ተጽዕኖ ፈጣሪው የሱዳን ጄነራል መፈንቅለ መንግሥቱ ስህተት ነበር አሉ

የሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሌፍተናንት ጄነራል ሐምዳን ዳጋሎ እአአ 2021 ላይ የተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ‘ስህተት’ ነበረ አሉ።

ሔምቲ በሚለው መጠሪያ ስማቸው በስፋት የሚታወቁት ሞሐመድ ዳጋሎ፤ ለመፈንቅለ መንግሥቱ ድጋፍ ማድረጋቸው ከፈጸሟቸው ስህተቶች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ዳጋሎ መፈንቅለ መንግሥቱ ለቀድሞ ስርዓት አስተዳደር ‘ርዝራዦች ማምለጫ’ ሆኗል ብለዋል።

ሔምቲ የተሳተፉበት መፈንቅለ መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመሩትን መንግሥት ከስልጣን አውድርዷል።

ሲቪል መንግሥትን ሲመሩ የነበሩት አብደላ ሐምዶክ ወደ ስልጣን የመጡት የሱዳን የረዥም ግዜ መሪ ኦማር አል-በሺር በሕዝባዊ ተቃውሞ ስልጣን ለመልቀቅ ከተገደዱ በኋላ ነው።

ከአል-በሽር ከስልጣን መወገድ በኋላ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሱዳን የአገሪቱ ጦር ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር አሳልፎ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ቆይቷል።

ይህንን ተከትሎ ከጥቂት ወራት በፊት ወታደራዊው ሉዓላዊ ምክር ቤት ስልጣን ለሲቪል አስተዳደር አስተላልፋለሁ ብሎ ነበር።

ሞሐመድ ዳጋሎ ጦሩ ስልጣን ለሲቪል አስተዳደር አስተላልፋለሁ ማለቱ የሚወደስ መሆኑን ገልጸው፤ በአገሪቱ የደኅንነት ሪፎርሞች እንደሚካሄዱ እንዲሁም እርሳቸው የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ወደ አገሪቱ ጦር እንደሚቀላቅሉም ተናግረዋል።

ጀኔራል ዳጋሎ በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ባለችው ሱዳን ከጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን በመቀጠል ቁልፍ ሰው ሲሆኑ ከጀርባቸው ባሰለፉት ወታደራዊ ኃይልም በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሰው ናቸው።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሚሊሻን የሚመሩት ሔምቲ የቀድሞው መሪ አል ባሽር የቅርብ አጋር ነበሩ።

የሚመሩት ኃይልም በአገሪቱ ምዕራብ ክፍል ውስጥ በሚገኘው የዳርፉር አካባቢ ተፈጽመዋል በተባሉ ከባድ ጭፍጨፋዎች ሲከሰስ ቆይቷል።

በዚህ ብቻም አይደለም ካርቱም ውስጥ በተካሄዱት ግድያዎች እጃቸው አለበት የሚሉ ወገኖች በርካቶች ናቸው።

ሄሜቲ የዳርፉሩን ጭፍጨፋ በተመለከተ "እርምጃው ንዑሃንን ለመጠበቅ ሲባል አስፈላጊ ነበር" ሲሉ በአንድ ወቅት ምላሽ ሰጥተው ነበር።

ከግመል ነጋዴነት ወደ ጦር መስፍንነት

ሄሜቲ ከቻዳዊ የዐረብ ጎሣ ነው የተወለዱት።

ጦርነትን በመሸሽ በ1980ዎቹ በዳርፉር መኖር ጀመሩ። እ.አ.አ 2003 ላይ በዳርፉር ጦርነት ተቀሰቀሰ። መብታችን ተረግጧል የሚሉ ጥቁር ነዋሪዎች አማፂ ቡድንን ፈጠሩ። የመንግሥት ወታደርም ጃንጃዊድ ከሚባለው ቡድን ጋር በመሆን ጥቃት ፈፀመ። በዚህም ግመል የሚያረቡ ሰዎች ተገደሉ፣ ሴቶች ተደፈሩ፣ ያገኙትንም ንብረት ዘረፉ።

ከ2005 ጀምሮም ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የዘር ፍጅት እና በንፁሃን ላይ በተከፈተ የጦር ወንጀል ጥናት አድርጓል። በዚህም በርካታ የሱዳን ባለሥልጣናት፣ የጃንጂዊድ እና የአማፂ ቡድኑ ጥፋተኛ ተብለዋል።

በሱዳንና ቻድ ድንበር ያለውን አካባቢ ከተቆጣጠሩት የዐረብ ጎሣዎች መካከል የሄሜቲ አጎት ጁማ ዶንጎሎ ዋናው ናቸው። ሄሜቲ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው የግመል ንግድ ይሠሩ የነበር ሲሆን በዳርፉር ጦርነት ወቅትም ለተዋጊዎች ግመል ያከራዩ ነበር። በዚህ ሥራቸው የንግድ ሰው እና ባለፀጋ መሆንም ችለዋል።

በ2003 የዳርፉር አማፂያን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሄሜቲ ዘላኖችን በማደራጀት መንግሥትን እንዲያግዙ አድርገዋል። ከዓመት በኋላ ደግሞ ይህ ቡድን መደበኛ ወታደር መሆኑን መንግሥት ይፋ አደረገ። በዚህም ሄሜቲ በፕሬዝዳንት አል በሽር ድጋፍ አገኙ። ወዲያውም ዳርፉር አካባቢ ለሚገኘው የድንበር ጠባቂ ጦር መሪ ሆነው ተመረጡ።

በ2013 መደበኛ ሠራዊቱን ለማገዝ "ፈጥኖ ደራሽ ኃይል" ተቋቋመ። ከዓመት በኋላ ደግሞ ቡድኑ መደበኛ ሠራዊት እንዲሆን በመንግሥት እውቅና ተሰጠው። ተንታኞች እንደሚሉት ግን ጃንጂዊድን እንደገና ማቋቋም ነው።