ሦስት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በወሲባዊ ትንኮሳ ምክንያት ከብሔራዊ ፈተና ተባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Mattu University
የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ በመቱ ዩኒቨርስቲ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል በሴት ተማሪዎች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል የተባሉ ሦስት ወንድ ተማሪዎች ከፈተና ተባረሩ።
ሰኞ ዕለት በጀመረው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመውሰድ ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት በመቱ ዩኒቨርሲቲ ከተሰባሰቡት ተማሪዎች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ የፈጸሙት ተማሪዎች ጉዳያቸው በኮሚቴ ታይቶ ነው ከፈተናው የተሰናበቱት።
ስለ ጉዳዩ ለቢቢሲ መረጃ የሰጡት የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዓለሙ ዲሳሳ (ዶ/ር) "መጀመረያ ላይ ሴቶቹ ተፈታኞች ከወንዶቹ ጋር ይጫወቱ ነበር" ብለዋል።
በሂደት ግን ወንዶቹ "ሴቶቹን አስገድደው ሳሟቸው። መነካት የሌለባቸውን የአካላቸውን ክፍል መንካት ጀመሩ" ብለዋል።
ከዚህ በኋላ አንደኛው "የሴቶቹን ሞራል በነካ መልኩ ልብሳቸውን በመግለብ ገላቸው እንዲታይ በማድረግ ትንኮሳ ፈጸመ" ሲሉ አክለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት የተማሪዎቹ ድርጊት ወንጀል መሆኑን ገልፀው፣ ሴት ተማሪዎቹ የደረሰባቸው ትንኮሳ እንዳሳሰባቸው እና "ግቢውን ለቀን እንሄዳለን" ማለታቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም ፈተናውን እንዲወስዱ እንዳግባቧቸው አስረድተዋል።
ወንጀሉን ከፈፀሙት ሦስት ወንድ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ ከምዕራብ ወለጋ አንዱ ደግሞ ከኢሉ አባቦራ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን ወደ መቱ ዩኒቨርስቲ የመጡ መሆናቸውንም ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።
ዩኒቨርስቲው ተማሪዎቹ ወሲባዊ ትንኮሳ መፈጸማቸው መረጃ እንደደረሰው በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ የፀጥታ ጥበቃ የሚያደርጉ የፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል።
በማስከተልም ተማሪዎቹ ፈተናውን እንዲያስፈጽም በተቋቋመው ከፍተኛ ኮሚቴ ፊት መቅረባቸውን ዶ/ር ዓለሙ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት መሰል ድርጊቶች የሴቶችን ሥነ ምግባር የሚጎዱ እና በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የተከለከሉ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Education
ኮሚቴው ወንጀሉን በፈፀሙ ተማሪዎች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ውይይት ማድረጉን የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረዋል።
ሦስቱን ተማሪዎች ወደ ፍርድ ቤት የማቅረቡ ሃሳብ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኗል ብለዋል።
ነገር ግን "በአሁኑ ጊዜ ተጎጂዎችን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረቡ ተማሪዎች በመሆናቸው በፍርድ ቤት ውጣ ውረድ አእምሮአዊ ችግርን ይፈጠርባቸዋል። በመሆኑም እነዚህ ታዳጊዎች በአገር አቀፍ የፈተና ሥነ ምግባር መመሪያ መሠረት ከፈተና ታግደዋል" ብለዋል።
በዚህም መሠረት የትምህርት ቢሮ ተወካይ ተማሪዎቹን በመውሰድ ወደ ቤተሰቦቻቸው የመመለስ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ብለዋል።
እርምጃው ከተወሰደ በኋላ በግቢው ውስጥ ያለው ሁኔታ ሲያስረዱም "በምሽት በግቢው ውስጥ ተሰብስበው የሚታዩ ወንዶች እና በምሽት ወደ ሴቶች ማደሪያ ለመሄድ የሚደረጉ ሙከራዎች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል" ብለዋል።
ወደ ፊት ከፈተና የተባረሩት ሦስት ተማሪዎች ምን ይሆናሉ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ "ትምህርት ሚኒስቴር ይወስናል፣ ነገር ግን እነዚህ ልጆች እንዳልተፈተኑ እና ምክንያቱ ይገለጻል።
"ወደፊት ባህሪያቸውን ካረሙ በሚቀጥለው ዓመት ፈተናውን እንደሚወስዱ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።
ተማሪዎች ወደ መቱ ዩኒቨርስቲ የመጡት የ12 ዓመት ልፋታቸውን ለማየት መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚደንቱ "ስለሆነም ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ ሥነ ምግባራቸውን በመጠበቅ፣ አእምሮአቸውን ከተለያዩ ሃሳቦች በማላቀቅ፣ በፈተና ላይ ብቻ በማተኮር ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማድረግ አለባቸው" ሲሉ መክረዋል።
የ12ኛ ክፍል አንደኛ ዙር አገር አቀፍ ፈተና ሰኞ ሰኔ 23/2017 ዓ.ም. መጀመሩን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቋል።
ሰኞ የተጀመረው የ2017 ዓ.ም. አገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዙር የፈተና መርሐ ግብር በወረቀት እና በበይነ መረብ የሚሰጥ ሲሆን እስከ ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም. ይቆያል።
ፈተናውን ለመውሰድ 608 ሺህ ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ 150 ሺህ የሚሆኑት በበይነ መረብ የሚፈተኑ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።















