ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፓሪስ ከተፈጸመው ቦምብ ጥቃት ጀርባ ነበር የተባለው ግለሰብ ከ43 ዓመት በኋላ ተፈረደበት
በፓሪስ የአይሁድ ስርዓተ አምልኮት መፈጸሚያ ስፍራ ወይም ምኩራብ ላይ የተፈጸመውና አራት ሰዎች የተገደሉበትን የቦምብ ጥቃት ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤት የሊባኖስና ካናዳ ጥምር ዜግነት ያለውን የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ከ43 ዓመታት በፊት ጥቃቱን አድርሷል ሲል በጥፋተኝነት በይኗል።
የፍርድ ቤቱ ዳኞች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 1980 የተፈጸመውን አሰቃቂ በሞተር ሳይክል የተጠመደ የቦምብ ጥቃት ያደረሰው የ69ዓመቱ ሃሰን ዲያቢ ነው ሲሉ ደምድመዋል።
በዚያ ጥቃት አራት ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ 38 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ዲያብ ብያኔውን የተቃወመ ሲሆን ፍርድ ቤትም ላለመቅረብ አሻፈረኝ ብሏል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ የእድሜ ልክ እስራት በይኖበታል።
አቃቤ ህግ ግለሰቡ ከቦምብ ጥቃቱ ጀርባ እንዳለ “ከጥርጣሬ በላይ” ነው ሲል ገልጿል። የግለሰቡ ደጋፊዎች ፍርዱ ፍትሃዊ አይደለም ሲሉ አውግዘዋል።
ከ48 ዓመታት በፊት የተፈጸመው የፖሪስ ምኩራብ ጥቃት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በፈረንሳይ አይሁዶች ላይ የተፈጸመ የመጀመሪያው ጥቃት ሲሆን ተከትለው በመጡት አመታት በመካከለኛው ምስራቅ ታጣቂዎች ላደረሷቸው ጥቃቶች እንደ መነሻ የሆነ ነው።
ለአስርት ዓመታት የቆየው ይህ የፍርድ ሂደት መደናገሮችን ያስተናገደበት ጊዜ ቢሆንም ወንጀሎች ፍትህ ሳያገኙ እንዳይረሱ ያደረገም ነው ተብሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1993 የካናዳ ዜግነት ያገኘው ዲያብ የፍልስጤም የዘር ሀረግ ያለው ሲሆን በካናዳ ኦታዋ የማህበረሰብ ሳይንስ መምህር ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1999 ጥቃቱ ከተፈጸመ ከ20 ዓመት በኋላ ግለሰቡ ተጠርጣሪ እንደሆነ ይፋ ሆኗል።
ከ8 ዓመታት በኋላ ፈረንሳይ የእስር ማዘዣ ብታወጣም ካናዳ አሳልፋ ለመስጠት እስከትስማማ 2014 ድረስ አልታሰረም ነበር።
ሆኖም በ2018 በቂ ማስረጃ የለም በሚል መዝገቡ እንዲዘጋና ተከሳሹም ወደ ካናዳ እንዲሄድ ተፈቅዶለታል።
በመጨረሻም በ2021 ለፈረንሳይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ መቅረቡን ተከትሎ በፈረንሳይ የመጀመሪያ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቷል።
ያኔ የጀመረው የፍርድ ሂደት በዚህ ወር ተጠናቋል።
ወደ ፈረንሳይ ያልተመለሰው ዲያብ በሌለበት የሚካሄደውን ችሎት ከመጀመሪያም ሲቃወመው ቆይቷል።
ጥፋተኛ ተብሎ መፈረዱ ካናዳ ዳግም አሳልፋ እንድትሰጥ ጥያቄ ይቀርብላታል ማለት ነው። ሆኖም የመሳካት ዕድሉ አጠራጣሪ ሆኗል።
ፍርዱን ተከትሎ የሁሴን ዲያቢ ደጋፊዎች የካናዳ መንግስት ዳግም አሳልፎ እንዳይሰጥ ጠይቋል።
ጉዳዩን ሲመለከተው የነበረው ፍርድ ቤት ከሶስት ሳምንታት በላይ የሚታወቁ እውነታዎችን ሲመረምርና የዲያቢስን ማንነት ሲመረምር ቆይቷል። በተጨማሪም ሰውዬው በተሳሳተ ማንነት የተከሰሰ ነው የሚል ምላሽም ሲያደምጥ ነበር።
በሌላ በኩል የመጀመሪያው የምርመራ ቡድን አባላት አንዳቸውም በህይወት በሌሉበት ሁኔታ ጥቃት አድራሹን አይተነዋል ያሉ ሰዎች ከ40 ዓመታት በኃላ ያስታወሷቸው ነገሮች ተአማኒ አድርጎ መቀበል ከባድ እንደሆነ ሲገለጽ ነበር።
ያኔ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተደረገው የመነሻ ምርመራ የ‘ኒዎ’ ናዚ አቀንቃኞችላይ ያተኮረ ሲሆን በፖለቲከኞች ሰላማዊ ሰልፎች ሲደረጉ ነበር።
ሆኖም ጽንፍ በረገጡ የቀኝ አክራሪዎች የተነሳው ይህ ሃሳብ ሃሰት እንደሆነ ተገልጾ ጥቃቱ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ያለው ግንኙነት ላይ አተኮረ።
ጥቃት አድራሹም አሌክሳንድራ ፓንዳራዩ በሚል ስም ሀሰተኛ የቆጵሮስ ፓስፖርት እንዳለው ተደርሶበታል።
በሌላ የአውሮፓ ሀገር በኩል ወደ ፈረንሳይ እንደገባና የትልቅ ቡድን አባል እንደሆነ የሚታመነው ግለሰብ ሞተር ሳይክሉንም ከፓሪስ እንደገዛው ታውቋል።
ጥቃቱ ከአንድ የፍልስጤም ልዩ ተልዕኮ ጋር ግንኙነት እንዳለው ቢጠረጠርም እንደ አውሮፓውያኑ በ1999 ከሶቪየት ህብረት የመነጨ እንደሆነ በተገመተ አዲስ መረጃ ተኩረቱ ወደ ሁሴን ዲያብስ አመዝኗል።
ፖሊስ ጥቃቱ በተፈጸመ ወቅት አቅራቢያ ተከሳሹ የነበረውን እንቅስቃሴ፣ በሆቴል የነበረውን ቆይታና ሌሎች ማስረጃዎች በማጣመር ነበር ለፍርድ ያቀረበው።