ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ በተከፈተ ተኩስ 10 የአንድ ቤተሰብ አባላት ተገደሉ
በደቡብ አፍሪካ ቤታቸው ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸው የአንድ ቤተሰብ 10 አባላት መገደላቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ፒተርማሪትዝበርግ ከተሰኘው ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ትላንት አርብ በደረሰባቸው ጥቃት ከተገደሉት የቤተሰብ አባላት ሰባቱ ሴቶች ናቸው።
የደቡብ አፍሪካ የፖሊስ ሚኒስትር ቤሄኪ ሴሌ አንድ ተጠርጣሪ በፖሊስ ተተኩሶበት መገደሉን እንዲሁም ሌሎች ሁለት ሰዎች መታሰራቸውንና አንድ ተጠርጣሪ እየተፈለገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ግድያው የተፈጸመበት ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።
ደቡብ አፍሪካ በከፍተኛ ቁጥር ግድያ ከሚፈጸምባቸው ሀገራት አንዷ ናት።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ተከትሎ ለፖሊስ በማሳወቃቸው ጉዳዩ ተደርሶበታል።
የፖሊስ ሚኒስትሩ ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል የ13 ዓመት ልጅ እንደሚገኝ ገልጸው ወንጀሉ የተፈጸመበት ቦታ የሚያሳቅቅ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ በምስራቃዊ የደቡብ አፍሪካ ክፍል ካውዙሉናታላ ግዛት በምትገኘው ኢምባሊ የተሰኘች አነስተኛ ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ “ሁለት ሰው ታስሯል፣ አንዱ ተጎድቷል፣ አንደኛው አምልጧል። ሶስት መሳሪያዎችም ተገኝተዋል።”
ከጥቃቱ በኋላ አንድ ህጻን ልጅ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች የፖሊስ አባላት መስለው ወደ ቤት ውስጥ መግባት እንደቻሉ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፖሊስ ተጠጣሪዎቹ ከተሸሸጉበት የባህል ህክምና መስጫ ቦታ መያዛቸውን የገለጸ ሲሆን የተገደለው ተጠርጣሪ በፖሊስ ለረጅም ጊዜ ሲፈለግ የነበረ እንደሆነ አስታውቋል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት አከባቢ በደቡብ አፍሪካ ተደጋጋሚ ግድያ ከሚፈጸምባቸውና መፍትሄ ሊያገኙ ካልቻሉ አከባቢዎች አንዱ ነው።
በደቡብ አፍሪካ በዚህ ሳምንት የጅምላ ግድያ ሲፈጸም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ባለፈው ሀሙስ በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል በምትገኘው የወደብ ከተማ አራት ሰዎች ተኩስ ተከፍቶባቸው ተገድለዋል።
በጥር ወርም በዚያው ደቡብ አፍሪካ በልደት ድግስ ላይ ስምንት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ባለፈው ዓመት ደግሞ በምሽት መዝናኛ ቤት ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት 15 ሰዎች ተገድለዋል።