣና ውስጥ መገኘት እጅግ ያልተጠበቀ ነው።

ዋይት ሐውስ ባይደን ወደ ኪዬቭ ያደረጉትን ጉብኝት “በዘመናዊው ዓለም ያልተጠበቀ” ሲሉ ገልጾታል።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በጦርነት ሲታመሱ የነበሩትን ኢራቅን እና አፍጋኒስታንን ሲጎበኙ በከባድ ጦር ሠራዊት ታጅበው ነው።

ምንም እንኳ ጆ ባይደን በፖላንድ አድርገው ወደ ዩክሬን ሊያቀኑ ይችላሉ የሚሉ ጭምጭምታዎች ቢኖሩም የፕሬዝዳንቱ ድንገት ኪዬቭ መገኘት ብዙዎችን ያስገረመ ነበር።

ፕሬዝደንት ባይደን ፖላንድ ተገኝተው ለዩክሬን ያላቸውን ድጋፍ ከሚገልጹ ይልቅ ወደ ዋና ከተማዋ ኪዬቭ አቅንተው፣ ከፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር አንድ ላይ ቆመው የሚነሱት ፎቶ የተሻለ መልዕክት ይኖረዋል።

የዋይት ሐዋስ ቃል አቀባይ ኬት ቤዲንግፊልድ “አደጋ የነበረው፣ ነገር ግን ጆ ባይደን ቁርጠኛ መሪ መሆናቸውን የሚያሳይ እርምጃ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ስልክ መያዝ አይቻልም”

ባይደን ለሁለት ቀናት ጉብኝት ከአሜሪካ ወደ ፖላንድ ዋርሶው ሰኞ አመሻሹን እንደሚበሩ ነው የተያዘላቸው መረሃ ግብር የሚያሳየው።

ቀድሞ የወጣው የጊዜ ሰሌዳቸው ሁለት ረዘምረ ያሉ እና አጠራጣሪ ክፍት ጊዜዎች ይታዩበታል። ብዙዎች በዚህ ቀዳዳ ወደ ዩክሬን አቅንተው ሊመለሱ ይችላሉ ሲሉ ገምተዋል።

በየቀኑ የሚካሄደው የዋይት ሐውስ ጋዜጣዊ መግለጫ በመሰል ጥያቄዎች የተሞላ ነው፤ ፕሬዝዳንቱ ወደ ዩክሬን ያቀናሉ ወይ?

ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ከዜሌንስኪ ጋር ለመገናኘት ዕቅድ እንደሌላቸው እና ከዋርሶው ውጭ እንደማይሄዱ ለጋዜጠኞች ተነግሯቸዋል።

ምንም እንኳ የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ አማካሪዎች ይህን ለወራት ሲወጥኑት ቢቆዩም፣ ፕሬዝዳንት ባይደን ከፕሬዝደንት ዜሌንስኪ እንደሚገናኙ አርብ ማታ ነው የታወቀው።

እሑድ ዕለት የተለቀቀው የዋይት ሐውስ ይፋዊ የፕሬዝዳንቱ መረሃ ግብር እንደሚጠቁመው ፕሬዝዳንት ባይደን ሰኞ ምሽት 1፡00 ወደ ዋርሶው ያቀናሉ።

ቢሆንም ኤይር ፎርስ ዋን የተሰኘችው አውሮፕላን እሑድ ንጋት 10፡15 በረራዋን አደረገች።

በውስጧ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ አማካሪዎችን፣ የሕክምና ባለሙያዎችን እና የደኅንነት ባለሙያዎችን ይዛለች።

ከፕሬዝዳንቱ ጋር ወደ ፖላንድ እንዲያቀኑ የተፈቀደላቸው ሁለት ጋዜጠኞች ብቻ ናቸው። ስለ ፕሬዝዳንቱ ጉዞ ትንፍሽ እንዳይሉ ቃል እንዲገቡ ተደርገው “ስልክ መያዝ አይቻልም” ተብለው ተንጠቀዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ወደ ዩክሬን እንደሚያቀኑ መናገር የሚችሉት ባይደንበ ኪዬቭ ከገቡ በኋላ ብቻ እንደሆነም ተስማምተዋል።

የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን እንደሚሉት ሩሲያ ስለጉብኝቱ የተነገራት ከጉብኝቱ ጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ ነው።

“ምን እንደተባባልን ባልገልጽላችሁን፤ እኛ አስቀድመን መረጃውን እንዳደረስን ግን ልንግራችሁ እችላለሁ” ብለዋል አማካሪው።

ጠጣር መልዕክት

ፕሬዝዳንት ባይደን ኪዬቭ ለመድረስ የ10 ሰዓታት የባቡር ጉዞ ማድረግ ነበረባቸው።

ዩክሬን ውስጥ ያሉ ሌሎች ሥፍራዎችን መጎብኘት ይቀላቸው የነበረ ቢሆንም፣ ወደ ዋና ከተማ ኪዬቭ ማቅናት የመረጡት መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።

የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ለሩሲያ ያለው መልዕክት አሜሪካ ከዩክሬን ጎን እንደምትቆም ከመሆኑ ባለፈ፣ አገር ቤት ላሉ አሜሪካውያንም መልዕክት አለው።

የባይደን ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ዣን-ፒዬር ባለፈው ሳምንት አሜሪካውያን ለዩክሬን ያላቸው ድጋፍ እየቀነሰ መጥቷል ወይ? ተብለው ተጠይቀው ነበር።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ፕሬዝዳንት ባይደን መልዕክት ሲያስተላልፉ ለአሜሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብም ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ሰኞ ዕለት ወደ ኪዬቭ ያደረጉት ጉብኝት ያለው መልዕክት አገር ቤት ላሉ አሜሪካ እስመቼ ድረስ ዩክሬንን ትደግፋለች የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ ሪፐብሊካን ነው ሲሉ አክለዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ወደ ፖላንድ ያቀኑት ኤይር ፎርስ ዋን በተሰኘችው ፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላን ሳይሆን ስሟ ባልታወቀ ሌላ አውሮፕላን ተሳፍረው ነው።