ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ የሚገኙ የብሪታንያ ወታደሮች ክልከላ ቢጣልባቸውም ለወሲብ እየከፈሉ መሆኑ በምርመራ ተረጋገጠ
አወዛጋቢ በሆነው እና በኬንያ በሚገኘው የብሪታኒያ የጦር ካምፕ ከሰፈሩ ወታደሮች መካከል የተወሰኑት የወሲብ ንግድን እንዳይጠቀሙ ክልከላ ቢጣልባቸውን ድርጊቱን መፈጸም መቀጠላቸውን የብሪታንያ ሠራዊት ያደረገው ምርመራ አመለከተ።
'ባቱክ' ተብሎ በሚጠራው የብሪታንያ ሠራዊት የኬንያ ስልጠና ክፍል የሚገኙ ወታደሮች "በዝቅተኛ ወይም መካከለኛ" ደረጃ የወሲብ ንግድ ተዳዳሪዎችን እየተጠቀሙ መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርቱ፤ ይህንን ልምምድ ለማስቀረት የበለጠ ስራ ሊከናወን እንደሚገባ ገልጿል።
የሠራዊቱ ምርመራ ከሐምሌ 2022 ጀምሮ ያለውን ሁኔታ የዳሰሰው ምርመራው፤ ከሁለት ዓመት በላይ የሚሆን ጊዜም ሸፍኗል።
ምርመራው የተካሄደው የእንግሊዙ አይቲቪ በባቱክ የሚገኙ ወታደሮች ባህሪን በተመለከተ በጥቅምት 2024 ያወጣውን የምርመራ ዘገባ ተከትሎ ሲሆን ዘገባው አንዳንድ የሠራዊቱ አባላት በአካባቢው ከሚገኙ ሴቶች ጋር ወሲብ ለመፈጸም ይከፍላሉ የሚል ክስን ያካተተ ነበር።
አይቲቪ ዶክመንተሪ፤ አግነስ ዋንጂሩ የተባለች አካባቢው ነዋሪ በ2012 በካምፑ በሚገኙ የብሪታኒያ ወታደሮች ተገድላለች መባሉን ተከትሎ ከዚህ ቀደም የተነሱ ስጋቶችን የሚዳስስ ነበር።
ከዚህ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ካምፕ ውስጥ የሰፈሩ ወታደሮችን ባህሪን በተመለከተ ተከታታይ ውንጀላዎች ቀርበዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር በሠራዊቱ የሚፈጸም ወሲባዊ ብዝበዛ እና በደልን ለመከላከል በሚል ወታደሮች የወሲብ ንግድ ተዳዳሪዎችን እንዳይጠቀሙ በ2022 ክልከላ ጥለዋል።
የሠራዊቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጄነራል ሮሊ ዋከር ባወጡት መግለጫ፤ ሰራዊቱ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ አባላቱ የሚፈጸም ወሲባዊ ብዝበዛን ለማስቆም ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
"እንዲካሄድ ያደረግኩት ምርመራ ግኝት፤ አሁንም ኬንያ ውስጥ ልውውጥ የሚደረግበት ወሲብ በዝቅተኛ ወይም መካከለኛ ደረጃ እየተፈጸመ ነው ሲል ደምድሟል። ይህ ድርጊት ጭራሹኑ መፈጸም አልነበረበትም" ብለዋል።
"በብሪታኒያ ሠራዊት ውስጥ በሚገኙ ሰዎች የሚፈጸም ወሲባዊ ብዝበዛ ወይም በደል ምንም አይነት ቦታ የለም። የብሪታኒያ ወታደር ከመሆኑ ትርጉም ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣረስ ነው። የተጋለጡ ሰዎች ላይ ማድባት እንዲሁም ከበደል እና ብዝበዛ ማትረፍ የሚፈልጉ ሰዎችን መጥቀም ነው" ሲሉም አክለዋል።
ምርመራው የተካሄደው ሁለት ወታደራዊ መኮንኖችን፣ አንድ የመንግሥት ሰራተኛ እንዲሁም ገለልተኛ አማካሪን በያዘ የአራት ሰዎች ቡድን ነው።
ቡድኑ፤ በባቱክ የሰፈሩ ወታደሮች ባህሪን እንዲሁም ሠራዊቱ ወታደሮች ለወሲብ እንዳይከፍሉ የሚከለክለውን ህግ ጥሰት ለመከላከል የዘረጋውን ስርዓት መርምሯል።
ይህ ህግ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በባቱክ የሚገኙ ወታደሮች ለወሲብ ከፍለዋል የሚል ጥርጣሬ የቀረበባቸው 35 ክስተቶች በሪፖርቱ ውስጥ ተዘርዝረዋል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ 7,666 የብሪታንያ ወታደሮች በዚያ ካምፕ ውስጥ አገልግለዋል።
ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው ከክስተቶቹ ውስጥ 26 ያህሉ ተፈጽመዋል የተባለው ህጉ ተግባራዊ መሆኑን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ህዳር ላይ ለሁሉም የሰራዊቱ አባላት ስልጠና ከመሰጠቱ በፊት ነው። ዘጠኙ ደግሞ ከዚያ ጊዜ በኋላ ተፈጽመዋል የተባሉ ናቸው።
በአብዛኛዎቹ ክስተቶች ውስጥ ወታደሮቹ ለወሲብ ከፍለዋል የሚለው ውንጀላ በማስረጃ አልተረጋገጠም።
ሪፖርቱ ውስጥ ከተካተቱት ዝርዝሮች በተጨማሪ ከአምስት በታች የሆኑ ከወሲብ ንግድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
እነዚህ ክስተቶች ተፈጸሙት ጉዳዩን በተመለከተ የተደረገው ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው።
ሪፖርቱ፤ ስልጠና የተሰጠ ቢሆንም እና የቁጥጥር እርምጃዎች ቢዘረጉም፤ እውነታው ግን ኬንያ ውስጥ በሚገኙ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች "ልውውጥ የሚደረግበት ወሲባዊ እንቅስቃሴ" እየተፈጸመ መሆኑ እንደሆነ አመልክቷል። "ያለበት ደረጃም በዝቅተኛ እና መካከለኛ ውስጥ ነው" ብሏል።
ከዚህ ውጪ የኬንያ የፓርላማ አባላት፤ በባቱክ የሚገኙ ወታደሮች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያደርሱታል የተባለን በደል በተመለከተ ምርመራ እያካሄዱ ነው።
የፓርላማ አባላቱ፤ በብሪታኒያ ወታደሮች ባህሪ የተነሳ ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉ ሰዎችን እንዲሁም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ከኬንያውያን የወለዷቸውን ልጆች ችላ ብለዋል የተባሉ ወታደሮች ላይ የቀረቡ ውንጀላዎችን አዳምጠዋል።
በዚህ ዓመት ሰኔ ላይ በካምፑ የሚገኝ ወታደር በመድፈር የቀረበበትን ክስ ተከትሎ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዲመለስ ተደርጓል።