የአዶልፍ ሂትለር ሰዓት ተቃውሞን ባስከተለ ጨረታ በ1.1 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

የአዶልፍ ሂትለር እንደነበረ የተነገረለት ሰዓት በ1.1 ሚሊዮን ዶላር በጨረታ ተሸጠ።

የናዚ ምልክት የሆነው ስዋስቲካ እና ኤኤች የሚል ምጽህረ ቃል የተቀረጸበትን ሰዓት የገዙት ግለሰብ ማንነት አልታወቀም።

አሜሪካ፣ ሜሪላንድ በሚገኘው አሌክሳንደር ሂስቶሪካል ኦክሽንስ በተባለው አጫራች በኩል የሂትለር ሰዓት መሸጡ አይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎችን አስቆጥቷል።

ከዚህ ቀደምም የተለያዩ የናዚ ቁሳቁሶችን ለጨረታ ያቀረበው ተቋሙ በበኩሉ፣ አላማው ታሪክን ጠብቆ ማቆየት እንደሆነ ገልጿል።

ናዚ ጀርመንን እአአ ከ1933 እስከ 1945 የመራው አዶልፍ ሂትለር ስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያንን ጨምሮ 11 ሚሊዮን ሰዎችን ጨፍጭፏል።

በጨረታ የተሸጠው ሰዓቱ በ1933 ለሂትለር በስጦታ የተሰጠ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።

ሂትለር የጀርመን መራሔ መንግሥት የሆነው በ1933 ነበር።

ሂትለር ተራራ ላይ ያስገነባው በርጎፍ የተባለውን ቤቱን በ1945 የፈረንሳይ ወታደሮች ሲወሩ ከሰበሰቧቸው ቁሳቁሶች አንዱ ይሄ ሰዓት ነው።

ሰዓቱ በተለያዩ ሰዎች እየተሸጠና እየተገዛ እስካሁን ቆይቷል።

ከሰዓቱ ጋር የሂትለር ባለቤት የኤቫ ብሩዋን ቀሚስም ለጨረታ ቀርቧል።

የናዚ ባለሥልጣናት በቢጫ ጨርቅ የተሠራ የዳዊት ኮከብና ‘ጁድ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት ልብስ ይዘው የሚያሳይ ምሥልም አለ።

‘ጁድ’ በጀርመንኛ አይሁድ ማለት ነው።

ናዚዎች አይሁዳውያን ቢጫ ቀለም ያለው መለያ እንዲያስሩ ያስገድዷቸው ነበር።

ይህን የሚያደርጉት አይሁዳውያን ተለይተው የጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ ለማድረግ ነበር።

34 አይሁዳውያን የማኅበረሰብ መሪዎች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ የሂትለርን ሰዓት ጨምሮ ሌሎችም የናዚ ቁሳቁሶች ከጨረታ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአውሮፓ አይሁዳውያን ማኅበር ሊቀ መንበር ራባይ ሜናቺም ማርጎሊን፣ ሰዓቱ መሸጡ “የናዚ ፓርቲ የቆመለትን አላማ የሚደግፉ ሰዎችን የሚያጀግን ነው” ሲሉ ተችተዋል።

“ከታሪክ መማር አለብን። የናዚ ቁሳቁሶች በሙዝየም ወይም በከፍተኛ የትምህር ተቋም ሊቀመጡ ይችላሉ። ይሄ ሽያጭ ግን እርባና ቢስ ነው” ብለዋል።

የአጫራቹ ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት ሚንዲ ግሪንስቲን፣ ከዚህ ቀደም ከጀርመን መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የጨረታው አላማ ታሪክን ጠብቆ ማቆየት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በጨረታ የሚሸጡት አብዛኞቹ ቁሳቁሶች በግለሰቦች ይዞታ የሚቆዩ አልያም የአይሁዳውያንን ጅምላ ጭፍጨፋ (ሆሎኮስት) ለሚዘክረው ሙዝየም የሚለገሱ እንደሆኑም አክለዋል።

“ታሪክ በጎም ሆነ እኩይ መጠበቅ አለበት። ታሪክን ካጠፋን ማስረጃዎችን እናጣለን” ብለዋል።

ሰዓቱ ለጨረታ ሲቀርብ ይሸጣል ተብሎ የተጠበቀው በሁለት ወይም በአራት ሚሊዮን ዶላር ነበር።