ሃማስ የአሜሪካ ዜግነት ያለውን እስራኤላዊ ታጋች ሊለቅ ነው

ባለፈው ወር የኤዳን አሌክሳንደርን አያት የልጅ ልጇ እንዲለቀቅ በጠየቀችበት ወቅት ፎቶውን ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ወር የኤዳን አሌክሳንደርን አያት የልጅ ልጇ እንዲለቀቅ በጠየቀችበት ወቅት ፎቶውን ይዛ

ሃማስ በጋዛ ታግቶ ያለውን የመጨረሻውን በሕይወት ያለ የአሜሪካ ዜግነት ያለውን እስራኤላዊ ኤዳን አሌክሳንደርን እንደሚለቅ አስታወቀ።

ሃማስ የመጨረሻው በሕይወት ያለ አሜሪካዊ ታጋች ነው የተባለውን ኤዳን አሌክሳንደርን የሚለቅቀው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ የሚደረገው ጥረት አካል በሚል መሆኑ ተገልጿል።

ውሳኔው የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት መካከለኛውን ምሥራቅን ከመጎብኘታቸው በፊት ነው።

ሃማስ በጋዛ የሚገኘውን የአሜሪካ ዜግነት ያለውን ታጋች እንደሚለቅ ሲገልጽ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እና እርዳታ ወደ ጋዛ ዳግም እንዲገባ ለማድረግ ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ውይይት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።

እስራኤል ወደ ጋዛ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ ካገደች 70 ቀናት አልፈዋል።

ቀደም ብሎ የሃማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኑ በቀጥታ ከአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ጋር በኳታር ድርድር ሲያደርግ ነበር።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሃማስ ለምን አሌክሳንደርን መልቀቅ እንደፈለገ በአሜሪካ እንደተነገራቸው አስታውቀዋል።

ድርድሩን በቅርበት የሚከታተሉ ከፍተኛ የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሃማስ አሜሪካዊውን ታጋች ለመልቀቅ መወሰኑን ይፋ ያደረገው ትራምፕ ወደ ቀጠናው ሲመጡ መልካም ገጽታን ለማሳየት በማለም ነው።

ኤዳን አሌክሳንደር የሚለቀቅበትን ሂደት ለማመቻቸት በሃማስ እና በአደራዳራዳሪዎቹ መካከል ሌላ ስብሰባ ለሰኞ ጠዋት ቀጠሮ ተይዟል።

በዚህም የተነሳ እስራኤል ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን ለጊዜው የምትገታ ሲሆን የአየር ድብደባዎችንም ታጋቹን በሚያስረክቡበት ወቅት ታቋርጣለች ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኤልክሳንደር እንደሚለቀቅ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ትልቅ ዜና" በማለት አረጋግጠው "በበጎ እምነት የተወሰደ እርምጃ" ሲሉ ጠርተውታል።

ቴላቪቭ ተወልዶ ኒው ጀርዚ ያደገው የ21 ዓመቱ አሌክሳንደር ጥቅምት 7 በሃማስ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት በጋዛ ድንበር አቅራብያ በልዩ ሁኔታ በሰለጠነ የእግረኛ ጦር ውስጥ በማገልገል ላይ ነበር።

ሃማስ በ2023 በፈጸመው ጥቃት 251 ሰዎች ሲታገቱ 59 አሁንም በሃማስ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ ተብሎ ሲታመን ከእነዚህ መካከል ደግሞ 24 በሕይወት መኖራቸው ይገመታል።

ከታጋቾቹ መካከል አምስቱ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፣ አሌክሳንደር በሕይወት ካሉት መካከል ብቸኛው እንደሆነ ታምኗል።

የተቀሩት ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቁ ሠልፈኞች ከያዝዋቸው ምስሎች መካከል የኤዳን አሌክሳንደር ምስል ይታያል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሃማስ ባወጣው መግለጫ ታጋቹ የሚለቀቀው የተኩስ አቁም ለማድረግ እና ላለፉት 70 ቀናት ሙሉ በሙሉ እገዳ ተጥሎበት ያለው የምግብ፣መድሃኒት እና ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ የሚደረገው ጥረት አካል ነው ብሏል።

