ሃላንድና ምባፔ በፒኤስጂ ማሊያ አንድ ላይ ሲጫወቱ እናያቸው ይሆን?

ሰን የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው የኤቨርተኑ ግብ ጠባቂ ወደ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ሊያቀና ይችላል።

የ29 ዓመቱ እንግሊዛዊ ግብ ጠባቂ በቅርቡ ረዘም ያለ ፊርማ ለኤቨርተን መፈረሙ ይታወሳል።

ቶተንሃም የኤቨርተኑን ግብ ጠባቂ ማምጣት ካልቻለ አርጀንቲናዊው ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝን ሊያስፈርም ይችላል ሲል ጋዜጣው ፅፏል።

አርአምሲ ስፖርት የተሰኘው ጋዜጣ ደግሞ የፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ኧርሊንግ ሃላንድን ሊያስፈርም ይሻል ሲል አስነብቧል።

ፒኤስጂ፤ የ22 ዓመቱን ኖርዌያዊ አጥቂ ከማንችስተር ሲቲ በማስመጣት ከኪሊያን ምባፔ ጋር ሊያጣምራቸው አስቧል ይላል ጋዜጣው።

ነገር ግን ምባፔ አሁንም ወደ ስፔን በማቅናት ለሪያል ማድሪድ መጫወት እንደሚፈልግ ማርካ ዘግቧል።

እንደ ማርካ ዘገባ የምባፔ ወኪሎች ተጫዋቹ ለፒኤስጂ አዲስ ፊርማ በማሳረፉ እንደሚቆጭ ይናገራሉ ይላል።

ቼልሲ በሚመጣው ክረምት ኔዘርላንዳዊው የባርሴሎና አማካይ ፍራንኪ ዲ ዮንግን ማስፈረም ተቀዳመ ዓላማው ነው ሲል የዘገበው ፉትቦል ኢንሳይደር ነው።

በሌላ በኩል ከአትሌቲኮ ማድሪድ በውሰት መጥቶ ለቼልሲ እየተጫወተ ያለው የ23 ዓመቱ ፓርቹጋላዊ ጃዎ ፌሊክስ በሰማያዊዎቹ ቤት ደስተኛ መሆኑን ሬሌቮ ዘግቧል።

የቀድሞው የአስተን ቪላ አሠልጣኝ ስቴቨን ጄራርድ ወደ ቱርክ በማቅናት የትራብዞንስፖርት አለቃ ሊሆን ነው ሲል የቱርኩ ካራር ፅፏል።

ወደ እንግሊዝ ስንመለስ ማንችስተር ዩናይትድ የቶተንሃም ሆትስፐሩን ሃሪ ኬን ለማስፈረም የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም ሲል ሚረር ገልጧል።

ሚረር እንደዘገባው ማንችስተር ዩናይትድ የ29 ዓመቱ እንግሊዛዊን ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ማስፈረም ይፈልጋል።

ፒኤስጂ የቪያሪያሉን ተከላካይ ፓው ቶሬዝ በሚመጣው ክረምት ወደ ፈረንሳይ ሊያስመጣ ይችላል።

ፓው ቶሬዝ ለማንችስተር ዩናይትድ ይፈርማል ቢባልም አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃገር ተጫዋቹን እንደማይፈልጉት ገልጠዋል።

ቴን ሃግ ምንም እንኳ ባለፈው ሳምንት በሊቨርፑል ከባድ ሽንፈት ቢደርስባቸውም ሊያስፈርሟቸው የሚሹ ተጫዋቾችን ስም አልቀየሩም።

ዩናይትድ እንግሊዛዊው ተከላካይ ሃሪ ማጓዬርን መሸጥ ሊከብዳቸው ይችላል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ተጫዋቹ ደመወዙ ከፍተኛ መሆኑ ነው። ፉትቦል ኢንሳይደር እንደሚለው ማጓዬር በሳምንት 200 ሺህ ፓውንድ ይከፈለዋል።

በተመሳሳይ ኤሲ ሚላን የሊቨርፑሉን ጊኒያዊ አማካይ ናቢ ኬይታን ማምጣት ቢሹም የተጫዋቹ ደመወዝ ከፍ ማለቱ እንዳያግዳቸው ተሰግቷል። ነገር ግን ኬይታ በቅርቡ ኮንትራት አልባ ሊሆን ይችላል።

ባርሴሎና የማንችስተር ሲቲውን አማካይ በርናንዶ ሲልቫ ማምጣት ቢፈልጉም የተጫዋቹ ዋጋ 70 ሚሊዮን ፓውንድ መሆኑ ሁኔታውን ያከብደዋል ይላል ሙንዶ።