ቱሪስቶች ሶፍ ዑመር ዋሻ ከደረሱ በኋላ ሳይጎበኙ የሚመለሱት ለምንድን ነው?

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ባለፈው ጥቅምት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሥራ ላይ ያሉ እና የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አስከትለው በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ለሦስት ቀናት የቆየ ጉብኝት አካሂደው ነበር።

ዐቢይ በዚህ ጉዟቸው ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምሥራቅ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጎብኝተው ነበር።

በአካባቢው እየተገነባ ያለው የዲንሾ ሎጅ እና በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ የተገለጸውን የሶፍ ዑመር ሎጅ ቱሪዝም ፕሮጀክትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት አካል ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ባለሥልጣናቱ እድሳት እንደተደረገለት በተገለጸው እና በመብራቶች ባጌጠው የሶፍ ዑመር ዋሻ ውስጥ ተቀምጠውም ሁለት ሰዓት ገደማ ጊዜ የወሰደውን "የሶፍ ዑመር ወግ" ሲያደርጉ ታይተዋል።

በዚህ ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት ዐቢይ፤ በባሌ ዞን የሚገኘው ሀብት በሚገባው ልክ ባለመልማቱ የተሰማቸውን ቁጭት ገልጸዋል።

ሶፍ ዑመር ዋሻን ይበልጥ ለቱሪዝም መስህብ ለማድረግ በተከናወነው ሥራ "እምብዛም አይታወቅም" ሲሉ የገለጹትን አዲስ የዋሻ ክፍል "ማግኘታቸውን" ጭምር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ 536 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሶፍ ዑመር ዋሻ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ቢሆንም በመሠረተ ልማት እጥረት እና በቦታው ርቀት ምክንያት ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸውን ጉብኚዎች ሲያስተናግድ ቆይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በባለሥልጣናቶቻቸው በባሌ ዞን ካደረጉት ቆይታ በኋላ የቱሪስቶች ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የአካባቢው አስጎብኚዎች ተናግረዋል።

በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተላለፉትን የባሌን የቱሪስት መስህብ ቪዲዮዎች የተመለከቱት ጎብኚዎች ግን የሶፍ ዑመር ዋሻ እስካሁን ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት አልመሆኑን አላወቁም።

ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ያነጋገራቸው የአካባቢው ምንጮች፤ በርካታ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች በየቀኑ ረዥም ርቀት ተጉዘው ወደ ዋሻው ከደረሱ በኋላ መጎብኘት እንደማይችሉ ሲረዱ እየተመለሱ መሆኑን ገልጸዋል።

ላለፉት በርካታ ዓመታት ሶፍ ዑመርን በማስጎብኘት ተግባር ላይ የተሰማራ አንድ አስጎብኚ፤ በየቀኑ ሁለት ወይም ሦስት ተሽከርካሪዎች ወደ ሥፍራው እንደሚመጡ ተናግሯል።

"በተለይ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ስለ ሶፍ ዑመር ከተናገሩ በኋላ ወደዚህ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ዋሻው ግን ለጎብኚዎች ክፍት አይደለም" ብሏል።

"ዋሻው ለጉብኝት ክፍት እንዳልሆነ ለሕዝብ መረጃ የሰጠ አካል የለም" የሚለው አስጎብኚው፤ በዚህም ምክንያት በቡድን መኪና ተከራይተው እና ረዥም መንገድ ተጉዘው የሚደርሱ ጎብኚዎች እየተመለሱ መሆኑን ያስረዳል።

"አገልግሎት አልጀመረም ተብሎ መነገር አለበት። ሰዎች በቴሌቪዥን ስላዩ ክፍት መስሏቸው ይመጣሉ። ተማሪዎች እና የተለያዩ ሰዎች በቡድን እንደ አዲስ አበባ እና አዳማ ካሉ ከተሞች ይመጣሉ" ሲል ሁኔታውን ገልጿል።

የሶፍ ዑመር ዋሻ እስካሁን ክፍት ባይሆንም "አንዳንድ ሰዎች በተለየ ሁኔታ ገብተው እንዲጎበኙ እየተፈቀደላቸው መሆኑ" ሌሎች ሰዎችን እያሳሳተ እንደሆነ ጠቁሟል።

ስለ ጉዳዩ ጥያቄ የቀረበላቸው የኦሮሚያ ቱሪዝም ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ፤ ጎብኚዎች የሶፍ ዑመር ዋሻ እድሳት ተጠናቆ ክፍት እስከሚሆን ድረስ በትዕግስት እንዲጠባበቁ ጠይቀዋል።

"እስከማውቀው ድረስ በዋሻው ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎች በፍጥነት እየተሠሩ ነው። ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ለጎብኚዎች ዝግ ነው። እስከዚያው ሕዝቡ በትዕግስት መጠበቅ አለበት" ብለዋል።

የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት በቂ መረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ከዋሻው ውጪ ያሉ መስህቦችን እንዲጎበኙም መክረዋል።

"ባሌ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች አሉት። ይህንን ዋሻ ለመጎብኘት የወጣ ሰው ባሌ ከደረሰ በኋላ ዋሻው ዝግ ስለሆነ ብቻ መመለስ የለበትም። እዚያው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን እና ዲንሾን እንዲጎበኙ እመክራለሁ" ብለዋል።

ባሌ ትኩረት ከተሰጠው ወዲህ ወደ ሥፍራው የሚጓዙ የውጭ እና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር መጨመሩን ምክትል ኮሚሽነሩ አንስተዋል።

ለቱሪስቶች የሚሆን በቂ ማረፊያ እንዲኖር ለማድረግ እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎችም አገልግሎት በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።

"የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሥፍራው የየቀኑ በረራ ስላለው በብዛት ጎብኚዎቸ ወደዚያ ይሄዳሉ። ባሌ ብዙ ቱሪስት የመሳብ አቅም አለው፤ በዚያው ልክ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ትልቅ ሥራ ነው" ብለዋል።