ሕይወት ከመርዓዊ ግድያ በኋላ

የተቃጠሉ ባጃጆች

የፎቶው ባለመብት, Human rights watch

የምስሉ መግለጫ, የተቃጠሉ ባጃጆች

በአማራ ክልል ሰሜን ምዕራብ በምትገኘው መርዓዊ ከተማ የመከላከያ ኃይል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ ከፈጸመ ከሁለት ወራት በላይ አስቆጥሯል።

የመከላከያ ኃይል በመርዓዊ ከተማ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን እና ሌሎች የጦር ወንጀሎች ፈጽሟል ሲልም ሂውማን ራይትስ ዋች ዛሬ መጋቢት 26/ 2016 ዓ.ም ባወጣው የምርመራ ሪፖርቱ ገልጿል።

በአማራ ክልል ግጭት ከተቀሰቀበት ጀምሮ የፌደራል ኃይሎች በርካታ ጥሰቶችን ፈጽመዋል ሲል ተቋሙ የከሰሰ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ቢቢሲ የመርዓዊ ከተማ ከግድያው በኋላ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች ሲልም እንዲህ ቃኝቷታል።

****

መርዓዊ ከተማ በአማራ ክልል ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር በ35 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ‘የመስመር’ ከተማ ናት።

ባህር ዳርንና አዲስ አበባን የሚያገናኘው የፌደራል መንገድ ለሁለት የሚሰነጥቃት ከተማ ስትሆን፤ በ1940ዎቹ እንደተመሰረተችም ይነገርላታል።

ከቆጋ የመስኖ ግድብ በሰባት ኪ/ሜ ርቀት ላይ ምትገኘው መርዓዊ በነዋሪዎቿ ዓመቱን ሙሉ እሸት የማይጠፋባት “ለምለም” እንድትባል አድርጓታል።

በንግድ እንቅስቃሴዋ ደማቅ እንደሆነች የሚነገርላት መርዓዊ ከተማ የሰሜን ሜጫ ወረዳ ዋና ከተማ ከሆነች ሁለት ዓመትን እንኳ አልደፈነችም።

ከ52 ሽህ በላይ ሠዎች ኑሯቸውን የሚገፉባት መርዓዊ ጥር 20፤ 2016 ዓ/ም የገጠማት ዱብዕዳ ግን ደብዛዋን ስለማጥፋቱ ነዋሪዎቿ ይናገራሉ።

በከተማዋ በየዓመቱ የሚከበረውን የማርያም ክብረ በዓል ለማክበር ሽርጉድ ላይ ብትሰነብትም፤ በክብረ በዓሉ ዋዜማ ጥር 20 ሰኞ ዕለት የመንግሥት ኃይሎች በሰላማዊ ሠዎች ላይ በሰነዘሩት ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦችና የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከጥቃቱ ቀደም ብሎ ከማለዳው 12 ሰዓት አካባቢ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል “ከባድ ውጊያ” መደረጉን ተከትሎ ለሰዓታት በዘለቀ ጥቃት ከ50 እስከ 100 የሚደርሱ ሰዎች “ተረሽነዋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዚህ ጥቃት ማንነታቸውን ያረጋገጣቸው 45 ሠዎች ስለመገደላቸው በምርመራ ማረጋገጡን አስታውቋል።

ይህ ከሆነ ሁለት ወራት አልፈዋል። መንግሥት ካስተባበለው ከዚህ ጥቃት በኋላ የሟች ቤተሰቦችና ነዋሪዎች ሕይወትን እንዴት እየገፉ ነው? ከግድያው በኋላ ማሕበረሰቡንና መርዓዊን ምን ገጠማቸው?

