ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፡ ሁለቱ ሀገራት የሰላም ስምምነት ይፈርሙ ይሆን?
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ይያዙ እንጂ በዩክሬን ያለውን ጦርነት “በአንድ ቀን” እንደሚቋጩት ቃል ገብተዋል።
ትራምፕ ይህን ዕቅዳቸውን እንዴት እንደሚያሳኩት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም። ነገር ግን ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ በርካታ ተንታኞች ትራምፕ ጦርነቱን ሊቋጩት ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው።
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዩክሬን እና ሩሲያን ወደ ውይይቱ ጠረጴዛ ሊያመጧቸው እንደሚችሉ ይታሰባል። ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ጥንቃቄ ባልጎደለው ንግግራቸው በሚመጣው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጦርነቱ “በዲፕሎማሲያዊ መንገድ” ሊቋጭ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
ለመሆኑ ሁለቱ ሀገራት ለሰላም ስምምነት ይቀመጡ ይሆን? ይህስ መቼ ሊሆን ይችላል?
አድካሚው ጦርነት
የጦር አውድማ ላይ ሩሲያ የበላይነቷን እያሳየች ትገኛለች። የሩሲያ ወታደሮች የዩክሬንን ግዛቶች እየተቆጣጠሩ ወደፊት በመገስገስ ላይ ናቸው።
በተለይ በምሥራቃዊው ዶንባስ ኻርኺቭ ግዛት በምትገኘው ኩፕያንስክ ከተማ እና ሰሜን ምሥራቅ በምትገኘው ዛፖሪዢያ ከተማ የሩሲያ ኃይሎች ወደፊት እየገሰገሱ ይገኛሉ።
ባለፈው ጥቅምት ሩሲያ 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆን የዩክሬን ግዛትን በቁጥጥር ሥር አውላለች። ይህ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ትልቁ ግዛት ነው።
ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ እንደሚሉት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ከተሰጠው የዩክሬን ግዛት 27 በመቶው በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ይገኛል። በአውሮፓውያኑ 2014 በሩሲያ ቁጥጥር ሥር የሆኑት ክሬሚያ እና ሌሎች የምሥራቅ ዩክሬን አካባቢዎችን ይጨምራል።
ዋና ከተማዋ ኪየቭን ጨምሮ ሱሚ፣ ኻርኺቭ እና ኦዴሳ በየቀኑ የቦምብ እና የድሮን ጥቃቶች እያስተናገዱ ነው።
ሞስኮ በሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት የደረሰውን ጥቃት ለመመከት ዝግጅት እያደረገች እንዳለ ይነገራል። ይህን ለማገዝ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መሰማራታቸውም ተሰምቷል። ዩክሬን ባለፈው ነሐሴ ነው ያልተጠበቀ ጥቃት በመሰንዘር የኩርስክን ግዛት በመያዝ ለመደራደሪያ ልትጠቀመው ያሰበችው።
ሩሲያ ወደ ድርድሩ ብትመጣ እንኳ የበላይነቱን ይዛ መቅረብ ትሻለች። የዩክሬን ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚያምኑት ክሬምሊን ከድርድሩ በፊት ሰፊ ግዛት ለመያዝ እየጣረች ነው። ይህን እያደረገች ያለችው ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሀገራቱ ለድርድር እንዲቀመጡ ሊያደርጉ ይችላሉ በሚል ግምት ነው።
ፕሬዝደንት ፑቲን፤ ዶኔትስክ እና ሉሀንስክ ግዛቶችን ከተቻለም የክልል ከተማ የሆነችውን ዛፖሪዢያን መጠቅለል ይፈልጋሉ።
ዩክሬን የወታደር እጥረት አለባት። በርካታ ወንዶች ወደ ጦርነት ሜዳ መሔድ አይመርጡም። ላለፈው ሁለት ዓመት ተኩል ሲዋጉ የከረሙ ወታደሮች ደግሞ ድካም ላይ ናቸው።
የዩክሬን ሕዝብ በጠቅላላው በጦርነቱ ተዳክሟል፤ ተሰላችቷል። የቦምብ ውርጅብኝ አዲስ ነገር አይደለም፤ መብራት በየጊዜው ይቆራረጣል፤ በርካቶች ደህና እንቅልፍ ከተኙ ከራርመዋል። ክረምት እየመጣ ነው። በሚቀጥሉት ሳምንታት ጠንካራ ብርድ እና በረዶ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሩሲያ ጋር የሚደረግ የሰላም ድርድር የሚባለውን ሐሳብ ዩክሬናውያን አይቃወሙትም። ይህ ማለት ግዛቶችን ማጣት እና ወደፊት የድንበር ጉዳይ አሳሳቢ ቢያደርገውም እንኳ የሰላም ድርድሩን የሚጠሉት አይመስልም።
ራዙምኮቭ ማዕከል ባለፈው ጥቅምት ያወጣው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከሦስት ዩክሬናውያን አንዱ የሰላም ድርድሩን ይደግፉታል። ባለፈው ዓመት ይህ ቁጥር ከአምስት አንድ ነበር።
