ከ13 ዓመት በፊት በተፈጸመ የአንዲት ኬንያዊት ግድያ የተጠረጠረ የቀድሞ የብሪታኒያ ወታደር በቁጥጥር ሥር ዋለ

አንድ የቀድሞ የብሪታኒያ ወታደር በአውሮፓውያኑ 2012 ኬንያ ውስጥ በሚገኝ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደር ተፈጽሟል ከተባለ የ21 ዓመት ሴት ግድያ ጋር በተያያዘ ለአገሪቱ መንግሥት ተላልፎ ሊሰጥ ነው።

ሐሙስ ዕለት በዩናይትድ ኪንግደም ቲድዎርዝ በተባለች ከተማ በቁጥጥር ሥር የዋለው ሮበረትት ጄምስ ፑርኪስ፤ በማግስቱ ፍርድ ቤት መቅረቡን የአገሪቱ የወንጀል ቁጥጥር መሥሪያ ቤት የሆነው 'ዘ ናሽናል ክራይም ኤጀንሲ' አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎችን ለሌሎች አገራት አሳልፎ የሚሰጠው የተቋሙ ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ልዩ መኮንኖች የቀድሞውን ወታደር የያዙት፤ አግነስ ማንጁሪ ከተባለችው ኬንያዊት ግድያ ጋር በተያያዘ ነው። ተጠርጣሪው ላይ የእስር ትዕዛዝ የወጣው መስከረም ላይ እንደነበርም ተገልጿል።

ኬንያዊቷ ዋንጁሪ መገደሏ የተረጋገጠው ከናይሮቢ በ200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ናኙኪ ከተማ አስከሬኗ የፍሳሽ ማስወገጃ ታንክ ውስጥ ተጥሎ ከተገኘ በኋላ ነበር። በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2012 የጠፋችው ኬንያዊቷ፤ አስከሬኗ የተገኘው ከሦስት ወራት ፍለጋ በኋላ ነበር።

አስከሬኑ የተገኘው በአገሪቱ ከሚገኘው የብሪታኒያ ወታደሮች ማሠልጠኛ ካምፕ አቅራቢያ ነው። ዋንጁሪ በተገደለችበት ዕለት የብሪታኒያ ወታደሮችም በነበሩበት አንድ ባር ውስጥ ከጓደኞቿ ጋር እየተዝናናች እንደነበር ተነግሯል።

የዋንጁሪ የቅርብ ዘመድ የሆነችው ኢስተር ኛጆኪ በግድያ የሚጠረጠረው የቀድሞ ወታደር ወደ ኬንያ ተላልፎ እንዲሰጥ የሚደረገውን ግፊት ለማጠናከር ባለፈው ወር የዩናይትድ ኪንግደም ተጉዛ የመከላከያ ሚኒስትርን አግኝታለች።

የ38 ዓመቱ ፑርኪስ ረቡዕ ዕለት በነበረው የችሎት ውሎ፤ ለኬንያ ተላልፎ ሊሰጥ መሆኑን በመቃመው አቤቱታ የማቅረብ ዕቅድ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። ቀጣዩ የችሎት ቀጠሮ በመጪው ሳምንት አርብ ዕለት ሲሆን እስከዚያ ድረስም በእስር ላይ ይቆያል።

የቀድሞው ወታደር ጠበቆች ደንበኛቸው የቀረበበትን የሰው መግደል ውንጀላ "በጽኑ እንደሚክድ" ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

የዋንጁሪ የቅርብ ዘመድ የሆነችው ኛጆኪ፤ "በአክስቴ ጉዳይ ተጠርጣሪው መያዙን በመስማታችን ቤተሰቤ እጅጉን እረፍት ተሰምቶታል" ስትል እንደተናገረች የሟቿን ቤተሰብ የወከሉት ጠበቆች አርብ ዕለት ባወጡት መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

"ለምንወዳት አግነስ ፍትሕ ለማስገኘት ትልቅ እርምጃ የሆነውን ይህንን ቀን ለብዙ ዓመታት ጠብቀነዋል" ሲሉም የተሰማቸውን ገልጸዋል።

የሟቿን ቤተሰቦች የወከለው የእንግሊዙ 'ሊ ደይ' የሕግ አገልግሎት ድርጅት ጠበቃ የሆነችው ቴስ ጂኦርጂ በበኩሏ፤ "ይህ [እርምጃ] በአግነስ ጉዳይ ፍትሕ ለማግኘት ከአሥር ዓመት በላይ ሲታገሉ ለቆዩት ለደንበኛችን እና ለቤተሰቦቿ ትልቅ ጊዜ ነው።

"አሁን የዩኬ እና የኬንያ ባለሥልጣናት ተጠርጣሪው በተቻለ ፍጥነት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በጋራ እንደሚሠሩ ተስፋ እናደርጋለን" ብላለች።

የዋንጁሪ ቤተሰብ፤ የብሪታኒያ ጦር የኬንያዊቷን ሞት እየሸፈነ መሆኑን በመግለጽ ለረዥም ጊዜ ወቀሳቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የኬንያ ባለሥልጣናትን በወቅቱ ጉዳዩን በተገቢው ሁኔታ አለመመርመራቸውን በማንሳት ሲተቹ ነበር።

የአሁኑ ሒደት የተጀመረው የዋንጁሪ ቤተሰብ እንዲሁም የኬንያ የመብት ተሟጋች ቡድኖች እና የሴቶች መብት ተሟጋቾች ያደረጉትን ግፊት ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2018 መዝገቡ በድጋሚ በመከፈቱ ነው።

ዋንጁሪ በአንድ ወይም ሁለት የብሪታኒያ ወታደሮች እንደተገደለች እንዲሁም ደረቷ እና ሆዷ ላይ በስለታማ ነገር እንደተወጋች በ2019 ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

ከሁለት ዓመት በኋላ በ2021 የእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ ያወጣው የምርመራ ዘገባ አንድ የብሪታኒያ ወታደር ዋንጁሪን እንደገደላት ለባልደረባው ተናዝዞ እንደነበር አጋልጧል።

ወታደሩ ከዚህ ክስተት በኋላ ሠራዊቱን ለቅቆ እንደወጣ እና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መኖር እንደቀጠለም ተዘግቧል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ግድያ የተፈጸመበትን ናኙኪ ከተማን ጨምሮ ኬንያ ውስጥ የሚገኙ ወታደሮቹን ምግባር በተመለከተ ውስጣዊ ምርመራ እንደሚያካሄድ በ2024 አስታውቆ ነበር።

ሠራዊቱ ባደረገው ምርመራ 35 ወታደሮች ከኬንያዊ ሴቶች ጋር የወሲብ ንግድ ጨምሮ ወሲባዊ ብዝበዛ እና በደል መፈጸም ውስጥ ተሳትፈው እንደተገኙ ተደርሶበታል። ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኝ ያህሉ እነዚህን ድርጊቶች የፈጸሙት ሠራዊቱ፤ ወታደሮች በ2022 በክፍያ የሚደረግ ወሲባዊ ግንኙነትን እንዳይፈጽሙ ክልከላ ከጣለ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።