መንገደኞችን በማጓጓዝ ቀዳሚዎቹ ግዙፍ አውሮፕላኖች የትኞቹ ናቸው?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤ350-1000 አውሮፕላን ከኤር ባስ ተረክቧል።

ይህ አውሮፕላን ከመንገደኞች አውሮፕላኖች መካከል በመጫን አቅሙ ትልቅ ከሚባሉት አንደኛው ነው።

አየር መንገዱ የኤ350 ቤተሰብ የሆኑ 21 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው።

በቀጣዮቹ ዓመታትም 14 ተጨማሪ ኤ350 አውሮፕላኖችን ለአየር መንገዱ እንደሚያስረክብ ኤር ባስ በድረገጹ ላይ አስፍሯል።

ከእነዚህ ውስጥ አስራ አንዱ ኤ350-900 ሲሆኑ፣ ሦስቱ ደግሞ ኤ350-1000 ናቸው።

ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት ነው የተባለው ይህ አውሮፕላን፣ 395 መቀመጫዎች ተገጥመውለታል።

አስካሁን ዓለማችን ላይ እስከ 800 ሰዎችን ማሳፈር የሚችሉ የመንገደኛ አውሮፕላኖች ለሰማይ በቅተዋል።

ለመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተረከበው አውሮፕላን ከዓለማችን የመንገደኛ አውሮፕላኖች አንጻር ምን ያህል ትልቅ ነው?

በመቀመጫ ብዛት ቀዳሚ የሆኑት 5 አውሮፕላኖችስ የትኞቹ ናቸው?

ኤር ባስ ኤ340

በአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠው የኤር ባስ ምርት የሆነው ኤ340 ነው። ከቁመቱ ረዘም፣ ከወርዱም ሰፋ ያለ እንደሆነ ይነገርለታል።

ኤ330 እና ኤ340 ከሚባሉት አውሮፕላኖች ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፣ ኤ300 የሚባለውን የአውሮፕላን ሞዴል መነሻ አድረጎ የተሠራ ነው።

የአውሮፕላኑ ዓይነት የሆነው ኤ340-300 የመጀመሪያውን በረራ ያደረገው እአአ በ1991 ነበር።

ኤ340 የመንገደኛ አውሮፕላኖች ከ12400 እስከ 14450 ኪሜ የመብረር አቅም ያላቸው ሆነው ለገበያ ቀርበዋል።

ኤር ባስ ኤ340ን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ያዋሉት ሉፍታንዛ እና ኤር ፍራንስ የተባሉት የጀርምን እና የፈረንሳይ አየር መንገዶች ናቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በርካታ ኤ340 አውሮፕላኖችን በሥራ ላይ ሲያውል የቆየውም ሉፍታንዛ አየር መንገድ ነው።

የአውሮፕላኑ ዓይነቶች የተለያየ መጠን ያላቸው መንገደኞችን የመጫን አቅም አላቸው። ኤ340-200 የሚባለው ዓይነት እስከ 375 መንገደኞችን የመጫን አቅም አለው።

ኤ340-300 የሚባለው እስከ 440 መንገደኞችን ሲያጓጉዝ ኤ340-600 ደግሞ 475 መንገደኞችን በአንዴ መጫን እንዲችል ተደርጎ ተገንብቷል።

ኩባንያው ኤር ባስ በቁጥር 377 የሚደርሱ ኤ340 አውሮፕላኖችን አምርቶ ለገበያ አብቅቷል።

በአውሮፓውያኑ 2012 ግን ይህንን የአውሮፕላን ሞዴል ማምረት ማቆሙን አስታውቆ ፊቱን ወደ ኤ350 ማዞሩን ይፋ አደረገ።

ኤር ባስ ኤ350ኤክስደብሊውቢ

በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውም በርዝማኔው የሚታወቀው ኤር ባስ ኤ350ኤክስደብሊውቢ ነው።

የዚህ አውሮፕላን የመጀመሪያ ዓይነት ከሆኑት ቀዳሚ የሆነው ኤ350-900 ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአየር የበቃው እአአ በ2013 ነበር።