ባለፈው ጥቅምት የወጣ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ ዩክሬናውያን ጦርነቱን ስለማሸነፋቸው ጥርጣሬ ገብቷቸዋል። ነገር ግን አብዛኛው ሰው አሁንም ሩሲያን ማሸነፍ እንደሚችሉ ነው የሚያስበው።
የትራምፕ ዕቅድ
ትራምፕ የአሜሪካን ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል ሰላም ሊያሰፍን ይችላል የተባለውን ዕቅድ በርካቶች በጉጉት እየተጠባበቁት ይገኛሉ።
ዶናልድ ትራምፕ ከድላቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ ብዙም ዝርዝር ያለው ነገር አልተናገሩም። “ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጋር ጠንክረን እንሠራለን። ይሄ መቆም አለበት። ሩሲያ እና ዩክሬን ማቆም አለባቸው” ነበር ያሉት።
በወቅቱ የአሜሪካ መገናኝ ብዙኃን ትራምፕ ከፑቲን ጋር በስልክ አውርተዋል፤ የሩሲያው ፕሬዝደንት ጦርነቱን እንዳያካርሩት አስጠንቅቀዋል ብለው ቢዘግቡም ክሬምሊን ይህን ዘገባ አጣጥሏል።
የዩክሬን ተንታኞች እንደሚያምኑት ምንም እንኳ የትራምፕ ዕቅድ ቅርፅ ባይይዝም የትራምፕ ቡድን ሁሉን ነገር አዘጋጅተው እየተጠባበቁ ይሆናል።
ያም ሆነ ይህ የትራምፕ ዕቅድ ጦርነቱን ማስቆም ነው ይላሉ ‘ኒው ዩሮፕ’ የተሰኘው የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተቋም ኃላፊ አልዮና ሄትማንቹክ።
“ጦርነቱን ማስቆም። የኔቶ አባል የመሆን ጥያቄን ማስቆም። የገንዘብ እርዳታን ማስቆም። ብቻ ሁሉን ነገር ማስቆም ነው ፍላጎታቸው” ሲሉ አልዮና ያስረዳሉ።
ምሑሯ እንደሚሉት ይህ ‘ስትራቴጂ’ ከባይደን አስተዳደር ጋር ይህን ያህል ልዩነት ያለው አይደለም። ልዩነቱ በባይደን ዘመነ መንግሥት ዩናይትድ ስቴትስ የሰላም ድርድር ሐሳብ መምጣት ያለበት ከዩክሬን ነው የሚል መሆኑ ነው። አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገው የገንዘብ እርዳታም እንዳለ ሆኖ።
ከዲሞክራቶቹ በተቃራኒ ትራምፕ ልዩ የዩክሬን መልዕክተኛ በመሾም ድርድሩን መምራት ይፈልጋሉ። ይህ ለዩክሬን መልካም ዜና ነው። የዩክሬን ባለሥልጣናት አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር መጥቶ ሥራውን እስኪጀምር ቸኩለዋል። ሒደቱ ቀላል እንደማይሆን ግን ያውቁታል። የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሒደቱ ለሩሲያም ቀላል አይሆንም ይላሉ።
የፍሎሪዳ የኮንግረስ አባል ማይክል ዋልትዝ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እንዲሆኑ በትራምፕ ታጭተዋል። የፍሎሪዳው ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ይህ ለዩክሬን መልካም ዜና ይመስላል። ምክንያቱም ሁለቱ ግለሰቦች ከዚህ ቀደም ቻይና፣ ሩሲያ እና ኢራን ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት ሲሉ ተደምጠዋል።
ተሿሚዎቹ ከዚህ ቀደም የሰጡትን አስተያየት ተንተርሶ መደምደሚያ ላይ መድረስ ከባድ ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ ቮሎድሚር ፌሴንኮ።
“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያሳዩት አቋም የትራምፕን አቋም የሚያንፀባርቅ ነው” ይላሉ።
የኪየቭ ባለሥልጣናት ከአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ጋር የተሻለ ግንኙነት ለመመሥረት ደፋ ቀና እያሉ ነው። ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ በባይደን የሥልጣን ዘመን መጨረሻ ሳምንታት የተሻለ ነገር እንደሚኖር ይጠብቃሉ።
ፕሬዝደንት ባይደን ዩክሬን ረዥም ርቀት የሚጓዙ ከአሜሪካ የተለገሱ ሚሳዔሎችን እንድትጠቀም ፈቃድ ሰጥተዋል። ባይደን ዩክሬን እኒህን ሚሳዔሎች ሩሲያ ውስጥ መጠቀም ትችላለች ብለዋል። ይህ የአሜሪካን በርካታ ዓመታት የፀና ፖሊሲ የሚንድ ትዕዛዝ ነው።
ነገር ግን እኒህ ሚሳዔሎች ጥቅም ላይ የሚውሉት በዩክሬን ቁጥጥር ሥር ባለችው ኩርስክ ግዛት ውስጥ ነው። እኒህ ጥቃቶች የሚቀይሩት ነገር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። ነገር ግን የሩሲያን ግስጋሴ ሊገቱት ይችላሉ።
የሰላም ድርድሩ ወዲያው ተጀምሮ ወዲያው ይጠናቀቃል የሚል ግምት የለም። ፑቲንም ሆኑ ዜሌንስኪ ጦርነቱ በሚፈታበት መንገድ ላይ የራሳቸው የሆነ አቋም አላቸው።