ከቀናት በፊት ቀይ ባሕር ላይ በሁቲ አማፂያን የተመታችው ነዳጅ ጫኝ መርከብ አሁንም እየነደደች መሆኑ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ሳምንት በየመን አማፂያን በቀይ ባሕር ላይ ጥቃት የደረሰባት ነዳጅ ጫኝ መርከብ አሁንም በእሳት እንደተያያዘች መሆኗን እና ነዳጅ እየፈሰሰ ሊሆን እንደሚቸል ፔንታጎን አስታወቀ።
በግሪክ ባለቤትን የተያዘችውን ይህችን ነዳጅ ጫኝ መርከብ ለመታደግ ጥረት ቢደረግም ከሁቲ አማፂያን የተጨማሪ ጥቃት ዛቻ በመድረሱ ጥሩ መስተጓጎሉን የአሜሪካ መከላከያ ኃይል አክሎ ገልጿል።
መርከቧ 150 ሺህ ቶን ወይንም አንድ ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የጫነች ሲሆን፣ በታሪክ ተመዝግቦ የማያውቅ ከፍተኛ ነዳጅ ወደ ባህሩ ሊፈስ እንደሚችል ተሰግቷል።
በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጽያን አብዛኛውን የመንን የሚቆጣጠሩ ሲሆን ባለፉት 10 ወራት በጋዛ ሰርጥ እስራኤል እና ሐማስ የሚያደርጉትን ጦርነት ተከትሎ ፍልስጤማውያንን በመደገፍ ጥቃቶችን እያደረሱ ነው።
በእነዚህ ጊዜያት ሁቲዎች ባደረሱት ጥቃት ሁለት መርከቦችን ማስመጣቸውን፣ እንዲሁም ቢያንስ ሁለት የመርከቡን ሰራተኞች መግደላቸውን ገልጸው ነበር።
አማፂያኑ ጥቃት የምናደርሰው ከእሰራኤል፣ አሜሪካ ወይንም ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ግንኙነት ያለውን ብቻ ነው ይበሉ አንጂ እስካሁን ድረስ በተለያዩ አገራት የተመዘገቡ መርከቦችን ዒላማ አድርገዋል።
ሶዩኒየን የተባለችው ይህች ነዳጅ የጫነች መርከብ ባለፈው ሳምነት ረቡዕ ከሁለት አነስተኛ ጀልባዎች በተተኮሰ ጥይት፣ ቀጥሎም እስካሁን ድረስ በውል ባልተለየ ሦስት ተወንጫፊ መሳርያ ነበር የተመታቸው።
ይህም በመርከቧ ላይ እሳት እንዲነሳ ማድረጉን የዩኬ ባህር ኃይል አስታውቋል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአንድ ቀን በኋላ የመርከቧ 25 ሠራተኞችን የአውሮጳ የጦር መርከብ አባላት ወደ ጅቡቲ በሰላም ማድረሳቸው ተገልጿል።
ከዚያ በኋላም አማፂያኑ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በለቀቁት ተንቀሳቃሽ ምስል እንደታየው ነዳጅ የጫነችውን መርከብ ዳግም አጥቅተው በእሳት አንድትያያዝ አድርገዋል።
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት በሶዩኒየን መርከብ ላይ የደረሰው ጥቃት እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር።
ቢሮው አክሎም ከዚህ በፊት እእአ በ1989 በኤክሶን ቫልዴዝ መርከብ ላይ ከታየው እና በአላስካ ባህር ዳርቻ ላይ ከፈሰሰው 257 ሺህ በርሜል ነዳጅ በአራት እጥፍ በከፋ መልኩ ከመርከቧ ነዳጅ ወደ ቀይ ባሕር ሊፈስ ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሜጀር ጄነራል ፓትሪክ ራይደር ማክሰኞ ዕለት እንዳሉት ሁለት መርከቦች የደረሰውን ጉዳት ለመታደግ ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ከሁቲዎች ጥቃት ለማድረስ ማስፈራርያ በመሰንዘሩ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም አሜሪካ በቀጠናው ካሏት አጋሮች ጋር አካባቢው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ስራ እየሰራች መሆኑን አስታውቀዋል።