የመንገደኞች አውሮፕላኑ የተለያዩ መቀመጫዎች ብዛቶች ያሉት ሲሆን፣ በርካታ ክብረወሰን የሰበሩ በረራዎችንም አከናውኗል።

ኤ350 የመንገደኞች አውሮፕላኖች ከ8 ሺህ 704 እስከ 15 ሺህ 372 ኪሎ ሜትር የመብረር አቅም ያላቸው ሆነው ለገበያ ቀርበዋል።

አውሮፕላን አምራቹ ኤር ባስ 521 የሚሆኑ ኤ350 አውሮፕላኖችን ለደንበኞቹ አስረክቧል።

የሲንጋፖር አየር መንገድ የበርካታ ኤ350 ኤር ባስ አውሮፕላኖች ባለቤት በመሆን ቀዳሚው አየር መንገድ ነው።

ኤ350-900 በአንድ ጊዜ እስከ 400 መንገደኞችን መጫን ይችላል።

ኤ350-1000 ደግሞ 480 መንገደኞችን በአንድ ጊዜ ከቦታ ወደ ቦታ ማጓጓዝ እንዲችል ተደርጎ ለገበያ ቀርቧል።

ኢትዮጵያ አየር መንግድ 20 ኤር ባስ ኤ 350-900ኤክስደብሊውቢ አውሮፕላኖች ሲኖሩት፣ 348 መንገደኞች የመያዝ አቅም አላቸው።

ቦይንግ 777

በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቀመቱ ረዥም እና ወረዱ ሰፊ የሆነው ቦይንግ 777 ነው። አውሮፕላኑ በመጠናቸው ትልልቅ የሚባሉ ሁለት ሞተሮች ተገጥመውለታል።

የዚህ አውሮፕላን ዓይነት ሆነው ቦይንግ 777-200 የመጀመሪያ በረራውን ያደረገው እአአ በ1994 ነበር።

ቦይንግ አስካሁን ድረስ የቦይንግ 777 ዓይነት ያላቸውን 1 ሺህ 700 አውሮፕላኖች ለደንበኞቹ አስረክቧል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የግዢ ጥያቄዎችንም ተቀብሎ በማስተናገድ ላይ ይገኛል።

ኤምሬትስ አየር መንገድ 166 የቦይንግ 777 ዓይነት አውሮፕላኖች ባለቤት በመሆን ከዓለም ቀዳሚው አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል።

የቦይንግ 777 የመንገደኞች አውሮፕላኖች ከ9 ሺህ 700 እስከ 15 ሺህ 843 ኪሎ ሜትር የመብረር አቅም ያላቸው ሆነው ለገበያ ቀርበዋል።

የዚሁ አውሮፕላን ቤተሰብ የሆነው ቦይንግ 777ኤክስ የሙከራ ጊዜውን አጠናቆ በቀጣይ ወራት ለበረራ ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ቦይንግ 777-200/200ኢአር በአንድ ጊዜ 440 መንገደኞችን መጫን የሚችል ነው።

ቦይንግ 777-300/300ኢአር ደግሞ 550 መንገደኞችን ጭኖ ከመነሻው ወደ መዳረሻው መብረር ይችላል።

በቅርቡ ለበረራ የሚበቃው ቦይንግ 777ኤክስ ደግሞ 426 ሰዎችን እንዲጭን ተደርጎ ወደ ሥራ ይገባል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራት ቦይንግ 777-300ኢአር እና 6 ቦይንግ 777-200ኤልአር አውሮፕላኖች አሉት።

የአየር መንገዱ ቦይንግ 777-200ኤልአር አውሮፕላኖች 321 መንገደኞችን የመያዝ አቅም ሲኖራቸው ቦይንግ 777-300ኢአር ደግሞ 365 ሰዎችን መጫን ይችላል።

አየር መንገዱ ለካርጎ አገልግሎት የሚጠቀምባቸው 10 ቦይንግ 777-200ኤልአርኤፍ አውሮፕላኖች እንዳሉት በድረገጹ ላይ አስታውቋል።

