ዩክሬን በአሜሪካ ሚሳኤሎች ሩሲያ ውስጥ ዒላማ እንድትመታ ባይደን መፍቀዳቸው ቁጣ ቀሰቀሰቀ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን የአሜሪካን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ዒላማዎችን እንድትመታ መፍቀዳቸው ሩሲያን ውስጥ ቁጣ ቀሰቀሰ።

የሩሲያ መንግሥት ጋዜጣ የሆነው ሮስያስካያ ጋዜት “ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጣም የሚያስቆጣ እና ያልታሰበ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል። ይህም ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል” ሲል አስነብቧል።

ሩሲያዊው የሕዝብ እንደራሴ እና ለክሬምሊን ቅርብ የሆነው የሊበራል ዴሞክራሲ ፓርቲ ኃላፊ ሊዮኒድ ስላትስኪ ውሳኔው “ወደ ከፍተኛ ግጭት ያመራል” ብለዋል።

ሩሲያዊው ሴናተር ቭላድሚር ዳባሮቭ “ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የሚያስገባ” ሲሉ ውሳኔውን ኮንነዋል።

ለክሬምሊን ቅርብ የሆነው ድረ ገጽ ኮምሶሞልካያ ፕራቭዳ “ይጠበቅ የነበረ ውጥረት ማባባስ” ሲል አስተያየት ሰጥቷል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እስካሁን ምንም አላሉም።

የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “እንዲህ ያለ ውሳኔ ከተላለፈ ውጥረቱን ያባብሰዋል። አሜሪካ በግጭቱ ያላትን ሚናም ይለውጣል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የባይደን አስተዳደር “ግጭቱን ለማባባስ” እየሞከረ ነው ሲሉም ከሰዋል።

ምዕራባውያን መሪዎች “ግጭቱን እያባባሰ ያለው የሩሲያ አስተዳደር ነው” ብለው ያምናሉ።

በቅርቡ ሰሜን ኮርያ ወታደሮቿ በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጦር ጋር ተሰልፈው እንዲዋጉ መላኳ ይታወሳል።

ባለፉት ወራት የሩሲያ መንግሥት አቋሙን ለምዕራባውያን ግልጽ አድርጓል።

ዩክሬን የምዕራባውያንን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች እንድትጠቀም መፈቀድ እንደሌለበት አስታውቋል።

ፈቃድ ከተሰጠ ግን “ሩሲያ በኔቶ አባላት እንደተቃጣ ቀጥተኛ የጦርነት ተሳትፎ” ትቆጥረዋለች ሲሉ ፑቲን አስጠንቅቀው ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ሩሲያ የኒክሌር ጦር መሣሪያ የምትጠቀምባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ለውጠዋል።

አሜሪካ እና አውሮፓ ዩክሬን የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች በሩሲያ ግዛት ላይ እንድትጠቀም መፈቀድ እንደሌለበት ለማስረገጥ ነበር ውሳኔውን ያሳለፉት።

ከአውሮፓ በተገኘ የረዥም ርቀት ሚሳኤል ዩክሬን ሩሲያ ላይ ጥቃት እንድትፈጽም ቢፈቀድ ሩሲያ ምን ታደርጋለች? በሚል ከዚህ ቀደም በጋዜጠኖች ተጠይቀው ነበር።

ፑቲን የሰጡት ምላሽ “መጀመሪያ የአየር መከላከያ መሣሪያዎቻችንን እናጠናክራለን። ከዚያም ሚሳኤላቸውን እናወድማለን። ግዛታችንን ለመምታት መሣሪያ መለገስን የሚመርጡ ካሉ እኛም በእነሱ አቅራቢያ ላሉ እና ዒላማ ሊያደርጓቸው ለሚችሉ አገራት መሣሪያ ልንሰጥ እንችላለን” የሚል ነበር።

የፑቲን የቅርብ አጋር ቤላሩስ ሩሲያ ምዕራባውያን አገራትን ዒላማ ለማድረግ ምዕራባውያንን ልትጠቀም እንደምትችል ጠቁመዋል።

የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ጉዳዩን ከምዕራባውያን ጋር እንደተነጋገሩበት ገልጸዋል።

“ረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ላይ ጥንቃቄ አድርጉ። የየመን ሁቲ አማጽያን መርከብ ላይ ጥቃት የሚያደርስ የባሕር ላይ መሣሪያ ከፑቲን ሊጠይቁ ይችላሉ። የረዥም ርቀት ሚሳኤል ዩክሬን እንድትጠቀም ፈቅዳችሁ ፑቲን በምላሹ ሁቲዎችን አስታጥቆ የአሜሪካ ወይም ዩኬ መርከብ ቢመታ ምን ይፈጠራል? ብያቸዋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

በሁለት ወራት ውስጥ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ይገባሉ።

ባይደን ለዩክሬን የሚያደርጉት የመሣሪያ ድጋፍ ላይ ትራምፕ ቅራኔ እንዳላቸው ፑቲን ያውቃሉ።

በባይደን ውሳኔ ላይ አሁንም የፑቲን አስተያየት እየተጠበቀ ነው።