በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በጋዛ ታግተው ያሉትን ለማስለቀቅ ስምምንት እንዲደረስ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በጋዛ ታግተው የሚገኙ ሰዎችን እንዲለቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ለመጠየቅ አደባባይ ወጡ።
ይህ ሰልፍ በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ እና በሌሎች ከተሞች የተደረው የአገሪቱ ጦር ኤልዳ ካትዚር የተባለ ታጋች አስክሬንን ማግኘቱን ተከትሎ ነው።
አደባባይ የወጡ ሰዎች “አሁኑኑ ምርጫ ይካሄድ” እንዲሁም “ኤልዳ እናዝናለን” ሲሉ ደምጻቸውን አስተጋብተዋል።
ፖሊስ በቴል አቪቭ ተሰባስበው የነበሩትን ተቃዋሚዎች በኃይል ለመበተን ተገዷል።
ተቃዋሚዎቹ ሐማስ እና አጋሮቹ በጋዛ የያዟቸውን 130 ታጋቾች የእስራኤል መንግሥት ማስለቀቅ አለመቻሉ እንዳበሳጫቸው አስተያየት ሲሰጡ ነበር።
ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 28/2016 ዓ.ም. ይህ የተቃውሞ ሰልፍ ከመደረጉ ከሰዓታት በፊት፤ የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ታግቶ ወደ ጋዛ ተወስዶ የነበረው ኤልዳ ካትዚር አስክሬን በእስራኤል ጦር ተገኝቶ ነበር።
ሐማስ ከሦስት ወራት በፊት ባጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል ኤልዳ በሕይወት ታይቶ ነበር።
“ኤልዳ ካትዚር በእገታ ስር ሆኖ ለሦስት ወራት በሕይወት መቆየት ችሎ ነበር። ዛሬ ከእኛ ጋር መሆን ይችል ነበር፥። ዛሬ ከእኛ ጋር መሆን ነበረበት” በማለት ናኦም ፔሪ የተባለች የሰልፉ ተሳታፊ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የኤልዳ ካትዚር እህት ካርሚት ካትዚር ለወንድሟ ሞት የእስራኤል ባለስልጣናትን ተጠያቂ ማድረጓ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ አስተዳደር ላይ ቁጣውን አባብሷል።
ካርሚት በማሕበራዊ ገጿ ላይ የኔታኒያሁ መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደርስ ኖሮ ወንድሜ በሕይወት ከእኛ ጋር ይኖር ነበር ብላለች።
የዚህ የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎች ድምጻቸውን ለማሰማት በቴል አቪቭ የተገኙ ሰዎች ቁጥር 100ሺህ ነው ብለዋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ሰልፎች በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ስድስት ወሩን የደፈነው ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተደራዳሪዎች በካይሮ ለድርድር እንደሚቀመጡ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።
አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ ዳይሬክተር ቢል በርንስ እና የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ቢን አብዱልራሃማን አል ታኒ በዚህ ድርድር ተሳታፊ ይሆናሉ።
ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመ ወቅት 1ሺህ 200 ሰዎችን ገድሎ 253 አግቶ ወደ ጋዛ ወስዶ ነበር።
እስራኤል ደግሞ ለጥቃቱ በወሰደችው የአጸፋ ምላሽ እስካሁን አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ33ሺህ በላይ ሰዎችን ገድላለች።
እስካሁን ድረስ 129 ታጋቾች ያሉበት አይታቅም። ከእነዚህ መካከል 34 የሚሆኑ ሕይወታቸው አልፏል ተብሎ ይገመታል። ከእነዚህ መካከል ግን አስክሬናቸው የተገኘው የ12 ታጋቾች ብቻ ነው።