ቦይንግ 747

በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠው ስመ ገናናው ቦይንግ 747 ነው። ባለ አንድ ፎቅ የሆነው ቦይንግ 747 በርካታ ሰዎችን በመጫን በመላው ዓለም ታዋቂ ለመሆን በቅቷል።

ይህ የመጀመሪያው ባለአንድ ፎቅ አውሮፕላን እአአ በ1968 ለበረራ በቅቷል።

ይህ አውሮፕላን ከ8 ሺህ 560 እስከ 14 ሺህ 320 ኪሎ ሜትር መብረር እንዲችል ተደርጎ ተሠርቷል።

በሰዓት እስከ 939 ኪሜትር መጓዝ የሚችለው ይህ አውሮፕላን ከ59.6 እስከ 68.5 ሜትር ድረስ ርዝመት አለው።

ቦይንግ እስካሁን ድረስ የ747 ቤተሰብ የሆኑ አንድ ሺህ 574 አውሮፕላኖችን ለደንበኞቹ አቅርቧል።

አውሮፕላኑ በተለያዩ ዓይነቶቹ መንገደኞች የመጫን አቅሙም የተለያየ ነው።

ቦይንግ 747ኤስፒ በአንድ ጊዜ 400 መንገደኞችን ማጓጓዝ ይችላል። ቦይንግ 747-100 ደግሞ 440 መቀመጫዎች አሉት።

ቦይንግ 747-200ቢ እና ቦይንግ 747-300 በተመሳሳይ 550 መቀመጫዎች ተገጥሞላቸዋል።

ቦይንግ 747-400 በአንድ ጊዜ 660 መንገደኞችን እንዲጭን ተደርጎ ሲሠራ ቦይንግ 747-8 ደግሞ 605 ወንበሮች ተገጥመውለታል።

ኤር ባስ ኤ380

መንገደኞችን በመጫን አቅም ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው ኤር ባስ ነው።

መንገደኞችን በመጫን ቀዳሚ የሆነው ኤር ባስ ኤ380 ሰፊ ከመሆኑ በላይ አራት ሞተሮች ተገጥመውለታል።

ከተጠበቀው ጊዜ ዘግይት ብሎ ለገበያ የቀረበው ኤ380-841 የተባለው የአውሮፕላኑ ዓይነት በአውሮፓውያኑ 2005 ነው ለሥራ የበቃው።

የአውሮፕላኑን የሙከራ በረራ ያደረጉት የኤር ባስ ዋና አብራሪ የሆኑት ዣክ ሮሳይ ኤ380 አውሮፕላንን ማብረር ማለት “ሳይክል እንደመንዳት” ነው ሲሉ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

ኤር ባስ አውሮፕላኑን ለገበያ ያቀረበው ከቦይንግ 747 ጋር ለመፎካከር ቢሆንም ኩባንያው የጠበቀውን ያህል ውጤት ማግኘት አልቻለም።

የአውሮፓው የአውሮፕላን አምራቹ ኤርባስ ከቦይንግ 747 አንጻር የተቀበለው የግዢ ትዕዛዝ በስምንት እጥፍ ያህል ያነሰ መሆኑ አንደዋነኛ ማሳያ ነው።

የኤ380 አውሮፕላኖች ምርትም እአአ በ2021 እንዲቋረጥ ተደርጓል። እስከ 2021 መጨረሻ ድረስ ኤርባስ በመላው ዓለም ለሚገኙ ደንበኞቹ 251 ኤ380 አውሮፕላኖችን አስረክቧል።

የኤምሬትስ አየር መንገድ 120 የሚደርሱ ኤ380 አውሮፕላኖችን በመግዛት ቀዳሚው አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል።

ይህ አውሮፕላን ከ14 ሺህ 800 ኪሎ ሜትሮች በላይ ብረር እንዲችል ተደርጎ ተሠርቷል።

አውሮፕላኑ 72.7 ሜትር ርዝመት ሲኖረው በሰዓት 903 ኪሜ መብረር ይችላል።

ይህ መንገደኞችን በመጫን አቅም ቁጥር አንድ የሆነ አውሮፕላን እስከ 853 መንገደኞችን መጫን እንደሚችል ታውቋል።