“ካለ ቀን የማይሞት ሆኖ ነው እንጂ. . .”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወ/ሮ ጸሀይ* ጥር 20፤ 2016 ዓ/ም ሕይወታቸው ከተመሰቃቀለባቸው በርካታ የመርዓዊ ከተማ ነዋሪዎች መሀል ናት። ትዳር መስርታ የአብራኳን ክፋይ ካገኘች ገና የወራት እድሜ ብቻ ነበር የተቆጠረው።

የተኩስ ድምጽ ከተማዋን ሲንጣት ቤት ዘግተን ተቀመጥን ትላለች። የግንባታ ባለሙያ ከሆነው ባለቤቷ ጋር ትዳር ከመሰረተችም ገና አንድ ዓመቷ ነበር።

ተኩስ ልውውጡ ጋብ ማለቱን ተከትሎ በር ከፈትን የምትለው ወ/ሮ ጸሀይ፤ ሕይወቷ የተቀየረበትን ቅጽበት “ባልናገር ደስ ይለኝ ነበር” በማለት እንዲህ ትገልጻለች።

“መጀመሪያ የገቡት እኛ ቤት ይመስለኛል። [ባለቤቷን] ከቤት አውጥተው ተንበርከክ ሲሉት እንኳን ጊዜ አልነበረውም። የሁለት ወር ህጻን ታቅፎ [ነበር]፤ መንጥቀው አውጥተው ሲገድሉት ህጻኑን እስከሚያወርደው እንኳ አልቆዩም” በማለት ድርጊቱን ትገልጻለች።

ቤታቸው በር ላይ “ሰው እንኳ ቀና ብሎ አያይም ነበር” ያለችው የ32 ዓመት ባለቤቷ እንደተገደለባት የምትናገረው ወ/ሮ ጸሀይ፤ የሁለት ወር ህጻን የነበረው ልጃቸው በወከባው በመውደቁ የአንገት ጉዳት እንደደረሰበት ለቢቢሲ ተናግራለች።

በባለቤቷ ገቢ ላይ ተመስርተው ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር የምታነሳው ወ/ሮ ጸሀይ ከባለቤቷ ግድያ በኋላ “ካለ ቀን የማይሞት ሆኖ ነው እንጂ. . .” በማለት አዲሱን ሕይወት በአጭር ትገልጻለች።

“ከግድያው በኋላ የምኖረው ኑሮ ኑሮ አይደለም። . . . ለዕለት የሚበላ እንኳ የለኝም ማለት እችላለሁ። ምክንያቱም የእሱን [የባለቤቷን] እጅ አይቼ ነው የምተዳደረው። እኔ ብቻ ሳልሆን አባቱ ህመምተኛ ነው፤ እሱ ነበር [የሚጦራቸው]። እነሱ [የመንግሥት ኃይሎች ከአባቱ] ያስጣሉት ህጻን አንገቱ ተቀጭቶ ስላመመው እሱን ነው ወደዚህና ወደዚያ ስል የምውለው።

ግጭቱ የተነሳበት የከተማው አስተዳደር

የፎቶው ባለመብት, Human Rights watch

የምስሉ መግለጫ, ግጭቱ የተነሳበት የከተማው አስተዳደር

“እኔ ብቻ ብሆን ችግር የለውም፤ ልቋቋመው እችል ነበር። ነፍስ ያላወቀ ህጻን ሁለት ወር ማለት. . . እንዲያውም ጠንካራ ነኝ እስካሁን ቆሜ በመገኘቴ” ስትል ትናገራለች።

እንደ ወ/ሮ ጸሀይ የመጀመሪያ ልጇን ነፍሰ ጡር የነበረችው ባለቤታቸው የተገደሉባቸው አቶ ዝናቡ*፤ የቀደመ ኑሯቸውን ጥለው የትውልደ አገራቸው ገብተዋል።

የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ባለቤታቸው እንጀራ እየጋገረች እያለች “ግምባሯን” በጥይት ተመታ እንደተገደለች ተናግረዋል።

“እኔም ቤት ነበርኩኝ። ሁለት ወንዶች እያባረሩ መጥተው ሲያመልጧቸው እሷን ነው መትተዋት የሄዱት” በማለት ግድያውን የሚገልጹ ሲሆን፤ ባለቤታቸውን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ወደ ቤት ቢያስገቧትም ወዲያው ሕይወቷ እንዳለፈ ተናግረዋል።

