የአሜሪካ መንግሥት በሶሪያ እና ኢራቅ የሚገኙ የኢራን ዒላማዎችን ለመምታት ፍቃድ ሰጠ

ከቅርብ ቀናት በፊት የአሜሪካ ወታደሮች በሶሪያ የቅኝት ስራ ሲሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከቅርብ ቀናት በፊት የአሜሪካ ወታደሮች በሶሪያ የቅኝት ስራ ሲሰሩ

የአሜሪካ መንግሥት በሶሪያ እና ኢራቅ በሚገኙ የኢራን ዒላማዎችን ለመምታት የቀረበውን እቅድ አጸደቀ።

ሲቢኤስ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው የአየር ጥቃቶቹ በቀጣዮቹ ቀናት ይፈጸማሉ።

ይህ የተባለው በኢራን ይደጋፈል የተባለ የሚሊሻ ቡድን በጆርዳን በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ የድሮን ጥቃት ፈጽሞ ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ ነው።

አሜሪካ እስላሚክ ሬዚዝታንስ ኢን ኢራቅ የተባለውን ቡድን ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን ቡድኑም ጥቃቱን ማድረሱን አምኗል።

ይህ የሚሊሻ ቡድን በኢራን አብዮታዊ ዘብ እንደሚሰለጥን፣ እንደሚታጠቅ እና በገንዘብ እንደሚደገፍ የአሜሪካ መንግሥት ይገልጻል።

ኢራን ግን ከዚህ ቡድን ጋር ግንኙነት እንደሌላት እና ሦስት ወታደሮችን ከገደደለው እና 41 የሚሆኑትን ባቆሰለው ጥቃት ላይ ምንም ተሳትፎ እንደሌላት ገልጻለች።

የአሜሪካ ባለስልጣናት እንደሚሉት ተዎር 22 በመባል የሚታወቀውን የጦር ሰፈር ለማጥቃት ጥቅም ላይ የዋለው ሰው አልባ አውሮፕላን ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ እያዋለች የምትገኘው ኢራን ሰራሽ ድሮን ነው ይላሉ።

አሜሪካ ይህ ጥቃት እንደተፈጸመባት ፈጣን የሆነው ወታደራዊ የአጸፋ ምላሽ ተሰጣችለች ተብሎ ተጠብቆ ነበር። የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ላሎይድ ኦስቲን ወታደራዊ እርምጃው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ይፈጸማል ብለዋል።

“ለጥቃቱ ተጠያቂ የሆኑ ሰዎችን መለየት ቀላል ተግባር እንደማይሆን ሰዎች ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ። . . . ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መቆጣጠሪያ መንገዶች አሉን። ትኩረታችን ይህ ሆኖ ቆይቷል” ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢራን በሚገኙ የኢራን ታጣቂዎች ላይ ጨምር ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስዱ ከሪፓብሊካን የምክር ቤት አባላት ጫናዎች ሲደረጉባቸው ነበር።

የባይደን አስተዳደር ግን ኢራን ውስጥ ጥቃት በመፈጸም በቀጠናው ያለውን ውጥረት ማባባስ እንደማይፈልግ ይገልጻል።

አሁን የጸደቀው የጥቃት እቅድም መገኛቸው ኢራቅ እና ሶሪያ የሆኑ በኢራን የሚደገፉትን ለመምታት እንጂ በኢራን ውስጥ የሚገኙትን አይደለም።

የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ቁጥር ጨምሯል።

ለምሳሌ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያ በቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ በሚያልፉ ዕቃ ጫኝ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶችን እየፈጸሙ የንግድ ሥራዎችን አውከዋል።