ቡድኑ ጦርነቱ እንዲያበቃ የመጨረሻውን ስምምነት ማድረግ እንደሚፈልግም ገልጿል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ባወጣው መግለጫ የአሜሪካ መንግሥት ሃማስ አሌክሳንደርን መልቀቅ የፈለገበት ምክንያት ማሳወቁን ገልጾ "ለአሜሪካውያን በጎ ገጽታን ለማሳየት" እንዲሁም ይህ እርምጃ ተጨማሪ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል እንደሚያደርግ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

መግለጫው አክሎም የእስራኤል ፖሊሲ "በጦርነት ውስጥ ሁሉንም የጦርነቱን ዓላማዎች ለማሳካት ባለው ቁርጠኝነት ላይ በመመስረት" ድርድሩ ማካሄድ ነው ሲል አክሏል።

ዘ ፋሚሊስ ኤንድ ሚሲንግ ፋሚሊስ ፎረም የተሰኘው ቡድን በበኩሉ የአሌክሳንደር መለቀቅ " የቀሩትን ታጋቾች ነጻነት የሚያረጋግጥ አጠቃላይ ስምምነት መጀመርያ ምልክት መሆን አለበት" ብሏል።

አክሎም ፕሬዝደንት ትራምፕ "ለታጋች ቤተሰቦች ሁሉ ተስፋ ሰጥተዋል" ካለ በኋላ ኔታንያሁን "ሁሉንም ወደ ቤታቸው ያምጧቸው" ሲሉ ጥያቄ አቅርቧል።

ከዚህ ቀደም ሃማስ ታጋቾቹን ለመልቀቅ የሚስማማው ጦርነቱ የሚያበቃ ከሆነ ብቻ ነው ብሎ የነበረ ሲሆን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ግን በተደጋጋሚ ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል።

በሃማስ እና በአሜረካ መካከል ንግግር የተካሄደው የትራምፕ አስተዳደር በኔታንያሁ አቋም ላይ ያለው ተስፋ መቁረጥ እየጨመረ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎች እየወጡ ባለበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እንዲሁ በጋዛ የሚያካሄዱትን ጦርነት ለፖለቲካዊ ምክንያቶች በሚል እያራዘሙ ነው በሚል በእስራኤላውያን ጫና እየተደረገባቸው ነው።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት መካከለኛው ምሥራቅ የሚደርሱ ሲሆን እስራኤል ጉዟቸው እስኪጠናቀቅ ድረስ ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ወታደራዊ እርምጃዋን አጠናክራ እንደምትቀትል ዝታለች።

የእስራኤል ባለስልጣናት ዕቅዱ የሚወሰደው ወታደራዊ እረምጃን ከማስፋት ባሻገር ላልተወሰነ ጊዜ ጋዛን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ በግዴታ ፍልስጤማውያኑን ከጋዛ ወደ ደቡብ ማፈናቀል፣ እንዲሁም ምንም እንኳ የመንግሥታቱ ድርጅት ውሳኔውን ቢቃወመውም የእርዳታ ስርጭቱን ለግል ኩባንያዎች አሳልፎ መስጠት ያካትታል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ይህንን የእስራኤል መንግሥት ውሳኔን በተመለከተ እንደማይተባበር ገልጾ እርዳታን "ለጦር መሳርያነት" መጠቀም ነው ብሏል።

እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገቡ የሰብዓዊ እርዳታዎችን፣ ምግብ፣ መድሃኒት እንዲሁም ሌሎች አቅርቦቶችን ካገደች 70 ቀን ሆኗታል።

የእርዳታ ድርጅቶች ይህንን የእስራኤል መንግሥት እርምጃ የማስራብ ፖሊሲ ሲሉ ጠርተው የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል ብለዋል።

እስራኤል በመጋቢት ወር የወታደራዊ እርምጃዋን ዳግም አጠናክራ ከቀጠለች ወዲህ ብቻ 2,720 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ይገልጻል።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ ከጥር ወር ጀምሮ በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዱ 10,000 ሕጻናት መለየት ተችሏል።

በጋዛ የምግብ ዋጋ በ1,400 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን በመግደል 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሔድ የጀመረችው።

በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ52,829 በላይ ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የግዛቲቱ ጤና ሚኒስቴር ይናገራል።

እስራኤል ሐማስ ላይ የሚደረግ ወታደራዊ ጫና በቁጥጥሩ ስር የሚገኙ 59 ታጋቾችን ለማስለቀቅ ያግዛል ትላለች። ከእነዚህ መካከል በሕይወት እዳሉ የሚታመነው 24 ብቻ ናቸው።