“ጭንቅላቷን ስለተመታች፤ በዛ ላይ ነፍሰ ጡር ስለነበረች [ሳትቀበር] ማደር አትችልም” በመባሉ ከመርዓዊ 14 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በሚገኝ የትውልድ ቀበሌያቸው [ገጠር] የባለቤታቸውን አስከሬን በጋሪ ጭነው እንደተጓዙና ቀብር እንደፈጸሙ አቶ ዝናቡ ገልጸዋል።

በቀን ስራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ ሲሆን፤ ባለቤታቸው በተገደለችበት ቤት መኖር ከብዷቸው ኑሯቸውን ገጠር ስለማድረጋቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“. . . የሚያስፈልገኝን እቃዬንም ሄጄ አመጣሁ። እሷ እንደዛ ሆና ከሞተችበት ቤት መኖር አልቻልኩም። ህሊናዬም እምቢ አለኝ” ይላሉ።

“አባቱን ጧሪ ነበር” የሚሉት ወንድማቸው [ወ/ሮ ጸሀይ ባለቤት] የተገደለባቸው የመርዓዊ ነዋሪ ሕይወት ከወንድማቸው ህልፈት በኋላ ከባድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል። የአእምሮ ህክምና ማግኘትም ግድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

“ውስጤ ይረበሽ ነበር፤ ያየሁት [ነገር]፤ እሱም [ወንድማቸው] ቅን ነበር፤ ሳያየኝ ከዋለ ይደውላል፤ ግንበኛ ነበር፤ ተቀምጬ ሁለመናው ይመጣብኛል። በዚህ የተነስ [ሆስፒታል] ሄድኩ። ሌላም ተጨማሪ ህመም ነበረብኝ። . . . በሀዘኑ የተነሳ የተወሰነ ጉዳት እንደደረሰብኝ ነው የነገሩኝ። የእኔ ወንድም ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሆነውን ነገር በአእምሮዬ መሸከም አልቻልኩም” ይላሉ።

ሂውማን ራይትስ ዋች ከአንድ ወር በላይ በፈጀና 20 የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዐይን እማኞችንና ነዋሪዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጎ ዛሬ መጋቢት 26/2016 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ተቀዳሚ ምርመራው ጥቃቱን በሁከቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል በሚደረገው ውጊያ ንጹሃን ላይ የደረሰ እጅግ የከፋ ጥቃት ነው ብሎታል።

የካቲት 16፤ 2016 ዓ/ም በተመሳሳይ የመንግሥት ኃይሎች ስምንት ንጹሃን ዜጎችን መግደላቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።

የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር ሊቲታ ባደር የመንግሥት ኃይል በአማራ ክልል በንጹሃን ላይ የሚያደርሰው የጭካኔ ግድያ በክልሉ ሕግና ስርዓትን እያስከበርኩ ነው የሚለውን አቋሙን የሚቀጭ ነው ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ላይ በሚያርፈው የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት የንጹሃን ግድያ፣ በደል፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት እንደ ጦር ወንጀል ሊታይ ይችላል ብሏል።

መርዓዊ አሁን ላይ

ከግድያው በፊት ደማቅ የነበረችው መርዓዊ የንግድ ቤቶቿ ተከርችመዋል፤ ነዋሪዎቿም በስጋት ምክንያት ተሰደዋል፤ ንብረቶች ተዘርፈውባታል፤ ወድመውባታል፤ ድባቧም ስለመክሰሙ ነዋሪዎቿ ይናገራሉ።

“አሁንም ስጋት አለ” የሚሉ አንድ ነዋሪ፤ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ውጥረት እንዳለ ጠቅሰው፤ “አሁንም የከፋ ነገር ይፈጠራል የሚል ስጋት አለን” ይላሉ።

