ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቱርክ በተከሰተው አዲስ ርዕደ መሬት በርካቶች በፍርስራሾች ውስጥ እንደሚገኙ ተነገረ
በቱርክ በሁለት ቦታዎች በተከሰተና ቢያንስ ለሶስት ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው አዲስ የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ በፍርስራሾች ውስጥ የቀሩ ሰዎችን ለመታደግ የነፍስ አድን ሰራተኞች እየተረባረቡ ነው።
በደቡባዊ ምስራቅ ቱርክ እና ሶሪያ በሚዋሰኑበት አከባቢ የተከሰተውና በመሬት መንቀጥቅጥ መለኪያ 6.4 እና 5.8 የሆነው ርዕደ መሬት በሳምንታት ልዩነት ውስጥ በሀገራቱ ሲከሰት ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ቀደም ብሎ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሁለቱ ሀገራት 44 ሺህ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ቤት አልባ እንዲሆኑ አደርጓል።
ትላንት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሁለቱም ሀገራት ህንጻዎች ተደርምሰዋል።
የቱርክ የአደጋና ደንገተኛ ጉዳዮች ኤጀንሲ በመሬት መንቀጥቅጥ መለኪያ 6.4 እና 5.8 ሆኖ የተመዘገበው ርዕደ መሬት በሰዓታት ልዩነት መፈጠሩን ገልጸዋል።
የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ሱሌይማን ሶልዩ መሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተበት አንታካያ፣ ዴፍኔና ስማንዳግ ላይ ሶስት ሰዎች መመሞታቸውን የገለጹ ሲሆን ሰዎች ከፍተኛ አደጋ ወደ ተጋረጠባቸው ህንጻዎች እንዳይገቡ አሳስበዋል።
ሚኒስትሩ 213 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል።
በአንታካያ ከተማ በርዕደ መሬቱ ክፉኛ የተጎዱ አከባቢዎችን አምቡላንሶችና የነፍስ አድን ሰራተኞች የተሰማሩ ሲሆን ነዋሪዎች በፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የአከባቢው ነዋሪ የሆነችው ሙና አልኦማር የ7 ዓመት ልጇን ይዛ እያለቀሰች “በእግሬ ስር ያለችው መሬት የምትሰነጠቅ መስሎኝ ነበር ” ስትል ለሮይተርስ ተናግራለች።
አሊ ማዝሉም የተባለ የ18 ዓመት ወጣት ልጅ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገረው ሁለተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት በመጀመሪያው ርዕደ መሬት ያጣችው ቤተሰቦች አስክሬን ሲፈልግ መከሰቱን ተናግረዋል።
“ምን ማድረግ እንዳለብህ አታውቅም. . . የህንጻው ግርግዳ ከፊት ለፊታችን ሲፈርስ አስቁመነዋል” ሲሉም አክለዋል።
በሶሪያ ትላንት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የተገዱ 470 ሰዎች ወደ ሆስፒታል መግባታቸው ተገልጿል። አዲሱ ርዕደ መሬት ግብጽና ሊባኖስ ድረስ እንደተሰማም ተገልጻል።