ፌስቡክ በጥላቻ ንግግር ምክንያት በኬንያ ሊታገድ እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

ፌስቡክ የጥላቻ ንግግር መስፋፋትን ለመከላከል ለወጡ ፖሊሲዎች የማይገዛ ከሆነ በኬንያ መንግሥት ሊታገድ እንደሚችል አንድ የአገሪቱ መንግሥት ተቋም አስጠነቀቀ።

በአገሪቱ ምኅበረሰቦች መካከል ትብብርና ስምምነትን በሚመለከት የሚሰራው ኮሚሽን ፌስቡክን በባለቤትነት ለሚያስተዳድረው ኩባንያ ሜታ፣ በጻፈው ደብዳቤ በግዙፉ የኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ቅሬታውን አቅርቧል።

ኮሚሽኑ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ በኬንያ ውስጥ ከሚካሄደው ምርጫ በፊት ፌስቡክ በመድረኩ ላይ በሚወጡ ይዘቶች ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር ደካማ ነው በሚል ለቀረበው ክስ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል።

ይህ የኮሚሽኑ ጥያቄ የቀረበው ግሎባል ዊትነስ እና ፎክስግሎቭ የተባሉት ቡድኖች ባካሄዱት ጥናት ፌስቡክ በመድረኩ ላይ የሚወጡ ይዘቶችን በመቆጣጠር በኩል የሚጠበቅበትን አላደረገም የሚል ሪፖርት ካወጡ በኋላ ነው።

“ፌስቡክ ብሔራዊ ደኅንነታችንን አደጋ ላይ እንዲጥል አንፈቅድም። ስለዚህም በሰባት ቀናት ውስጥ ላስቀመጥናቸው መመዘኛዎች የማይገዛ ከሆነ፣ ሥራው እንዲታገድ ሀሳብ እናቀርባለን” ሲሉ የኮሚሽኑ ኃላፊ ዶክተር ዴቪድ ማኮሪ ተናግረዋል።

ከ15 ዓመታት በፊት በኬንያ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ምርጫን ተከትሎ የተቋቋመው ይህ ኮሚሽን ፌስቡክን የማገድ ሥልጣን የለውም። ነገር ግን ፌስቡክ በሕግ የተቀመጡትን ደንብና መመሪያዎች የማያከብር ከሆነ የአገሪቱ መንግሥት ባለሥልጣናት እርምጃ እንዲወስዱበት የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል።

ግሎባል ዊትነስ እና ፎክስግሎቭ ባወጡት ሪፖርት ላይ ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ፣ በእንግሊዝኛ እና በስዋሂሊኛ የወጡ ግጭት ቅስቃሽ የማስታወቂያ ይዘቶችን ለመለየት አልቻለም ተብሏል።

ቡድኖቹ ምርመራውን ባደረጉበት ጊዜ በ2007 (እአአ) በተከሰተው ግጭት ወቅት ጥቅም ላይ ውለው የነበሩ በእንግሊዝኛ እና በስዋሂሊ ቋንቋዎች የተሰራጩ 20 የጥላቻ መልዕክቶችን ለይተው አቅርበዋል።

ሪፖርቱ እንዳለው እነዚህ በፌስቡክ በኩል እንዲሰራጩ የቀረቡት ማስታወቂያዎች አብዛኞቹ በመድረኩ ላይ እንዲቀርቡ ተፈቅዶላቸዋል።

ነገር ግን አንድ በእንግሊዝኛ የቀረበ መልዕክት ብቻ የፌስቡክን የጥላቻ ንግግር መመሪያን ያላከበረ ነው በሚል ውድቅ ተደርጓል።

ግሎባል ዊትነስ እንዳለው ማስታወቂያዎቹ ፌስቡክ ላይ ያልተሰራጩ መሆኑን ጠቅሶ፣ ነገር ግን ምንም አይነት ምርመራ ሳይደረግባቸው ማለፋቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጿል።

ፌስቡክ በምርመራው ሪፖርት ላይ በተባሉት ጉዳዮች ዙሪያ ምላሽ አልሰጠም።

የቴክኖሎጂ ተቋሙ ፌስቡክ በሐምሌ ወር ብቻ 37,000 መልክዕቶችን የጥላቻ ንግግርን በማሰራጨት እንዲሁም 42,000 ደግሞ በአገሪቱ በነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ከሚካሄደው ምርጫ አስቀድሞ ጥቃት እና ግጭት መቀስቀስን በተመለከተ የድርጅቱን ፖሊሲዎች በመጣስ እንዲነሱ ማድረጉን አሳውቋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መድረኩ ፌስቡክ በተጨማሪም 36,000 የፖለቲካ ማስታወቂያዎች የግልጽነት ደንቡን አላከበሩም በሚል ሳይቀበላቸው መቀረቱን ገልጿል።

የፌስቡክ የምሥራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ የፐብሊክ ፖሊሲ ዳይሬክተር ሜርሲ ንዴግዋ፣ ከኬንያ ምርጫ ጋር የተያያዙ ግጭቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚባሉ ይዘቶችን በቀላሉ ለመለየትና ለማስወገድ የሚያስችል የተጠናከረ የመቆጣጠሪያ ዘዴ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።