ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሚሊዮን ዓመታት በኋላ በምድር ላይ የሰዎች እንደነበሩ የሚያስታወቁ ቅሪቶች ሊገኙ ይችላሉ?
የሰው ልጆች ከሚያስደንቋቸው ነገሮች አንዱ ታሪክ ነው። 4.5 ቢሊዮን ዓመታት ያስቆጠረችውን ምድር በመቆፈር የቀደመው ታሪክ ቅሪቶችን ለማግኘት ይሞከራል።
ከሰው ልጆች በፊት የነበሩ ቀደምት ዝርያዎች እንዴት እንደሚኖሩ ለማወቅ ምርምሮች ይደረጋሉ።
ምናልባት የሰው ልጆች ከዚህ ምድር ጠፍተው የላቀ የማሰላሰል አቅም ያላቸው ዝርያዎች ቢፈጠሩስ? እነዚህ ዝርያዎች አሁን ያለነውን የሰው ልጆች ያስታውሱን ይሆን? አሁን ስላለው ሥልጣኔስ ያውቁ ይሆን?
የሰዎች ቅሪት ለወደፊት ይገኛል?
በአሜሪካ ሮቸስተር ዩኒቨርስቲ የአስትሮፊዚክስ ባለሙያ አዳም ፍራንክ እንደሚሉት፤ በመጪው ዘመን የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች የሰው ልጆችን ቅሪት ያገኛሉ ብሎ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
"ከምድር የተወሰነው ክፍል ብቻ ነው ቅሪተ አካሉ የሚገኘው። ሥልጣኔ በአንዳች ዘመን ብቻ ከቆየ ለወደፊት የመገኘት ዕድሉ ይጠባል" ይላሉ።
ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በአውሮፓውያኑ 2018 ያሳተሙት ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ከ165 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በርካታ ዳይኖሰሮች በምድር ቢኖሩም አሁን ላይ ማግኘት የተቻለው ውስን ቅሪተ አካል ብቻ ነው።
የሰው ልጆች እስካሁን የኖሩት 300 ሺህ ዓመታት ብቻ ስለሆነ ቅሪተ አካላችን ለወደፊት የመዝለቁ ነገር አስተማማኝ አይደለም።
ነገር ግን አንዳንድ ምልክቶች ትተን እናልፍ ይሆናል።
'የምድር ኬምስትሪ'
ዓለቶች በጊዜ ሒደት አንዳቸው ሌላቸው ላይ ይደራረባሉ። ይህ የዓለት ክምር ስትራታ ይባላል።
እያንዳንዱ የዓለቱ ክፍል የራሱ የኬሚካል ይዘት አለው። ከምድር ጋር የሚናበብም ነው።
ፕሮፌሰር አዳም እንደሚሉት፤ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሙቀት ጨምሯል፤ የባሕር ወለልም ከፍ እያለ ነው።
ይሄ ለውጥ የዓለቶቹን ይዘት ይለውጣል። ለውጡ የሚታወቀው ከመቶ ሚሊዮን ዓመታት በኋላ ይሆናል።
"የኦክስጂን እና ካርበን ይዘቱ ይለወጣል። በሰው ልጆች ድርጊት ሳቢያ የተፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ ይዘቱን ይቀይረዋል" በማለት ያስረዳሉ።
የዝግመተ ለውጥ መቀየር
የሰው ልጆች ቅሪተ አካል ለወደፊት ባይገኝም እንኳን፤ ሌሎች ዝርያዎች የሚኖሩበትን ምድር የዓለት አወቃቀር ለውጠናል።
በሰው ልጆች ምክንያት እንሰሳት ከቦታ ቦታ በመዘዋወራቸው እና እፅዋትም በመተከላቸው ለውጡ ይጎላል።
በ2018 የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ 96 በመቶ አጥቢ እንሰሳት ውስጥ ከሚካተቱ መካከል የሰው ልጆች እና ከብቶች ይገኙበታል።
በምድር ላይ ከሚገኙ በራሪ እንሰሳት መካከል ሁለት ሦስተኛው እንደ ዶሮ ያሉ የሰው ልጆች ያላመዷቸው እንሰሳት ናቸው።
በዓመት ውስጥ ከ75 ቢሊዮን በላይ ዶሮዎች ይታረዳሉ።
ዶሮን ጨምሮ የሌሎችም በራሪ እንሰሳት ቅሪተ አካል ለወደፊት ሲገኝ ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም።
በዩናይትድ ኪንግደም የሌስተር ዩኒቨርስቲ የቅሪተ አካል ተመራማሪ ጃን ዛላስዊዝ እንደሚሉት፤ የሰው ልጆች ሥነ ሕይወትን በመለወጥ የዝግመተ ለውጥ አካሄድን ለውጠዋል።
"ለወደፊት የሚመጡ ዝርያዎች እኛ ምን እንደሆንን ለማወቅ የተደራረበውን ቅሪት ይመለከታሉ" ይላሉ።
የሰው ልጆች እንዴት ይታወሳሉ?
