ግብፃዊቷ ቲክቶከር በሠራችው ቪድዮ ሰበብ ሳዑዲ ውስጥ ታሰረች

ግብፃዊቷ የማኅበራዊ ሚዲያ ኮከብ ታላ ሳፍዋን በሳዑዲ አረቢያ ታሰረች።

‘ወሲባዊ ይዘት’ ያለው መልዕክት በቲክቶክ አስተላልፈሻል ተብላ ነው ታላ የታሰረችው።

ቲክቶክ ላይ 5 ሚሊዮን፣ በዩቲዮብ ደግሞ 800 ሺህ ተከታዮች አሏት።

ከሰሞኑ የለቀቀችው ተንቀሳቃሽ ምሥል “የተመሳሳይ ጾታ ፍቅር ይዘት አዘል ነው” በሚል ስትተች ቆይታለች።

የወግ አጥባቂዋ ሳዑዲ አረቢያ ፖሊሶች፣ ተንቀሳቃሽ ምሥሉ የማኅበረሰቡን ሞራል ይነካል ሲሉ ከሰዋል።

ወጣቷ የማኅበራዊ ሚዲያ ኮከብ ወጣቶች ላይ ባነጣጠሩ መልዕክቶቿ፣ በጥቁር አጭር ፀጉሯና በቀልጣፋ አነጋገሯም ትታወቃለች።

ስለ ቴሌቭዥን መሰናዶች ይዘት፣ ስለ ፍቅር ግንኙነት፣ ስለ አሳፋሪ ገጠመኞች እና ሌሎችም ተከታዮቿ በሚጠይቋት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ቪድዮ ትሠራለች።

የምትለቃቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የተመልካቾችን ትኩረት በቀላሉ በሚስቡና አነጋጋሪ በሆኑ ርዕሶች ይታወቃሉ።

ሰዎችን በጨዋታ መልክ ማታለል (prank) እና ተመልካቾች አንዳች ድርጊት እንዲፈጽሙ ማግባባት (challenge) ሌሎቹ የግብፃዊቷ መለያ ናቸው።

ከሰሞኑ የለቀቀችው ቪድዮ ግን አነጋጋሪ ሆኗል።

አንድ ሳዑዲ አረቢያዊት ጓደኛዋን ስታዋራ ይታያል። ከዚያም ጓደኛዋን ወደ ቤቷ ትጋብዛታለች።

በሁለቱ መካከል የነበረው ልውውጥ ወሲባዊ መልዕክት አዘል ነው በሚል ነው ውዝግቡ የተነሳው።

ትዊተር ላይ፣ “ታላ ማኅበረሰቡን አስቀይማለች” በሚል ንቅናቄ ተጀምሯል።

ታላ በበኩሏ ወደ ቤቷ ከጋበዘቻት ሴት ጋር አንዳችም ወሲባዊ ግንኙነት እንደሌላትና ድርጊቷ በተሳሳተ መንገድ እንደተተረጎመባት በመግለጽ ተከራክራለች።

ከለቀቀችው ተንቀሳቃሽ ምሥል የተወሰነው ብቻ ተቆርጦ ከአውድ ውጪ እንደተወሰደም ገልጻለች።

የሪያድ ፖሊስ “ከአንድ ሴት ጋር ወሲባዊ ይዘት ያለው ንግግር ያደረገች ሴትን በቁጥጥር ሥር አውለናል። ድርጊቷ የማኅበረሰቡን ሞራል ይነካል” ብሏል።

የሳዑዲ መገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ፣ ዩቲዩብ ከሙስሊም አገር መርህ ጋር የሚጻረር ይዘት ያላቸውን ቪድዮዎች እንዳያስተዋውቅ ከሰሞኑ ጠይቋል።

ተቆጣጣሪው ዩቲዮብ ካልታረመ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።