ከአንድ ወር በላይ ተዘግቶ የቆየው የደብረ ብርሃን -ደሴ መንገድ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚከፈት ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, SM
ከአንድ ወር በላይ ተዘግቶ የቆየው የደብር ብርሃን - ደሴ መንገድ ከዛሬ መጋቢት 28/ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚከፈት የዞኑ ኮሙኒኬሽን ገለጸ።
መሥሪያ ቤቱ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስትን ጠቅሶ በማኅበራዊ ገጹ ላይ ባጋራው ጽሑፍ ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከየካቲት 16/2016 ዓ.ም አንስቶ ተቋርጦ የነበረው ከደብረ ብርሃን ደሴ የሚወስደው ዋና መንገድ ከዛሬ ጀምሮ ለመንገደኞች ክፍት እንደሚሆን አስታውቋል።
ኮማንድ ፖስቱ፣ መንገዱ እንዲከፈት የተወሰነው በአካባቢው ያለው የሰላም ሁኔታ በመሻሻሉ እና ኅብረሰተሰቡ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው ብሏል።
ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምሥራቅ 130 ኪሎሜትር ከምትርቀው የአማራ ክልል ፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው ደብረ ብርሃን ወደ ንግድ ከተማዋ ደሴ የሚወስደው መንገድ ላልተወሰነ ጊዜ ተዘግቶ እንዲቆይ የተወሰነው ኮማንድ ፖስቱ “ ፅንፈኛ” ያላቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል እንደሆነ ገልጾ ነበር።
“ፅንፈኛ” ሲል የገለጻቸው ኃይሎች እነማን እንደሆኑ ግን በስም አልጠቀሰም።
ሆኖም በአካባቢው የፋኖ ታጣቂዎች እንዲሁም መንግሥት ‘ኦነግ ሸኔ’ ሲል በሽብርተኝነት የፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ነጻናት ሰራዊት እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን እንደሚንቀሳቀሱ ይነገራል።
ከአዲስ አበባ ወደ ወደ የተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የሚወስደው ይህ ዋና መንገድ ከዚህ ቀደም በተከሰቱ ጥቃቶች፣ ግጭቶች፣ እገታዎችና “ያለአግባብ” በጸጥታ ኃይሎች በሚደረጉ የኬላ ፍተሻዎች ምክንያት ሲዘጋና ሲከፈት ነበር።
ለረዥም ጊዜ ተዘግቶ ሲቆይ ግን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዚህም ከመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ ደቡብ ወሎዋ ደሴ ከተማ፣ ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ወሎ እና ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ያለውን የንግድ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ አስተጓጉሎት ቆይቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም መንገዱ ተዘግቶ በቆየበት ወቅት ባጋጠማቸው የትራንስፖርት አገልግሎት እጦት ምክንያት በሕክምና እጦት ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች መኖራቸውንና ለኑሮ ውድነት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ትናንት መጋቢት 27/ 2016 ዓ.ም. ባጋራው መልዕክት የቀጠናው የሰላም ሁኔታ በመሻሻሉ እና ኅብረተሰቡ ጥያቄ በማቅረቡ መንገዱ ከዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 28/ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጓዦች ክፍት እንዲሆን መወሰኑን ገልጿል።
ሰላሙን ለማዝለቅ ኅብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል እና “ የጥፋት ኃይሎች” ወደ ተጠያቂነት እንዲቀርቡ ለማድረግ በጋራ እንዲሰራም ኮማንድ ፖስቱ ጥሪ አቅርቧል።
በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን ጨምሮ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ባለፈው ዓመት የተከሰተው ግጭት እስካሁን እልባት አላገኘም።
በዚህም ምክንያት የክልሉ ከተሞችን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች እንዲሁም አብዛኞቹን የክልሉን ከተሞች እርስ በርስ የሚያስተሳስሩ መንገዶች ሰላም እንደራቃቸው ናቸው።
ነዋሪዎችም በትራንስፖርት እጦት እና በደኅንነት ስጋት ምክንያት ለሕክምና፣ ለሥራ ጉዳይ፣ ለዘመድ ጥየቃ እንዲሁም የውጭ አገር ጉዞ ለማድረግ ወደ ክልሉ ትላልቅ ከተሞች እንዲሁም ወደ መዲናዋ ለመግባት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የአየር ትራንስፖርትን አማራጭ ማድረጋቸው ተስተውሏል።
ይህንን ለማድረግ አቅማቸው ያልፈቀደላቸው ሰዎችም ከእንቅስቃሴያቸው ለመገታት አሊያም የደኅንነት ችግር ያለባቸውን መንገዶች በስጋት ለማቋረጥ ተገደዋል።
ወራት ያስቆጠረው በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት የተቀሰቀሰው መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ነበር።












