የአልኮል ሱሰኝነትን ለመቆጣጠር ኬንያ የመጠጥ ቤቶችን ቁጥር ልትወስን ነው

ኬንያ የአልኮል አዘውታሪነትን ለመቆጣጠር በሚል በግዛቶቿ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ አልኮል የሚሸጡ መጠጥ ቤቶች ቁጥር ውስን እንዲሆን የወጣው ትዕዛዝ ተግባራዊ እንዲሆን አዘዘች።

የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻግዋ በአገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት መስተዳደሮች ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነውን “በአንድ ከተማ አንድ መጠጥ ቤት” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አዘዋል።

በተጨማሪም የአልኮል ሱሰኝነትን ለመቆጣጠር ምክትል ፕሬዝዳንቱ የመዝናኛ ስፍራዎች ክፍት መሆን ያለባቸው ከአመሻሽ 11 ሰዓት አስከ ምሽት አምስት ሰዓት ብቻ እንዲሆን አዘዋል።

ነገር ግን ይህ የኬንያ መንግሥት ትዕዛዝ በርካቶች የተለያዩ ጎጂ ኬሚካሎች ወደ ሚጨመሩባቸው እና በቤት ውስጥ ወደ ሚጠመቁ መጠጦች ፊታቸውን ሊያዞሩ ይችላሉ የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ግን በአሁኑ ወቅት በተለይ በማዕከላዊው የኬንያ ግዛቶች ውስጥ የአልኮል ሱሰኝነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ እርምጃ እንዲወሰድ አዘዋል።

“ይህንን ችግር በመጋፈጥ ቀጣዩን ትውልድ እንታደግ፣ ይህንን ካላደረግን ግን እንደ ማኅበረሰብ ችግር አለብን ማለት ነው” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ከአስተዳዳሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሪጋቲ ጋቻግዋ የግዛት አስተዳደሮች መጠጥ ቤቶች ማውንት ኬንያ በሚባለው አካባቢ ለበርካታ ወጣቶች በዕጽ እና በአልኮል ሰበብ መጥፋት ምክንያት በመሆናቸው የተሰጣቸው የሥራ ፈቃድ ጊዜ ሲያበቃ እንዳይታደስላቸው አዘዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ የወጣቱን ትውልድ ሕይወት እያበላሹ ነው ሲሉ የከሰሷቸው መጠጥ ቤቶች ብዛት በአካባቢው ካሉ ሱቆች በላይ መሆኑን በመግለጽ እርምጃው በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን አዘዋል።

ፖሊስ እና የግዛት አስተዳዳሪዎች የትኛውም የመዝናኛ ቦታ 24 ሰዓት እንዳይሰራ እንዲከለክሉ ያዘዙት ምክትል ፕሬዝዳንት ጋቻግዋ “ትውልድ እንዲጠፋ ከፈቀድን እንጸጸታለን፤ ስለዚህ አሁኑኑ እርምጃ እንውሰድ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአልኮል ሱሰኝነት በኬንያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ ወጣቶችን በመሳብ ለጉዳት እያደረገ በመሆኑ ነው መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እርምጃ መውሰድ እንዲጀምር የተገደደው።