ከ10 ዓመት በፊት ኬንያዊቷን የገደለው ብሪታንያዊ በቁጥጥር ስር እንዲውል የእስር ማዘዣ ወጣ

የኬንያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከአስር ዓመት በፊት የ21 ዓመቷን አግነስ ዋንጂሩን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረ ብሪታንያዊ በቁጥጥር ስር እንዲውል የእስር ማዘዣ አወጣ።

አግነስ ዋንጂሩ የተገደለችው እአአ በ2012 መጋቢት ወር ላይ ሲሆን አስከሬኗ በማዕከላዊ ኬንያ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ በፍሳሽ ማጠራቀሚያ [በሴፕቲክ ታንክ] ውስጥ የተገኘ ሲሆን ይህ የሆነው ከወታደሮች ጋር በፓርቲ ምሽቷን ካሳለፈች ከሦስት ወራት በኋላ ነው።

ሟቿ ኬኒያዊት የአምስት ወር ሴት ልጅ የነበራት ሲሆን ከናይሮቢ በስተሰሜን 200 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ኛኙኪ ከተማ የምትኖረው እህቷ ሮዝ ዋንዩዋ ልጇን እያሳደገች ትገኛለች።

አሌክሳንደር ሙቲቲ የተባሉት ዳኛ ተጠርጣሪው በኬንያ ችሎት ፊት ቀርቦ የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል የሚያስችል በቂ ማስረጃ አለ በማለት ውሳኔውን አሳልፈዋል።

የዋንጂሩን ቤተሰብ የወከሉት ጠበቃ ካማኡ ምቢኡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአሁኑ ውሳኔ ተጠርጣሪውን ከዩናይትድ ኪንግደም ለማስመጣት መንገድ የሚጠርግ ነው።

አክለውም "ይህንን እንደ በጎ ዜና ነው የምናየው፤ ነገር ግን ይህ የሕዝብ ፍላጎት ያለበት ስለሆነ በጣም ግልጽነት እንዲኖር እንጠይቃለን" ብለዋል።

ዳኛው የችሎቱን ነጻነት ለመጠበቅ ሲባል የተጠርጣሪውን እና የምስክሮችን ማንነት ይፋ ከማድረግ መቆጠባቸውን ገልፀዋል።

የዩኬ መንግሥት ቃል አቀባይ በመግለጫቸው ላይ "ሀሳባችን ሁሉ ከአግነስ ዋንጂሩ ቤተሰቦች ጋር ነው፤ እንዲሁም ፍትህ እንዲያገኙ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጥላቸዋለሁ" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም ጉዳዩ በሕግ የተያዘ በመሆኑ ተጨማሪ አስተያየት ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ከኬንያ መርማሪዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጾ ነበር።

የአግነስ ዋንጂሩ ቤተሰቦች ፍትህ ለማግኘት ለረዥም ዓመታት ሲጠይቁ ነበር።

ቤተሰቦቿ የሚኖሩት ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ኛኙኪ የብሪታንያ ጦር ማሰልጠኛ የሚገኝበት አካባቢ ነው።

የዋንጂሩ እህት ልጅ ኤስተር ንጆኪ ተጠርጣሪውን ወደ ኬንያ ለማምጣት ጊዜ እንደሚወስድ ገልጻ የእስር ማዘዣው "ቢያሳዝንም ደስ የሚል ቅጽበት ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ እንደተናገረው ምስክሮች በዩኬ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጾ ችሎቱ በሚታይበት ጊዜ ግን እንደሚገኙ አረጋግጧል።

መቀመጫዋን በዩኬ ያደረገችው የሕግ ወኪል ቴሳ ግሪጎሪ "በተቻለ ፍጥነት ተጠርጣሪው ወደ ኬንያ ተወስዶ ችሎት ፊት እንዲቀርብ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ የብሪታንያ መንግሥት ኃላፊነት ነው" ብላለች።