ፕሬዝዳንት ባይደን አሁንም ኮቪድ-19 እንዳለባቸው ተገለጸ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኮቪድ-19 ከተገኘባቸው ከሳምንት በኋላ በድጋሚ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ አሁንም እንዳለባቸው ሐኪሞች ገለጹ።

የ79 ዓመቱ ባይደን በወረርሽኙ የተያዙት ከሳምንት በፊት ሲሆን፣ ከቀናት በኋላ ቀላል የበሽታውን ምልክቶች ካሳዩ በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ ነበር ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠው።

ፕሬዝዳንቱ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የበሽራው ምልክቶች ባይታዩባቸውም በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች ደኅንነት ሲባል እራሳቸውን እንዳገለሉ ይቆያሉ ተብሏል።

ባይደን በማክሰኞ እና አርብ መካከል በተደረጉላቸው አራት ምርመራዎች ውጤታቸው ኔጌቲቭ የነበረ ሲሆን፣ የቅዳሜው ምርመታራ ግን ቫይረሱ እንዳለ አመልክቷል።

ፕሬዝዳንቱ ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ የግል ዶክተራቸው ኬቪን ኦኮኖር በጻፉት ደብዳቤ፣ ባይደን በአሁኑ ወቅት ህክምና መጀመር እንደማያስፈልጋቸው ነገር ግን “በቅርብ የህክምና ክትትል” ስር እንደሚቆዩ አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው ሳምንት ወረርሽኙ እንዳለባቸው ከታወቀ በኋላ ፓክስሎቪድ የተባለ ፀረ ቫይረስ መድኃኒት እየወሰዱ የቆዩ ሲሆን፣ ይህም “በተወሰኑ” ህመምተኞች ላይ በሽታው “የማገርሸት” ውጤትን ሊያስከትል እንደሚችል ዶክተሩ ገልጸዋል።

በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ጊዜ ከጆ ባይደን ቀደም ብሎ የነበሩት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም በኮቪድ ተይዘው እንደነበር ይታወሳል።

የኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ በተስፋፋበት ባለፉት ሁለት ዓመታት ክፉኛ ካጠቃቸው አገራት መካከል አሜሪካ አንዷ ስትሆን፣ አስካሁን ድረስ ከ93 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በበሽታው ሲያዝባት ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁት ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።