“በፍርሃት ነው የምንቀሳቀሰው። ጎረቤቶቼ ወጥተው ለመግባታቸው አያምኑም። እንኳን ያንን ቀን ያየ በወሬ የሰማ እንኳ ይከብደዋል” ትላለች ወ/ሮ ጸሀይ ።

“የከተማዋ ሁኔታ ጸጥ ያለ ነው። እንደ በፊቱ መሸጥ መለወጥ፤ እንደ በፊቱ እንቅስቃሴ [የለም]። በአስፓልት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው የሚንቀሳቀሱት። በዚህ ሰዓት [ከዚህ ቀደም] መርዓዊ ከተማ ገፋኸኝ ገፋኸኝ ነው የነበረው። ኢኮኖሚው በጣም የተሳለጠ ነበር” ሲሉ ከተማዋ ባዶ መሆኗን አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

“ከዓመት ዓመት እሸት የሚበላበት ነው። እሸት አይደለም ወደ ባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ የሚጫንበት ነው። ጎመኑ፣ በቆሎ እሸቱ፣ ድንቹ ምኑ ወደዬ ቦታው የሚጫንበት ነው። አንዳንዴ የወደብ ከተማ ሁሉ ይመስልሻል። በአጣናና ከሰል በጣም ታዋቂ ነው። አምስትና ስድስት ደቂቃ ጠብቀሽ ነው አስፓልት የምታቋርጭው። ምክንያቱም ባጃጁ ምኑ ወከባ ስለሆነ፤ ከሠው ጋር እተገፋፋሽ ነው የምታልፊው። አሁን ይሄ ነገር የለም” ሲሉ ሌላ ነዋሪ የከተማዋን ወና መሆንን ይገልጻሉ።

የመርዓዊ ከተማ ነዋሪዎች የጥር 20ውን ግድያ ተከትሎ ‘አቅም ያለው ወደ ባህር ዳር፤ አቅም የሌለው ወደ ገጠር’ ተሰዷል ይላሉ።

“ያለው ነገር ያስፈራል” የሚለው አንድ ነዋሪ ሦስት ጓደኞቹ መታሰራቸውን ተከትሎ መርዓዊን ለቆ እንዲወጣ ስለመገደዱ ይናገራል።

ግድያው ባለመቆሙ እና በቤት ለቤት አሰሳ እስር በመፈጸሙ ስጋት እንዳደረበት የሚገልጸው ነዋሪው፤ ባለቤቱንና ልጁን ወደ ገጠር በመላክ እሱ ወደ ባህር ዳር “ከተሰደደ” አንድ ሳምንት እንዳለፈው ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ምክንያቱም ምርጫ የለሽም። እኔ ሞትን ፈርቼ ተደብቄ ባለቤቴንና ልጄን እዛ አላስቀምጣቸውም። ነገሮች እስኪስተካከሉ ድረስ ገጠር ይሻላል ብዬ እነሱን ልኬ እኔ ወደዚህ [ወደ ባህር ዳር] መጣሁ። እንግዲህ ሰላም ሆኖ የምንገናኝ ከሆነ. . .” ይላል።

በባህር ዳር አንድ ክፍል ቤት ለሦስት ተከራይተው እየኖሩ እንደሆነ የሚናገረው ነዋሪው፤ ይህ የእርሱ ብቻ እጣ ፈንታ እንዳልሆነ ገልጿል።

“ሁላችንም ባለትዳሮች ነን፤ ሦስት ልጅ ያለው አለ፤ ሁለት ልጅ ያለው አለ። ሁላችንም በተመሳሳይ ልጆቻችንንና ሚስቶቻችንን [ወደ ገጠር] ልከን ነው የተገኘነነው። እነሱ ቀድመውኝ የገቡ ናቸው” ይላል።

ግድያውን ተከትሎ የመንግሥት ኃይሎች ከማሕበረሰቡ ጋር መነጋገራቸውን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፤ የሰላማዊ ሠዎች ግድያን ማስተባበላቸውን ተናግረዋል።

