በአሜሪካ በልደት ድግስ ላይ በተከፈተ ተኩስ ታዳጊው እህቱን አድኖ ሞተ

በአሜሪካ አላባማ ግዛት የ16ኛ ዓመት የልደት በዓልን ለማክበር በተሰባሰቡ ታዳጊዎች ላይ የጅምላ ተኩስ ከተከፈተ በኃላ አንደኛው ታዳጊ የእህቱን ህይወት አትርፎ መሞቱን ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

የ18 ዓመቱ ፊል ዶዴል ተኩሱ ሲከፈት 16ኛ ዓመት ልደቷን እያከበረች የነበረች እህቱን አሌክሲስ ዶዴል ገፍቶ ወደ መሬት በመጣል ህይወቷን መታደግ ችሏል።

አሌክሲስ ለወንድሜ “የነገርኩት የመጨረሻ ነገር ጠንካራ እንዲሆን ነው” ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።

በዴድቬል ከተማ ቅዳሜ ምሸት በተሰነዘረው ጥቃት አራት ሰዎች ሲገደሉ 32 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

አሌክሲስ ወንድሟ መሳሪያ ያለው ሰው እንዳለ ሲሰማ ሊታደጋት ወደ እሷ ማምራቷን ተናግራለች።

ተኩሱ ተከፍቶ እሷን ወደ መሬት ከገፋት በኃላ መለያየታቸውንም አክላለች።

ከጥቂት ጊዜ በኃላ እህትና ወንድም ዳግም ተገናኙ። የተገናኙት ግን ወንድሟ ለመሞት እያጣጠረና መናገር አቅቶት በክንዷ ላይ ሆኖ ቅንድቡን በማንቀሳቀስ ብቻ ነው።

ኤለክሲስም ትሁን እናቷ ላቶንያ አለን ተኩሱ የተከፈተበትን ምክንያት አያውቁም።

እናታቸው አሌን ልጄ “በሁሉም መንገድ” አኩርቶኛል ብላለች።

ሀዘኑ ክፉኛ እንደጎዳት የተናገረችው እናት “ልጄ በሚቀጥለው ወር ይመረቅ ነበር። ወደ ምርቃቱ ቦታ ከመሄድ ይልቅ ልጄን ለማየት ወደ መቃብሩ እሄዳለሁ” ብላለች።

በግርድፉ 3 ሺህ ነዋሪዎች ያሉበት ዴድቬል ከተማ የተፈጸመውን ይህንን ጥቃት ማን እንደፈጸመው እና ለምን እንደተፈጸመ ፖሊስ እስካሁን አልደረሰበትም።

ስለ ምርመራው ፖሊስ የሰጠው መረጃ ትንሽ ሲሆን ነዋሪዎች መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ ጠይቋል።

እናት አለን ጥቃቱ የተፈጸመው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች እንደሆነ ታምናለች።

በጥቃቱ ሌሎች የ17፣ የ19 እና የ23 ዓመት ሰዎችም ተገድለዋል።

በጥቃቱ ህይወቷን ያጣችው የ17 ዓመቷ ስሚዝ ዘመድ እና ጓደኞች ሟቿ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ልትመረቅ ተቃርባ እንደነበር ገልጸዋል።

ሌላኛው የ19 ዓመት ልጅ ኮሊንስ ደግሞ ስፖርተኛ የነበረ ሲሆን ጠበቃ የመሆን ህልም ነበረው።

የነ አሌክሲ እናት አለን ተኩሱ ከመከፈቱ በፊት የልደት ድግሱ ላይ ከተሳተፉት መካከል መሳሪያ የታጠቀ ሰው አለ የሚል ወሬ መስማቷን ትናገራለች።

በዚህም ምክንያት የጠፋውን መብራት በማብራት ወደ ሙዚቃ አጫዎቹ (ዲጄው) በመሄድ በድምጽ ማጉያ የጦር መሳሪያ የያዘ ሰው ካለ ከድግሱ እንዲወጣ ጠይቃለች።

የመለሰ ሰው ባለመኖሩ መብራቱን መልሳ ማጥፋቷን ትናገራለች።

ወዲያው ግን ትርምስ መፈጠሩን አሌክሲስ ትነገራለች።

“በድንገት የጦር መሳሪያ ድምጽ ሰማን እና ሁሉም ወደ በሩ መሮጥ ጀመረ። ሰዎች ይወድቁና ይጨኹ ነበር” ስትል ለቢቢሲ አስረድታለች።፥

አሌክሲስ ከስፍራው በወንድሟ እርዳታ ማምለጥ እንደቻለች ተናግራለች።

ነገሮች ሲረጋጉ ወደ ስፍራው ስትመለስ ወንድሟ ተተኩሶበት እንዳገኘች ገልጻለች።

በዚያ ወቅት ወንድሟ ብዙ ደም እንደፈሰሰው እና ነፍሱ እስክትወጣ አብራው እንደቆየች ተናግራለች።

የዴድቬል ከተማ ከንቲባ ጂሚ ፍራንክ ጉድማን ከጥቃቱ በኃላ ሆስፒታሉ ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል። ሁኔታው እሳቸው ከተረፉበት የቬትናም ጦርነት የሆስፒታል ግርግርም የከፋ እንደነበር አስረድተዋል።

“የሚያለቅሱ ሰዎች፣ ቆስለው ወደ ድንገተኛ ክፍል የሚገቡ ሰዎች ወይም አስክሬኖች እና በደም የጨየቀዩ ልብሶች መሬት ላይ ወድቆ ይታይ ነበር” ሰሉም አክለዋል።

እህቱን ከሞት የታደገው እና ከሶስት እህትና ወንድሞቹ ታላቅ የሆነው ፊል ደውዴል ስመ ጥር ስፖርተኛም ነበር። በስፖርተኛነቱ እና በታማኝ ጓደኝነቱ በአከባቢው ማህብረሰብ የማስታወሻ ፕሮግራም ተካሂዶለታል። ታዳጊው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሲሆን የስፖርት ትምህርት ዕድል አግኝቶ ጃክሶኒቭ ዪኒቨርሲቲ ሊገባ ነበር።

አሌክሲስ እሱ ሲጫወት ማየት ያስደስታት እንደነበርና በዚያም ይዝናኑ እንደነበር ተናግራለች። ሁልጊዜም በሩን ለሌሎች ይከፍት እንደነበርና እሱም ወደ እሷ ክፍል ይሄድ እንደነበርም ለቢቢሲ ገልጻለች። ሁልጊዜም ሲጣሉ ይቅርታ የሚጠይቀው እሱ ነበርም ብላለች።

ከዚህ በኃላ ልደቷ እንደዚህ እንደማይሆነም ተናግራለች።

ባለፈው እሁድ ለጥቃቱ ሰለባዎች ማስታወሻ የተደረገ ሲሆን የሚማሩበት ትምህርት ቤት ባንዲራም ዝቅ ብሎ ተውለብልቧል። በመታሳቢያ የቆሰሉ ሰዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቇጠሩ ሰዎች ታድመዋል።

የአሌክሲስ ወንደም የተገደለበትን ጥቃት ጨምሮ በዚህ ዓመት ብቻ በአሜሪካ 160 የጅምላ ተኩስ የተፈጸመ ሲሆን በዚህም በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ገን ቫዮለንስ አርካይቭ የተባለ ተቋም ገልጿል።