ቅጥረኛው ቫግነር ከሩሲያ ጦር ጋር እንዲቀላቀል የቀረበለትን ሃሳብ ውድቅ ማድረጉን ፑቲን አስታወቁ

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቅጥረኛው ቫግር ኃላፊ የቭጌኒ ፕሪጎዢን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) ከሩሲያ ጦር ጋር እንዲቀላቀል የቀረበለትን ሃሳብ ውድቅ ማድረጉን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።

የቅጥረኛው ቫግር ኃላፊ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ተዋጊዎቹ በሩሲያ ጦር ስር ሆነው እንዲያገለግል የቀረበለትን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ነው ፕሬዚዳንት ፑቲን ያስታወቁት።

ከሳምንታት በፊት በሞስኮ በተደረጉ ውይይቶች በርካታ የቫግነር ከፍተኛ የጦር አዛዦች ተዋጊዎቹ ከጦሩ ጋር የመቀላቀላቸውን ሃሳብ እንደደገፉ ኮመርሳንት ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ተዋጊዎቹን የሚመራው ከፍተኛ የቫግነር አመራር ሊሆን እንደሚችልም ሃሳብ የቀረበለት ፕሪጎዢን “ተዋጊዎቼ በዚህ አይስማሙም” የሚል ምላሽ እንደሰጠም ፑቲን ለጋዜጣው ተናግረዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የቫግነር ኃላፊ ፕሪጎዢን የሩሲያን መከላከያ ከፍተኛ አመራሮችን ልክ እንደሚያስገባና የትኛውንም ርቀት እንደሚሄድ መናገሩ ይታወሳል።

ኃላፊው በፕሬዚዳንት ፑቲን አስተዳደር ላይ የመራው እና ለ24 ሰዓታት የቆየው አመጽም ሳይሳካ ቀርቷል።

ለአጭር ጊዜ ከዘለቀው አመጽ በኋላ በተደረሰው ስምምነት ቅጥረኛ ተዋጊዎቹ ወደ መደበኛው የሩስያ ጦር እንዲቀላለቀሉ ወይም የሩሲያ አጋር ወደሆነችው ቤላሩስ እንዲያቀኑም ተነግሯቸዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ቫግነር ደም አፋሳሽ የሚባሉ ጦርነቶችን አካሂዷል።

ሆኖም የአሜሪካ ጦር ቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን ከአሁን በኋላ “በዩክሬን የሚካሄደውን የውጊያ ዘመቻ በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚና መጫወት እንደማይችልም” ግምገማውን አስቀምጧል።

ይህንን አስተያየት የሰጡት የፔንታጎን ቃለ አቀባይ ፓት ራይደር “አብዛኛዎቹ የቫግነር ተዋጊዎች አሁንም በሩሲያ በተያዙ የዩክሬን አካባቢዎች እንዳሉ ይታመናል” ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን ከኮመርሳንት ቢዝነስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በክሬምሊን በተደረገው ውይይት ፕሪጎዢንን ጨምሮ 35 የቫግነር ኮማንደሮች ተገኝተዋል።

ለተዋጊዎቹ በርካታ “የሥራ አማራጮችን” ያቀረቡላቸው ሲሆን በጦሩ ሥር ሆኖም በቫግነር ኮማንደር የሚመራ ክፍል እንደሚቋቋምም መንገራቸውን ገልጸዋል።

“በርካታ የቫግነር ተዋጊዎች ይሄንን ስናገር በመስማማት ራሳቸውን ሲነቀንቁ ነበር” ብለዋል ፑቲን።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም “ከፊት ለፊት ተቀምጦ ይህንን ሁሉ ያላየው ፕሪጎዢን ሃሳቡን ውድቅ በማድረግ “ ተዋጊዎቹ በዚህ ውሳኔ አይስማሙም” የሚል ምላሽ ሰጥቶኛል” ብለዋል።

በግል ወታደራዊ ድርጅቶች ላይ አገሪቷ ምንም ሕግ እንደሌላት የተናገሩት ፑቲን የቫግነር ዕጣ ፈንታንም በተመለከተ ፓርላማው ሊነገጋርበት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ፑቲን ሃሳብ አቅርበዋል።