ፕሬዚዳንት ባይደን አሜሪካ እስከ መጨረሻው ከዩክሬን ጎን ትቆማለች አሉ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ባልተጠበቀ ጉብኝታቸው አገራቸው እስከ መጨረሻው ከዩክሬን ጎን እንደምትቆም ተናገሩ።

አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ጦርነት “ምንም ያህል ጊዜ ቢፈጅም” ለዩክሬን ያላሰለሰ ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉም ፕሬዚዳንት ባይደን በኪዬቭ ጉብኝታቸው አስታውቀዋል።

“ዩክሬን እንደምታሸንፍ ሙሉ እምነት አለንም” ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የፕሬዚዳንት ባይደን ጉብኝት አንድ አመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የመጀመሪያው ነው።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ዩክሬን እና ምዕራባውያን አጋሮቿን ታሸንፋለች ብለው ማሰባቸው “ፍጹም ስህተት ነው” ሲሉም አስረግጠዋል።

ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጋርም ተገናኝተው ክሬሚያ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ በነበሩት ዘጠኝ ዓመታት የሞቱትን ወታደሮች መታሰቢያ ጎብኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ባይን ወደ ዩክሬን ያቀኑት አሜሪካ “ለዩክሬን ዲሞክራሲ፣ ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት” ለማረጋገጥም እንደሆነም ዋይት ሃውስ ባወጣው መግለጫ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከፖላንድ ወደ ዩክሬን መዲና ኪዬቭ አስር ሰዓታት የፈጀ የባቡር ጉዞ ያደረጉ ሲሆን ምስጢራዊም ነው ተብሏል።

ግጭት ለማብረድ በሚል ከፕሬዚዳንቱ ጉዞ ጥቂት ሰዓታት በፊት ለሩሲያ እንደተነገራትም የአሜሪካ ባለስልጣን ተናግረዋል።

ከዩክሬን ጉብኝታቸው በኋላም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለዩክሬን አዲስ የጸጥታና ደህንነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

በዚህም 450 ሚሊዮን ዶላር ለሚሳይሎች፣ ለአየር ክትትል ራዳሮችና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት ይውላል ተብሏል።

የዩክሬን የኃይል መሰረተ ልማትን ለመጠበቅ ተጨማሪ የ10 ሚሊዮን ተጨማሪ እርዳታ እንደሚሰጥ ብሊንከን ተናግረዋል።

ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ክምችት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድጋፍ በሚያደርጉ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ላይ አዲስ የማዕቀብ ዝርዝርም በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይም ይፋ ይሆናል።

ዩክሬን በሩሲያ ላይ የተቀናጀችው ድል በቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የገለጹት ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ይህንንም በዋነኝነት በፕሬዚዳንት ባይደን ላይ አይቻለሁ ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል።

“በመርህና ሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተው የዓለም ስርዓት ዕጣ ፈንታ የሚታየውና የሚወሰነው በዩክሬን አሁን ነው” ብለዋል።