“የታጠቀውን ኃይልም የሚደግፍ፤ ጀሌውን መታን ነው የሚሉት። ‘የተወሰነ ንጹኃን ተመቷል፤ ለእነሱም በመከላከያ [አባሎቻችን] ላይ እርምጃ እንወስዳለን [በሚል]’ ለማስተባበል ነው። መቶ በመቶ የታጠቀ ኃይል እንዳጠፉ አድርገው ነው የሚናገሩት” ሲሉ መንግሥት ለግድያው ኃላፊነት እንዳልወሰደ ተናግረዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው የምርመራ ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በአማራ ክልል በፈጸማቸው ጥሰቶች ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የፌደራል ኃይሎች በመርዓዊ ከተማ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን እና የጦር ወንጀል ፈጽሟል ሲል የከሰሰው ሂውማን ራይትስ ዋች በክልሉ ግጭት ከተቀሰቀሰም ጀምሮ በርካታ ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብሏል።

ሂውማን ራይትስ ዋች በምርመራ ሪፖርቱ የመንግሥታቱ ድርጅትና የአፍሪካ ሕብረት ለዘግናኝ ጥቃቶች እጃቸው ያለበት ወታደራዊ መሪዎች እስካልተጠየቁ ድረስ ከኢትዮጵያ የሚላከውን አዲስ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ መሰረዝን እንዲያጤን ጠይቋል።

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ሕብረት የመርዓዊ ግድያን በማውገዝ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

[*ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል የተቀየረ]

ሂውማን ራይትስ ዋች ስለ መርዓዊ ግድያ

ጥር 20 ማለዳ ላይ የፋኖ ታጣቂዎች መርዓዊ ከተማ ገብተው በከተማዋ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የሰፈሩትን የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አባላት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ያስረዳል።

ጥዋት 12፡30 ላይ የተኩስ ድምጽ መሰማት የጀመረ ሲሆን ተኩሱን የሰሙ አንድ የንግድ ድርጅት ባለቤት “የፋኖ ታጣቂዎች የአስተዳደሩን ህንጻ መክበባቸውን እና እየተገነባ በነበረውም ህብረት ባንክ ህንጻ ፎቅ ላይም ለመውጣት እየሞከሩ እንደነበር” ለሂውማን ራይትስ ዋች ተናግረዋል።

ከዚያም ፋኖ እና መከላከያ ተኩስ ይለዋወጡ ጀመር እናም ግለሰቡ ሁኔታውን “ጥይት እየዘነበ ነበር” ሲሉም ነው የገለጹት። በሁለቱ ኃይሎች መካከል ለሰዓታት ያህል የቀጠለ ሲሆን ከረፋዱ 5፡30 አካባቢ የፋኖ ተዋጊዎች ከተማውን ለቀው ወጡ። በዚህ ውጊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ለሂውማን ራይትስ የተናገሩት ነዋሪዎች ቢያንስ ሁለት የፋኖ ታጣቂዎች መሞታቸውን ገልጸዋል።

የፋኖ ታጣቂዎች መውጣታቸውንም ተከትሎ ተጨማሪ ኃይል ወደ ከተማዋ መግባቱን እና ለጥቂት ጊዜ ጋብ ብሎ የነበረው ተኩስ እንደገና መሰማቱን ነዋሪዎች ያስረዳሉ። ተኩሱ ከአንድ ወገን ብቻ ይሰማ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ “በየመንደሩ እየዞሩ ነዋሪዎች ላይ እየተኮሱ እንደነበር ተረዳን” ይላሉ።

በዚያች ዕለት የመከላከያ አባላት “ፋኖ የት ናቸው?” እያሉ “ሲያሸብሯቸው እንደነበር” እና የተፈጸመውን ግድያ “አሰቃቂነትም” ነዋሪዎች ለሂውማን ራይትስ ዋች ገልጸዋል።

