የአዲሱ 'ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት' አስተዳደር ለባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ ተሰጠ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በዛሬው ዕለት የተመረቀውን የአማራ ክልሉ ሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ "እንዲያስተዳድሩ መወሰኑን" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

በደቡብ ወሎ ዞን፣ ሎጎ ሐይቅ ዙሪያ የተገነባው አዲሱ ሪዞርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው በተገኙበት ዛሬ ቅዳሜ ጥር 30/2018 ዓ. ም. ተመርቋል። የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል ሆነው ይህ ሪዞርት፤ በ13.3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ እንደሆነ ተገልጿል።

በውስጡም መኝታ ክፍሎችን እንዲሁም "ዘመናዊ እና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምግብ ቤቶች" እንደያዘ ተገልጿል። "የመዋኛ ገንዳዎች፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶችን እና የሄሊኮፕተር ማረፊያም" የፕሮጀክት ግንባታው አካል እንደሆኑ ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "የወሎን ተፈጥሯዊ ውበት፤ ዘመናዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን ከጠበቀ መሠረተ ልማት ጋር አጣምሮ የያዘ ድንቅ ፕሮጀክት ነው" ሲሉ ሪዞርቱን አሞካሽተዋል።

"መንግሥትን እና የግሉን ዘርፍ" በማስተባበር የተገነባው ይህ ፕሮጀክት ለሁለቱ አካላት "አጋርነት፣ ለፖሊሲ ቀጣይነትና ለረዥም ጊዜ ዕድገት ዘላቂ መሠረት" እንደጣለም ገልጸዋል።

ዐቢይ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግርም ሪዞርቱ የተገነባው "በገበታ ለትውልድ የግሉ ባለሀብት መንግሥትን አምኖ ባዋጣው ገንዘብ" እንደሆነ ተናግረዋል።

በሥሩ ከ15 በላይ ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው 'በላይነህ ክንዴ ግሩፕ' ባለቤት የሆኑት ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ፤ የሪዞርቱን ግንባታ ሥራ ማከናወናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

"በላይነህ ክንዴ ከከፈልነው፣ ከጠየቅነው አሻግሮ እና አስበልጦ ለሕዝቡ መሥራት ችሏል" ያሉት ዐቢይ፤ ይህንን ምክንያት በማድረግ ባለሀብቱ ሪዞርቱን እንዲያስተዳድሩ መወሰኑን ይፋ አድርገዋል።

"የለፋበት፣ የደከመበት፣ የሚወደው ማኅበረሰብ ስለሆነ ይህንን ሪዞርት ራሱ በላይነህ ክንዴ እንዲያስተዳድረው [ተወስኗል]" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የገበታ ለሀገር ገንዘብ ንድፍ አማካኝነት የተገነቡ የአራት ሪዞርቶች አስተዳደር በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር እንዲሆን መደረጉን ይታወሳል።

አየር መንገዱ ግንቦት 2016 ዓ. ም. ከተረከባቸው ሪዞርቶች መካከል በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኘው ጎርጎራ ኢኮ ሎጅ ይገኝበታል።

የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና እና ሃላላ ኬላ ሎጆች እንዲሁም የወንጪ ኢኮሎጅም አስተዳደራቸው በአየር መንገዱ ሥር ገብቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፉት ሳምንታት የገበታ ለትውልድ አካል የሆኑትን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘውን ደንቢ ኢኮ ሎጅ እና በሶማሌ ክልል የተገነባውን የሸበሌ ሪዞርት አስመርቀዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያው ደንቢ ኢኮ ሎጅ በሚድሮክ ኢትዮጵያ ግሩፕ እንደገነባ ተገልጿል።