የአፍሪካ አገራት በሩሲያ ወረራ ላይ ለምን ተከፋፈሉ?

ሩሲያን የሚደግፍ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩስያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች አንድ ዓመት ቢደፍንም በአፍሪካ አገራት መካከከል ስለ ጦርነቱ ያለው አስተያየት ከጅማሮው ብዙ አልተቀየረም።

ከቀናት በፊት በነበረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያን የሚያወግዝ፣ የዩክሬንን የግዛት አንድነትን የሚደግፍ እና ሰላም የሚሰፍን ውሳኔን የደገፉት ሰላሳ ሃገራት ብቻ ናቸው።

ይህም ማለት ከጦርነቱ ጅማሮ ከነበረው የተለየው በሁለት ድምጾች ብቻ ነው።

ባለፈው ጉባኤ ድምጸ ተአቅቦ አድርገው የነበሩት ማዳጋስካር እና ደቡብ ሱዳን የድጋፍ ድምጻቸውን ሰጥተዋል። ሞሮኮ ባለፈው ዓመት የተመድ ጉባኤ ያልተገኘች ቢሆንም በሀሙሱ እለት ግን የድጋፍ ድምጽ ሰጥታለች።

የሩሲያን ወረራ ባወገዘው በዚህ ጉባኤ ድምጸ ተአቅቦ ካደረጉት ውስጥ ግማሽ ያህሉ የአፍሪካ አገራት ናቸው። ባለፈው ዓመት ከዩክሬን ጎን ቆማ የነበረችው ጋቦን በዘንድሮው ድምጸ ተአቅቦ በማድረግ ከ15ቱ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ሆናለች።

እነዚህ አገራት ከሩሲያም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ከምትደገፈው ዩክሬን ጋር እንደማይወግኑ በመግለጽ አቋማቸውን በይፋ ያሳወቁ ናቸው።

ጦርነቱ ከተጀመረ ባሉት ወራት ውስጥ የምዕራባውያን አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የዩክሬን እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአፍሪካ አገራት የሚያደርጓቸው ጉብኝት በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም አገራቱ ከአቋማቸው ንቅንቅ አላሉም።

ከተመድ ጉባዔ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከዩጋንዳ አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ቢወያዩም በመጨረሻ ሰዓት የተደረገው ይህ ንግግር ከአቋማቸው ፈቀቅ አላደረጋቸውም።

በዚህ ሳምንት የአሜሪካ ቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደንን የአፍሪካ የመጀመሪያ ጉብኝቷን ያስተናገደችው ናሚቢያም እንዲሁ አቋሟ ተመሳሳይነት አሳይቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ምዕራባውያኑ ለዩክሬን ድጋፍ ለማሰባሰብ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የገጠማቸውን ዲፕሎማሲያዊ ፈተናዎች አምነው “መብራት እንደ ማጥፋትና ማብራት አይደለም” ሲሉም ለአትላንቲክ ተናግረዋል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከቻይና እና ሩሲያ ጋር የ10 ቀናት ወታደራዊ ልምምድን እያስተናገደች ያለችው ደቡብ አፍሪካ አቋሟ ከሩሲያ የራቀ ነው የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የሩሲያና ዩክሬን ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ከሩሲያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ለምን ጠነከረ?

አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ከሶቭየት ኅብረት ጋር ለአስርት ዓመታት የዘለቀ ግንኙነት ነበራቸው። በአውሮፓውያኑ 1991 የሶቭየት ኅብረት መፈራረስ ተከትሎ ግንኙነታቸው ከሩሲያ ጋር ቀጥሏል።

በርካታ የአፍሪካ የነጻነት መሪዎችም የነጭ አናሳ አገዛዝ እና ቅኝ ግዛትን ለመታገል ሩሲያ ያደረገችው የጦር መሳሪያ አቅርቦት እና ወታደራዊ ስልጠና ቁልፍ ሚናም እንዳለው ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ አፓርታይድ ጋር በነበረው ትግል የአሜሪካ መንግሥት የአሁን ገዥ የአፍሪካ ናሺናል ኮንግረስ ፓርቲ አሸባሪ ቡድን ብሎ ሰይሞታል።

የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ መሪዎቹም በአሸባሪነት ተፈርጀዋል።

ማንዴላ በአውሮፓውያኑ 1993 የአገሪቱ የመጀመሪያ ጥቁር ፕሬዚዳንት ሆነው የኖቤል የሰላም ሽልማት ቢያሸንፉም እስከ 2008 ድረስ በአሜሪካ የአሸባሪነት ዝርዝር መዝገብ ውስጥ ተካትተው ቆይተዋል።

“በእርግን በሚያሳዝን ሁኔታ፣ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ አሜሪካ ለአፓርታይድ አገዛዝ ድጋፍ ነበራት። ታሪክ አይጠፋም ያውም በአንድ ጀንበር” ሲሉም ብሊንከን ለአትላንቲክ ጨምረው ተናግረዋል።

ነገር ግን የቅጭ ግዛት ታሪክ አሁን ከሩሲያ ጋር ያለውን የጠነከረ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አይገልጽም፣ ቢያንስ ለአንዳንድ አገሮች።

የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንደ ኤርትራ እና እንደ ማሊ ያሉ ሁለቱም በአብዛኛው ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተገለሉ አገራት ሩሲያ አጋር አድርጋቸዋለች።

በቅርቡ የሩሲያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭን ካስተናገዱ የአፍሪካ አገራት መካከል ሲሆኑ ሁለቱም ዩክሬንን የደገፈውን የተመድን ውሳኔ በመቃወም ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

የማሊ ወታደራዊ መሪዎች ባለፈው አመት በአገሪቱ የተሰማሩት የፈረንሳይ ወታደሮች አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ካዘዙ በኋላ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ጽንፈኛ ቡድን ለመዋጋት እንዲረዳቸው የሩስያውን ቅጥረኛ ቡድን ዋግነርን ጋብዘዋል።

ሌሎች ሰባት የአፍሪካ አገራት ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኢስዋቲኒ፣ ጊኒ ቢሳው እና ካሜሩን በተመድ ውሳኔ ላይ ምንም ዓይነት ድምጽ አልሰጡም። ከዚህ ቀደም ሴኔጋል፣ ታንዛንያና ኢኳቶሪያል ጊኑ ድምፀ ተአቅቦ አድርገው ነበር።

ከ50 በላይ አገሮችን በያዘችው አህጉር ለወረራው ያለውን ምላሽ እና ስሜት አጠቃሎ መናገር አይቻልም። እያንዳንዱ ሃገራት ለሰጡት ድምጽ የየራሳቸው ምክንያት ይኖራቸዋል።

ምንም እንኳን ውሳኔው በህጋዊ መንገድ አስገዳጅ ባይሆንም በሚቀጥሉት ወራት እና አመታት ውስጥ የጂአ ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ላይ የራሱን ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ ጥርጥር የለውም።