አንድ ነዋሪም ቄስ ይታይህ የሚባሉ ካህን እና ምስጋናው አማረ የተባለ ልብስ ሰፊ እና ሃብታም እምብያለ የተባለ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ወታደሮች ጎትተው ሲወስዷቸው መመልከቱን ገልጿል።

በኋላም አስከሬናቸውን መንገድ ላይ ተዘርግቶ ማየቱንም ይኼው ነዋሪ አክሏል።

ሌላ ነዋሪም እንዲሁ ቄስ ይታይህን ጨምሮ ሌሎች ነዋሪዎችን ወታደሮች መሬት ላይ በጉልበታቸው አምበርክከው ግንባራቸውን በጥይት ሲመቷቸውም መመልከቱን አስረድቷል።

በዚህች ዕለት አብዛኛዎቹ የተገደሉት ወንዶች ቢሆኑም የተወሰኑት ሴቶች መሆናቸውም የተናገሩት ነዋሪዎች ከነዚህም መካከል አትክልት በመንገድ ላይ በመሸጥ የምትተዳደር ሴት መንገድ ላይ ተገድላለች ብለዋል።

የበርካቶቹ አስከሬንም መንገድ ላይ እንደነበር የሚያስረዱት ነዋሪዎች አንዳንዶቹም መገደላቸውን ያወቁት በመንገድ ላይ አይተዋቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

አስከሬኖቹን አንስተውም ለመቅበር በሚሞክሩበት ወቅትም “የፋኖ አስከሬን ልትወስዱ ነው?” በሚል ተከልክለናል ብለዋል። በስፍራው የምትገኘው ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካህንም የአካባቢው ሽማግሌዎች ከመከላከያ ጋር እንዲነጋገሩ ከተላኩ በኋላም የተገደሉት ሰዎች አስከሬን መሰጠቱን ገልጸዋል።

ወታደሮች የፋኖ ታጣቂ የመለዮ ልብስ የለበሱ የሁለት ወታደሮችን አስከሬን ከለዩ በኋላ የሌሎቹን አስከሬን ቤተሰቦቻቸው እንዲያነሱ መፍቀዳቸውንም ሌላ የአካባቢ ነዋሪ መናገሩን የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት አስፍሯል።

አስከሬኖቹ ቶሎ እንዲቀበሩ ወታደሮቹ ጫና በማድረጋቸውም “ደም የተበላሸ ልብስ እንደለሰቡ፣ ሳይገነዙ በጅምላ መቀበራቸውንም” ካህኑ ለተቋሙ ገልጸዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋችም በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ አዲስ የመቃብር ስፍራ እንዳለ የሚያሳይ የሳተላይት ምስልም ማግኘቱን አመላክቷል።

በከተማዋ ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ እና ዝርፊያ ተከትሎም ነዋሪዎች ወደ ባህርዳር፣ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች መሸሻቸውም ተገልጿል። መውጣት ያልቻሉ ነዋሪዎች ፍርሃት እንደነገሰባቸው እና ከመከላከያም ትንኮሳ እንደቀጠለባቸውም ያስረዳሉ።

የፋኖ ታጣቂዎች የካቲት 16/ 2016 ዓ.ም እንደገና በከተማዋ ባለው መከላከያ ኃይል ላይ ጥቃት መፈጸማቸውንም ተከትሎም አጸፋዊ ምላሹ የከፋ ነበር ብለዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች ከዚያ ጥቃት ጋር በተያያዘ ስምንት ሰላማዊ ሰዎች ሳይገደሉ አልቀረም ብሏል። አንድ የ49 ዓመት ነዋሪ የልጃቸውን እና የሰባት ሰዎችን አስከሬን በባህረ ጥምቀት ሜዳ ላይ ማግኘታቸውም በዚሁ ሪፖርት ተካትቷል።

በነገታው ወደ ዩኒቨርስቲ ሊሄድ የነበረ የ23 ዓመት ልጃቸው እንደተገደለ የሚናገሩት አባት “ ልጄ መሳሪያ አልታጠቀም። ሸበጥ እንዳደረገ ነበር” ብለዋል።