ከሰሞኑ ቲክቶክን ያጥለቀለቀው ‘ዕድለኛ ሴት ነኝ’ ብሎ የማመን ዕሳቤ ሕይወትን ይለውጣል?

የተጀመረው በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግቢያ ሰሞን ነው። ከ80 ሚሊዮን በላይ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች አይተውታል።

እናንተንም አጋጥሟችሁ ሊሆን ይችላል። ‘ዕድለኛ ነኝ፣ ሁሉም ነገር ይሳካልኛል’ እያላችሁ በመደጋገም ለራስችሁ እንድትናገሩ ያበረታታል። ከዚያም ስኬታማ እንደሆናችሁ ታምናላችሁ።

ሐሳቡ #Luckygirlsyndrome በሚል ሀሽታግ ነው ቲክቶክ ላይ እየተሽከረከረ ያለው።

በጎ አስተሳሰብ በጎ ነገር ያስገኛል የሚል አመለካከት ነው። በሳይንስ ባይደገፍም በርካቶች ያምኑበታል።

ቲክቶክ ላይ እየተዘዋወሩ ያሉት አብዛኞቹ ቪድዮዎች ዕድለኛ እንደሆኑ የሚናገሩ ሴቶች ናቸው። ዕድለኛ ነኝ ብሎ ማመን ሕይወታቸውን ቀና እንዳደረገው ይመሰክራሉ።

በተቃራኒው ሐሳብ ያልተዋጠላቸው ንቅናቄውን እየኮነኑት ይገኛሉ።

እንዲያው ‘በጎ በጎ አስቡ’ የሚለው ምክር የተለያየ የአእምሮ ሕመም ባለባቸው ሰዎች አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሚናገሩም አልታጡም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያ እንደሚሉት፣ መልካም ማሰብ ባይጠላም፣ በጎ በማሰብ ብቻ የማይፈቱ ችግሮች አሉ።

‘ሕይወቴ ተለውጧል’

ታም ኩር የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘቶች አዘጋጅ ናት። 22 ዓመቷ ነው። ስለ ሥራዋ መጥፎ ስሜት ውስጥ ሳለች የቲክቶኩን ንቅናቄ አይታ አኗኗሯን እንደለወጠች ትናገራለች።

በየቀኑ የ“እችላለሁ” ስሜት እንደሚሰጣት ታምናለች። ለራሷ ዕድለኛ ነኝ ብሎ መንገር ያቀደችው እንዲሳካ ማድረጉን ትመሰክራለች።

ማግኘት የምትፈልገውን እና የምትወደውን ነገር በየቀኑ ትመዘገባለች።

“መጀመሪያ ላይ ይሄ ነገር ግን የእውነት ይሠራል? ብዬ ተጠራጥሬ ነበር። ብዙ ሳነብና ምን ማለት እንደሆነ ስገነዘብ ግን የሚመኙትን ነገር ለማግኘት የሚረዳ መንገድ እንደሆነ ገባኝ። ነገሩ ዕድለኛ ሴት ነኝ ብሎ በማመን የዕድለኛ ሴትነትን ሕይወት መላበስ ነው” ትላለች።

እስካሁን ይህ አመለካከት አወንታዊ ውጤት ነው ያሳያት።

ሕልሟ ሞዴል መሆን ነበር። በቅርቡ ሥራ አግኝታለች። ትልቅ ስም ካላቸው ድርጅቶች ጋር የመሥራት ዕድልም ገጥሟታል።

“አመለካከቴን ስቀይር ነው ይሄ ሁሉ የሆነው። ይሆናል ብዬ ሳምን ሆነ። አመለካከቴን ከቀየርኩ ጀምሮ ነገሮች ባሰብኳቸው መንገድ እየሄዱ እንደሆነ ይሰማኛል” ትላለች።

‘ይሆናል ስንል ይሆናል’