ፕሮፌሰር ጃን እንደሚሉት፤ በየቀኑ የሰው ልጆች የሚጠቀምባቸው መገልገያዎች በቅሪተ አካል ምርምር ወቅት ይገኛሉ።
የለስላሳ መጠጥ መያዣ ጠርሙስ፣ የመኪና ማቆሚያ ወይም ሱሪ ሊሆን ይችላል ለወደፊት የሚገኘው። እነዚህ ቅሪቶች ቴክኖፎሲልስ ይባላሉ።
በአውሮፓውያኑ 2020 የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በዓመት 30 ጊጋቶን ቁሳቁስ ይመረታል። ይሄ ማለት እያንዳንዱ ሰው ከክብደቱ የበለጠ ቁሳቁስ በየቀኑ ያመርታል ማለት ነው።
በሕይወት ካሉ ነገሮች ይልቅ በሰው ልጆች የተሠሩ ግዑዝ ቁሳቁሶች በቁጥር ይበልጣሉ።
"በአሸዋ በመጠቀም ግንባታ ይከናወናል። በማጉያ መነጽር ሲታይ ለየት ያለ ቅርጽ አለው። የመንገድ ጫፍ ወይም ሕንጻ ሲታይም የሚስተዋለው ይሄ ነው" ይላሉ ባለሙያው።
አብዛኞቹ መገልገያዎች ለረዥም ዘመን ይዘልቃሉ። ፕላስቲክ እስከ ሚሊዮን ዓመታት እንደሚቆይ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ በ2050 ውቅያኖስ ውስጥ ከዓሣ በላይ ፕላስቲክ እንደሚከማች ይታመናል።
ግራፋይት ያላቸው ዓለቶች አራት ቢሊዮን ዓመታት መኖር ችለዋል። ስለዚህም በግራፋይት የሚሠራ እርሳስ ለዘመናት ይዘልቅ ይሆናል።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ ለመቶ ሚሊዮን ዓመታት የቆዩ እፅዋት ቅሪት አካልም ተገኝቷል።
ወረቀት የሚሠራው እፅዋት ከሚሠሩበት ንጥረ ነገር ስለሆነ ወረቀት መቶ ሚሊዮን ዓመታት የመኖር ዕድሉ ሰፊ ነው።
ፕሮፌሰር አዳም እንደሚያስረዱት፤ የሰው ልጆች በምድር ላይ እስካሁን ድረስ ብዙ ቅሪቶች ትተናል።
ይሄንን ቅሪት ለወደፊት የሚመጡት የላቀ የማሰላሰል ብቃት ያላቸው ዝርያዎች ያገኙታል ወይስ አያገኙትም? የሚለውን ጥያቄ በግልጽ መመለስ አይቻልም።
"ለወደፊት ምን ይመጣል? የሚለውን ለማሰብ አሁን ያለውን የቴክኖሎጂ ወጀብ ዘመን ማለፍ ይኖርብናል። በምድር ላይ ለውጥ የሚያስከትሉ ክስተቶች በቀጣይ አሥርታት ወይም ሚሊዮን ዓመታት ይከሰታሉ" በማለት ያስረዳሉ።