የዩኬ ጦር የኬንያዊቷን ግድያ 'ለመሸፋፈን' ሞክሯል በሚል ቤተሰቦቿ ቁጣቸውን አሰሙ

እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 በብሪታኒያ ወታደር ተገድላለች የተባችው ኬንያዊት ቤተሰቦች ፍትህ እንዳልተሰጣቸው በመግለጽ ቁጣ እና ተስፋ መቁረጣቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

አግነስ ዋንጂሩ የተባለችው ሟች ቤተሰቦች እስካሁን በዚህ ጉዳይ በነፍስ ማጥፋት የተከሰሰ ሰው አለመኖሩንም ተናግረዋል።

በብሪታኒያ የሚታተም 'ሰንዴይ ታይምስ' የተሰኘ ጋዜጣ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መከላከያ ሠራዊት የአግነስ ዋንጂሩ ግድያ ለመሸፋፈን ሞክሯል የሚል ሪፖርት ይዞ መውጣቱን ተከትሎ የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ከኬንያ የምርመራ መሥሪያ ቤት ጋር በጋራ እየሰራሁ ነው ብሏል።

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በ21 ዓመቷ የተገደለችው አግነስ ዋንጂሩ አስከሬኗ በማዕከላዊ ኬንያ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ በፍሳሽ ማጠራቀሚያ [በሴፕቲክ ታንክ] ውስጥ የተገኘ ሲሆን ይህ የሆነው ከወታደሮች ጋር በፓርቲ ምሽቷን ካሳለፈች ከሦስት ወራት በኋላ ነው።

ሟቿ ኬኒያዊት የአምስት ወር ሴት ልጅ የነበራት ሲሆን ከናይሮቢ በስተሰሜን 200 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ናንዩኪ ከተማ የምትኖረው እህቷ ሮዝ ዋንዩዋ ልጇን እያሳደገች ትገኛለች።

ዋንዩዋ የሰንዴይ ታይምስ ዘገባ እንዴት የሚያሰቃዩና መራር ትዝታዎችን እንደቀሰቀሰባት ተናግራለች።

እሷ እና ባለቤቷ ጆን ሙቺሪ ሲሩ እያሉ ለሚጠሯት ዋንጂሩ ፍትህ የማግኘት ጉዳይ ተስፋ እንደቆረጡ ገልጸዋል።

"ነጩን ገዳይ የገደለችው ሲሩ ብትሆን ኖሮ አሁን የት እንደታሰረች እንኳን አላውቅም ነበር" ስትል ያስረዳችው ዋንዩዋ "ሆኖም ገዳይዋ ነጻ ሆኖ እየኖረ ነው። እኔ ልጇን ብቻዬን እያሳደግኩ ነው፣ ስለ ደኅንነቷ የጠየቀ ማንም የለም መንግሥትም ቢሆን" ስትል አክላለች።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አቋርጣ ልጇን ለማሳደግ በወሲብ ንግድ ተሰማርታ የነበረችው ሟቿ ዋንጂሩ ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው ከሁለት የብሪታኒያ ወታደሮች ጋር ከመጠጥ ቤት ስትወጣ ነበር።

ታዲያ ከጊዜ በኋላ ወታደሮቹ ከቆዩበት ክፍል በስተጀርባ የአካል ክፍሎቿ ጎድለው እና በስለት ቆስለው አስከሬኗ ተገኝቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 የኬንያ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ተመልክቶ በኋላ ዋንጂሩ በአንድ ወይም በሁለት የብሪታኒያ ወታደሮች ተገድላለች የሚል ብያኔ ሰጥቷል።

ዳኛዋም ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ያዘዙ ቢሆንም የዩኬ ሠራዊት ምንም ሲያደረግ አልታየም ሲል ሰንዴይ ታይምስ ዘግቧል።

የሟቿ እህት ባለቤት ሙቺሪ በጉዳዩ ቤተሰቡ ቅር ተሰኝቷል፣ ነገር ግን ጉዳዩን ከዚህ በላይ ለመውሰድ ለሕግ አገልግሎት መክፈል አልቻለም።

"ታውቃላችሁ፣ እኛ ድሆች ነን። እኔ ተራ ሠራተኛ ነኝ። ጉዳዩን ለመከታተል ጠበቃ ብንይዝ ደስ ይለን ነበር። ነገር ግን አንችልም" ብለዋል።

በኬኒያ ናንዩኪ ግዛት የብሪታኒያ ጦር ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚገኝ ሲሆን ለበርካታ ዓመታት የአካባቢው ነዋሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።