ሆሊ ቶማስ 20 ዓመቷ ነው። የሕግ ተማሪ ናት። ከአምስት ዓመት በፊት ነበር በዚህ አመለካከት የተሳበችው።

በእግሊዝኛው Lucky Girl Syndrome እየተባለ የሚጠራውን ዕሳቤ ከሚያራምዱ መካከል ናት።

“አንድን ነገር በማሰብ እንዲሳካ እናደርገዋለን ብዬ አምናለሁ። ትንሽ ነገር ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ወደ ሥራ ስንሄድ ዛሬ የሚገጥመኝ የትራፊክ መብራት አረንጓዴ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ ሊሆን ይችላል። ይህም የዕድለኛነት ዕሳቤ ነው” ትላለች።

በዚህ አመለካከት የሚመሩ ሰዎች ያላሰቡትን በጎ ነገር ሁሉ ወደራሳቸው ሊስቡ እንደሚችሉ ነው ሆሊ የምታምነው።

የምትፈልገውን ነገር እንደምታገኘው ለራሷ እንደምትነግር እና “99 በመቶ እንደሚሳካ” ትገልጻለች።

በእርግጥ ሆሊ ታትሮ በመሥራትም ታምናለች። በሕግ ትምህርት “ዕድለኛነት” ብሎ ነገር የለም ትላለች።

‘ይሳካል’ ማለት ብቻውን ይበቃል?

መልካም አመለካከት ጠቃሚ እንደሆነ ብታምንም ቲክቶክን ያጥለቀለቀው ዕሳቤ ላይ ጥያቄዎች አሏት።

ሐሳቡ መነሻው፣ ለራሳችን የምንመኘውን ነገር እናገኛለን የሚል ነው።

“በሕይወታችን በቀና አመለካከት ብቻ የማንወጣቸው መሰናክሎች ይገጥሙናል። ይህ አመለካከት ብቻውን ብዙ እንደማያራምድ ሰዎች የሚረዱበት ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ነው ስጋቴ” ስትል ዶ/ር ካሮላይን ታስረዳለች።

አመለካከቱን የሚራምዱ ሰዎች የባለሙያዋን ስጋት ይጋራሉ።

አንዳንድ የዚህ ዕሳቤ አራማጆች ቤተሰቦቻቸው ሲታመሙ በጎ በመመኘት ብቻ ለውጥ ማምጣት ሲያቅታቸው ፀፀት ውስጥ ይወድቃሉ።

ሰዎች አንድ ነገር እውነት እንዲሆን ሲፈልጉ ራሳቸውን ማሳመን እንደሚችሉ ታስረዳለች።

አንዲት ሴት በቂ ዝግጅት ሳታደርግ ወደ ሥራ ቃለ መጠይቅ ብትሄድ፣ ዝግጅት ባለማድረጓ የተነሳ ከጠያቂዎቹ በኩል አሉታዊ ነገር በቀላሉ ልታስተውል ትችላለች።

በተቃራኒው በቂ ዝግጅት ያደረገች ሴት፣ ጠያቂዎቹ ፊት ላይ አዎንታዊ አገላለጾች ነው የሚታያት።

ስለዚህም ሁለቱም ሰዎች የሚያዩት እውነት፣ ነው ብለው ያመኑትን ነው።

የዚህ አመለካከት ተከታዮች ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሄዱ ሲቀሩ ራሳቸውን እንደሚወቅሱ በመግለጽ ንቅናቄውን የሚተቹ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች አሉ።

የሐሳቡ ተቺዎች በዋነኛነት የሚጠቅሱት አካል ጉዳተኞችን እና የሥርዓታዊ የዘር ጭቆና ሰለባዎችን ነው።

“ይሳካል ብላችሁ አስቡና ይሆንላችኋል” የሚለው አመለካከት አካታች እንዳልሆነ እና ከአቅማቸው በላይ የሆነ መሰናክል የገጠማቸውን እንደማያማክልም ይተቻሉ።

ሆሊ እንደምትለው “ዕድለኛ ሴት ነኝ ብለሽ እመኚ” ሲባል ለመቀበል እንደሚያስቸግር ብታምንም፣ ሰዎች እንዲሞክሩት ትገፋፋለች።

“ድንቅ ሰው ነኝ ብላችሁ ለሰዎች ንገሩ። ዕድለኛ ነኝ በሉ። ከዚያ ምን እንደሚፈጠር ታያላችሁ። ውጤት ካላሳየ መተው ትችላላችሁ። መጀመሪያ ግን ሞክሩት” ስትል ትመክራለች።